የመሬት ጉዳይ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ቦታ አለው። አራሽ ገበሬው ምርት ቢያዘጋጅ ያለመሬት አይሆንም፣ ሰራተኛውም ቢሆን ቦታ ቤት ለመስራት መሬት ስለሚሻ ለመሬቱ ያለው ግምት ከፍተኛ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ከተወለደ ጀምሮ መሬቴ እያለ ኖሮ ከሞተ በኋላም እንኳን አስክሬኑ የሚቀበረው በአካባቢው ባለ መሬት ነው። ይህ ሁሉ ጉዳይ ከማህበረሰቡ አኗኗር ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ስለመሬት እና ስለህገመንግስቱ አንቀጾች የበለጠ መወያየት እና መግባባት ያስፈልጋል።
አቶ መድህን አሚር የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። ‹‹ህገ መንግስቱን የተለያዩ ሰዎች የየራሳቸውን ግምታዊ ምክንያት እየሰጡ እንደሚተረጉሙት እረዳለሁ›› ይላሉ። ለአብነት አንድ ሰው መሬት የመንግስት ነው ይላል። ነገር ግን መሬት ደግሞ ሲሸጥ እና ሲለወጥ ሲያይ መሬት የመንግስት ነው ከተባለ ለምን ግለሰብ ይሸጠዋል የሚል ክርክር ያነሳል። ሌላው ደግሞ መሬት የህዝብና የመንግስት ነው ስለሚባል በአንድ መሬት ላይ ህዝብም መንግስትም እኩል የመወሰን መብት አላቸው ብሎ ይከራከራል። በመሆኑም በመሬት ላይ በህገመንግስቱ የተጻፉ አንቀጾች ዝርዝር ጉዳያቸው ምን ማለት እንደሆነ በየጊዜው በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ መድረኮች ላይ ግልጽ የሆነ ሃሳብ ቢቀመጥ መልካም ነው።
አቶ መድህን እንደሚያስረዱት፤ መሬት ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ቦታ አለው። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን አብዛኛው መሬት በንጉሣውያን ቤተሰብ የተያዘ በመሆኑ መሬት ላራሹ የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር። በደርግ ዘመን ደግሞ መሬት ከባላባቶች ላይ ተቀምቶ ለህዝቡ እንዲከፋፈል ተደርጓል። አሁን በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ ንብረት መሆኑ ይገለጻሉ። ይሁንና በየጊዜው የመጡ ሹማምንቶች ሲሸጡት እና ሲለውጡት ነበር። ህዝቡም ያሻውን መሬት እየሸጠ ያሻውን በገንዘቡ ሲገዛ ኖሯል። ይሁንና በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት ስለመሬት የሚያነሳቸው የተለያዩ ሃሳቦች ናቸው። በመሆኑም አመርቂ መረጃ ለህዝብ ማስተላለፍ ይገባል።
ወይዘሮ ዙሪያሽ አለሙ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። በበኩላቸው ህገመንግስቱን እና ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተያያዙ አንቀጾቹን በወጉ እንደማይረዷቸው ይናገራሉ። የህገመንግስቱ አንቀጽ ውስጥ ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው ሰፍሯል። በተለይም መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው ተጽፏል፡፡ እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው ይላል። በመሆኑ መሬትን እንደዋነኛ ንብረት ይቆጥረዋል። በሌላኛው አንቀጽ ላይ ደግሞ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የጋራ ሃብት ነው ይላል። ይህ ሁልጊዜም ይጋጭብኛል ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ መሬት በሊዝ እንደሚከራይ የሚናገሩት ወይዘሮ ዙሪያሽ፤ በአንድ ወገን ለሃምሳ አመት እና ለመቶ ዓመት መሬት ገዛሁ ሲባል በሌላ ወገን ደግሞ መሬቱ ለኪራይ ነው ይባላል። መሬቱ ተከራዩም ተሸጠም ግን የሚጠቀሙት አካላት ገንዘብ እስካለችው ድረስ የትኛውንም ሰፊ መሬት ያህል ቢወስዱ ይፈቀድላቸዋል። በተለይ ሰዎችን አፈናቅለው ካሳ እስከከፈሉ ድረስ መሬቱ የሚሰጣቸው መሆኑን የሚያስቡ በርካታ ባለሃብቶች አሉ። ይህ ጉዳይ ደግሞ አብዛኛውን የመሬት ይዞታ ያለውን ዜጋ ይዞታው ላይ መወሰን የሚችለው መንግስት ብቻ እንደሆነ አድርጎ እንዲያስብ አድርጓል። የመሬት ባለይዞታው ዜጋ ደግሞ በመሬቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ መወሰን እንደማይችል አድርጎ እራሱን ይገምታል። በመሆኑም ግልጽ ውይይት የሚያስፈልጋቸው አሊያም ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው የህገ-መንግስት አንቀጾች አሉ።
በህገ-መንግስት እና ፌዴራሊዝም ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ዶክተር አሰፋ ፍስሃ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በህገመንግስቱ የመሬት ጉዳይ ላይ የተጻፉ አንቀጾች አሻሚ ናቸው። አንቀፅ 40 ንጹስ አንቀጽ ሶስት ላይ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ መሆኑ ሰፍሯል። እዛው ላይ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት መሆኑን ይገልጻል። በመሆኑም በአንድ በኩል የመሬት ባለቤትነት የመንግስት እና የህዝብ ሲለው በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያደርገዋል። ይህ አገላለጽ መንግስት እና ህዝብ አንድ ናቸው ከሚለው ሃሳብ የመጣ ከሆነ የተሳሳተ ነው። መንግስትና ህዝብ አንድ ሆነው አያውቁም። መንግስት በየጊዜው የሚቀያየር ሲሆን ህዝብ ግን የማይለወጥ ነው።
እንደ ዶክተር አሰፋ ገለጻ፤ በአንቀጽ አርባ ስር በተመሳሳይ የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን እንደሚ ያስከብርላቸው ተቀምጧል። በተጨማሪ ማንም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ፣ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት እንዳለው ተጽፏል። ይህ መብት የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነቱ ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት፣ ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብትን ያካትታል፡፡
ይህ ሁሉ ጉዳይ ባለበት ደግሞ ሌሎችም አሻሚ አንቀጾች አሉ። አንቀጽ 40 የንብረት መብት ላይ እንደሰፈረው፤ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ይወጣል፡፡ የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነጻ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሕግ እንደሚወሰን ይገልጻል። ይሁንና አርሶአደሮች በሁለት ብር እና በአምስት ብር የካሬ ሜትር ካሳ ክፍያ ከመሬታቸው ላይ ሲነቀሉ ከዚህ ቀደም ተስተውሏል።
የስልጣን ክፍፍልን በሚያመለክቱት የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 51 እና 52 ላይ መሬት ማስተዳደርን ለክልሎች ሃላፊነት ይሰጣል። በሌላ በኩል ህግ እና አዋጅ በተመለከተ መብቱን ለፌዴራል ያደርገዋል። ነገር ግን ኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲሰጥ አንዳንዶች በክልሎች ይዞታ ስር ያለውን ሰፊ መሬት ከፌዴራል መንግስት ተሰጥቷቸው ይሰራሉ። አንዳንድ ክልሎች ደግሞ ከስንት ሺ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት ነው በፌዴራል መንግስት የሚወሰነው ከስንት በታች ሲሆን ነው በክልል የሚወሰነው የሚለው ሃሳብ ስለሌላቸው በቃል የተነገራቸውን ይዘው ይሰራሉ። አንዳንዶች ከአምስት ሺ ሄክታር በላይ የፌዴራል መንግስት ነው የኢንቨስትመንት ጉዳይ የሚያገባው ብለው ይጠይቃሉ። በመሆኑም የህገመንግስቱ የመሬት ጉዳይ የያዙ አንቀጾች በድጋሚ መፈተሽ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የተሻለ መግባባት እንዲፈጠር በጉዳዩ ዙሪያ የተጠናከረ ውይይት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ጌትነት ተስፋማርያም