አዲሱ ገረመው
ቃላዊ ግጥም ባህል መሠረት በማድረግ የተለያዩ ማህበራዊ አጋጣሚዎች ላይ በግለሰብም ሆነ በቡድን የሚቀርብ የጥበብ ዘርፍ ነው። ምሁራን ከሚሰጡት ብያኔ መረዳት የሚቻለው የቃላዊ ግጥሞች የተለያዩ አጋጣሚዎችን መነሻ በማድረግ የሚቀርቡ፤ በአጭር የግጥም ቅርፅ ተሽሞንሙነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ የአንድ ማህበረሰብ ጥበባዊ ሀብቶች መሆናቸውን ነው ።
በዛሬው የማረፊያ አምድ ትኩረታችንን በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ልናደርግ ፈቅደናል። ለመነሻ ይሆነን ዘንድ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመርሀቤቴ ወረዳ ክብረ በዓላት ላይ የሚያተኩሩ አንዳንድ ቃላዊ ግሞችን ከአውዳቸው በመሰብሰብ ይዘታቸው ምን እንደሚመስል ‹‹አባይን በማንኪያ›› እንዲሉ የተወሰኑትን በመምዘዝ ለመመልከት ወደናል። ለመሆኑ ቃላዊ ግጥሞች በዚህ የአገራችን ክፍል ምን ይዘት ይኖራቸው ይሆን ?
ከወረዳው ትምህርት መምሪያ ዋና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከመርሐቤቴ ወረዳ ህዝብ 90 በመቶ ያህሉ ነዋሪ ገበሬ ነው። የመርሀቤቴ ህዝብ የሚታወቅበት የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶችና ወጐች አሉት። እነዚህም ልማዶች ጥንትም ነበሩ። አሻራቸው ሳይጠፋ ዛሬም አሉ ።በተለይ እንግዳ ተቀባይነቱ፣ ሰው አክባሪነቱ፣ ታማኝነቱ፣ ቃል ጠባቂነቱ፣ አምራችነቱና፣ ወዳጅነቱ የማህበረሰቡ መገለጫዎች ናቸው።
መርሐቤቴዎች እንደ ሌሎች ማህበረሰቦች ሁሉ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ እምነታቸውን ወግና ልማዳቸውን የሚያንፀባርቁባቸው የተለያዩ የስነ ቃል ሀብቶች አላቸው። ከእነዚህ የስነ ቃል አይነቶች መካከል እንቆቅልሾች፣ አፈ ታሪኮች፣ ተረቶች፣ የስራ ላይ ግጥሞች፣ የባህል ዘፈኖች የሚጠቀሱ ናቸው። እስቲ የመርሀቤቴ ህዝብ ቃላዊ ሀብቶች በሆኑ የክብረ በዓላት ግጥሞች ላይ አብነታዊ የይዘት ትንተና በማድረግ ለመመልከት እንሞክር ።
በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ የቃል ግጥሞች እንደ አይነታቸውና የሚከወኑበት አውድ ይለያያሉ። አውዱ ብቻ ሳይሆን ይዘታቸውም የተለያየ ነው። ዘርፈ ብዙ ከሆኑና በአካባቢው ከሚዘወተሩት ውስጥ የውዳሴና የፍቅር ቃል ግጥሞች ጥቂቶቹን ጀባ እንበላችሁ፡፡
በአካባቢው ባለሙያ ሴትን ለማወደስ፣ ቁንጅናዋንና ቁምነገረኝነቷን ለማሳየት ከሚደረደሩት ስንኞች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል።
ዘምባባ ዘምባባ ማሪ ዘንባባ
ዘምባባዬ፤
ጓዴ ባልንጀራዬ።
ልዙር ከኋላሽ፤
ዘንባባዬ፤
ለመልክሽም አይደል
ዘንባባዬ፤
ለቁምነገርሽ።
በዚህ ማሪ ዘንባባ በተሰኘ ጨዋታ ውስጥ ያሉት ግጥሞች ባልንጀራሞች የሆኑ ሴቶች እርስ በርስ የሚወዳደሱበት ነው። በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ዘንባባ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ነገሮች የሚመሰሉበት በመሆኑ ጓደኞቻቸውንም በዘንባባ በመመሰል ስለቁምነገርና መልካምነት የሚያወድሱበት፤ ከመልክም በላይ ውስጣዊ ማንነትና ስብዕናን የሚያጐሉበት የቃላዊ ግጥም ጨዋታ ነው ።ከዚህ ቀጥለውም፦
አይንና ጥርሷ የእግዚአብሔር ስራ ነው፤
እኔን የገረመኝ አረማመዷ ነው፡፡
በማለት በቃል ግጥሙ መልኳ በተፈጥሮ የሚያምር ደምግባት ያደላት ሴት መሆኗን በመግለፅ ከዚያ በላይ ደግሞ የእሷ የአረማመድ ለዛ ተጨምሮበት ውብ አድርጓታል በማለት ወጣት ወንዶች የመረጧትን ሴት የሚያወድሱበት ነው ።
የፈተለች እንደሁ አስመስላ ጭራ፤
የጋገረች እንደሁ አስመስላ ሞራ፤
አትወዳደሩ ሴቶች ከሷ ጋራ ።
የዚህ ቃል ግጥም አንድምታ፤ ፈትል በማንም ሊከወን የሚችል ተግባር ቢሆንም፣ እንጀራ መጋገርም እንዲሁ ሁሉም ቢሰራውም፣ ግጥሙ የተገጠመላት ሴት ግን ከሌሎች ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደተሸጋገረች የሚገልፅ ነው ።በመሆኑም ከባለሙያዎቹ የምትበልጥ ባለሙያ እንደሆነች የሚያቀነቅኑበት ነው ።በዚህ ሳይወሰኑ የሚከተለውን ግጥም ደግሞ ያዥጎደጉዱታል፤
ቀሚስሽ ከመሬ መቀነትሽ ከመሬ፤
እከሊት አበሉ ታምሪያለሽ ለኔ ።
የአካባቢው ተወላጅ አባቶች መሬ በባህሉ በወግና ልማዱ ተወዳጅ ነው። ይሄንን ባህል አጥብቀው የሚይዙትም ይወደዳሉ ይላሉ። በመሆኑም አለባበሷን መሬኛ አድርጋ የለበሰችና የተዋበችን ሴት ማማሯን በሚወዳት ወንድ ይነገራታል በማለት ቃል ግጥሙ የውበት ማወደሻ መሆኑን ይናገራሉ። እስቲ ለፅሁፋችን መደምደሚያም እንዲሆነን አንድ ተጨማሪ ቃላዊ ግጥም እናክልላችሁና የመሬዎችን ባህል ወግ የዳሰስንበትን ቆይታ እንቋጭ።
ይሄ የቆላ እንጨት አይነድም ይጨሳል፤
የእከሌ ዓመሉ አንጀትን ያርሳል፡፡
ይህ ቃል ግጥም ደግሞ አንዲት ኮረዳ ሴት በአመሉና በፀባዩ ተወዳጅ የሆነውን ወንድ ስለ ፀባዩ፣ ደግነት፣ የዋህነት፣ ወዘተ መልካም ስብዕና በማንሣት የምታወድስበት የቃል ግጥም ነው። ይህ ማህበረሰብ በነዚህ ግጥሞች ብቻ ያልተወሰኑ በርካታ ሃብቶችና ማንነቱን የገነቡ መሰረቶች ያሉት ነው።
የፍቅር ቃላዊ ግጥሞች፡- በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ቃል ግጥሞች በተቃራኒ ፆታ መካከል ወዳጅነትን ለመግለፅ፣ የመፈላለግ ስሜትን ለማንፀባረቅ እንዲሁም በፍቅር በመጐዳት ሳቢያ የደረሰን ስሜት፣ ወዘተ አስመልክቶ መልዕክቶች ይተላለፋሉ። ከዚህ በታች የቀረቡ ቃል ግጥሞችም በዚህ ድንበር ውስጥ የሚቀነቀኑ ናቸው ።
እቴ ባንቺ ነገር ባንቺ የተነሣ፤
ቅዳሴውም ቀረ ዳዊቱም ተረሣ፡፡
በቃል ግጥሙ በሴቷ ፍቅር የተነደፈው ወጣት የፍቅሩን ጥግ መድረስ ሲገልፅላት የተጠቀመበት ቃላዊ ግጥም ነው ። በዚህ ቃላዊ ግጥም እሷን እሷን ብቻ እያሰበ ስራ መፍታቱን የሚገልፅበት መንገድ ነው ።ወጣቱ ከሀይማኖታዊ ተግባራት መቆጠቡ የቱን ያህል ጥልቅ ፍቅር ውስጥ እንደገባ ይገልፃል ።
አባትሽ በጡቻ ወርውረው ሣቱኝ፤
ወንድምሽ በአንካሴ ወርውረው ሣቱኝ፤
እናትሽ በድውይ ወርውረው ጣሉኝ፤
አንቺን ስል ነው እንጂ ሊጥ አልደፋሁኝ፡፡
ወጣቱ የወደዳትን ልጃገረድ ከቤተሰቧ ተደብቆ ለማየት ሲሞክር አባትና እናቷ ወንድሟም በጥላቻ አይን ሁልጊዜ ሲመለከቱትና አሳሩን ሲያሣዩት እሱ ደግሞ ምሬቱን በግጥም ይገልፅበታል። የደረሰበት እንግልት እሷን ወዶ ባደረገው እንቅስቃሴ እንጂ ሌላ ምንም አለማጥፋቱን “አንቺን ስል ነው እንጂ ሊጥ አልደፋሁ ብሎ ይዘፍንላታል።
ታዲያ እኛ የአምዳችን ምጣኔ ይገድበናልና ቀሪውን እናንተ ወደ ስፍራው ሄዳችሁ እንድትቃኙት ጋበዝን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም
Hi! This is my first comment here so I just wanted to give a quick shout out and tell
you I really enjoy reading through your blog posts.
Can you suggest any other blogs/websites/forums that
go over the same subjects? Thank you!
you’re really a excellent webmaster. The site loading velocity is incredible.
It sort of feels that you’re doing any unique trick.
Furthermore, The contents are masterpiece. you’ve done a wonderful activity
on this topic!