
ገና በወጣትነቱ የዝናን ካባ የደረበ በተለይ በትወና ብቃቱ ብዙዎች አድናቆትን ቸረውታል። ከፊልም ሙያ ውጪ ያማረ ቁመናውን አይተው ሞዴል እንዲሆን ለገፋፉት ምክራቸውን ተቀብሎ በተግባር ስኬታማ ሆኖ አሳይቷቸዋል። በስራው ላይ የሚያሳየው መልካም ባህሪ ተወዳጅነቱን ከፍ አድርጎታል።አዲስ አበባ መርካቶ ዙሪያ ልዩ ስሙ ሰባተኛ አካባቢ ነው የተወለደው። መኖሪያው ደግሞ ሸጎሌ አካባቢ። ዝነኛው የፊልም ሙያተኛና ሞዴል ባህሬን ከድር።
የፊልም ሙያተኛ ሳይሆን በፊት የቅርጫት ኳስ ተጫዋች መሆንን ተመኝቶ ነበር። ወደ ፊልም ስራ በአጋጣሚ ነበር የገባው። ነገር ግን አይቶም የወደደው፣ የስኬት ደጃፍ የረገጠበት ሙያ ፊልምና ሞዴሊንግ ሆኖ አገኘው። ሞዴሊንግ ላይ ሲሰራ የተመለከተው ታዋቂው የፊልም አዘጋጅ በላይ ጌታነህ ተመልክቶት ለሚሰራው አንድ ፊልም አጨው። የመጀመሪያ ፊልሙን የተመለከቱት ሌሎች የፊልም ባለሙያዎች አይተው እና አድንቀው የአብረን እንስራ ጥያቄም አቅርበውለት ሰርቷል። አሁንም ዘወትር ከሙያው ላለመጥፋት ምክንያቱ ይሄው ነው።
የኪነ ጥበብ ተሳትፎና ያበረከተው ፋይዳ ገና ወደ ሙያው ሲገባ የተወነበትና የበዙ አድናቂዎች ባገኘበት ሌዲስ ፈርስትን ጨምሮ ምህረት፣ ባትመጪም ቅጠሪኝ፣ ሀ ግዕዝ፣ ባንቺ ጊዜ፣ ጥቁርና ነጭ፣ የሴት ፍቅር፣ ላላገኛት እና ሌሎች 17 ታላላቅ ፊልሞች ላይ ተሳትፏል። በተለይም በመሪ ተዋናይነት የተሳተፈባቸው ፊልሞቹ ላይ ተላብሶ የተጫወታቸው ገፀ ባህሪያት በዕውኑ ዓለም ላይ ያሉ ያህል ከብዙዎች አዕምሮ የማይጠፉ ሆነዋል።
ለፊልም እድገት
የባለሙያው ቀና የእርስበእርስ ትብብር የፊልም ሙያን ያሳድገዋል። የመንግሥት ትኩረትና የሚሰጠው ተገቢውን ያህል መሆን አለበት። በኪነ ጥበብ ብዙ ማስተማርና የተሻለ ትውልድ መፍጠር ይቻላል። ማህበረሰቡም ለፊልም ያለው አተያይ የተሻለ መሆንም ይገባዋል። ፊልም የሚገባው ያህል ጥቅም ይሰጥ ዘንድም ሁሉም ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
የዕረፍት ጊዜ
አብዛኛው የዕረፍት ሰዓቱን ከልጆቹ ጋር በቤት ውስጥ ያሳልፋል። ከቤተሰብ ጋር ከተማ ወጣ ብሎ መዝናናት ያስደስተዋል። ወጣ ሲል ቢሾፍቱ ሀይቆች ላይ የሚገኙ የመዝናኛ ስፍራዎችን ይመርጣቸዋል። እርግጥ እረፍትን አያበዛም። ሆኖም ባገኘው ትርፍ ጊዜ አብዝቶ ብቻውን ፀጥታ የሰፈነባቸው ቦታዎች ላይ ተገኝቶ መመሰጥና እራሱን ማድመጥ ያዝናናዋል።
“እኔ የመርካቶ ልጅ ነኝ፤ ቀለል ያለ አኗኗር እመርጣለሁ። እንደ አካባቢዬ ሰዎች ነገር ሲቀል ይመቸኛል” የሚለው ባህሬን፤ በእረፍት ሰዓቱ ቀለል ባሉ ልብሶች መዘነጥ ይወዳል። ቱታና ቁምጣ በካናቴራ ለብሶ ልጆቹን ይዞ ምቹ እና እረፍት የሚሰጥ አካባቢ ላይ ይገኛል።
ባህሬን ጥሩ አባትም ነው። ልጆቹን መልካም ነገር እያዩ እንዲያድጉ ይጥራል። ለዚህም ማሳያው የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ (በተለይ እርዳታ የሚሰጥባቸው ቦታዎች) ይዟቸው በመቅረብ ሰዎችን መርዳት አስፈላጊ መሆኑን በተግባር እንዲያዩ ነገም ተመሳሳይ ተግባር እንዲፈጽሙ መንገድን ያሳያቸዋል።
ከቲማቲም ከሚሰሩ ምግቦች ውጪ የሚመርጠው የምግብ አይነት የለም። ሁሉንም የምግብ አይነቶች ይጠቀማል። ነገር ግን ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እርሱ ጋር ቦታ የላቸውም፤ ባህሬን በአመጋገቡ ይለያል። በቀን ሶስቴ መብላት ስለለመድን የእርሱ አመጋገብ ሊያስገርመን ይችላል። እራት ፣ ቁርስ ብዙም አይደለም ምሳ ላይ ግን አይደራደርም። ምሳን በደንብ በልቶ ሌሎችን ማለፍ ያዘወትራል።
መልዕክተ ባህሬን
ወጣቱ የፊልም ባለሙያና ሞዴል ባህሬን ከድር ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታችንን በማስመልከት ለኢትዮጵያዊያን ይህንን መልዕክት አስተላልፏል። “የፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነቶች የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን ላይ ችግር ሊፈጥርብንና ለዘመናት የዘለቀው አብሮነታችንን ሊያሻክረው አይገባም። እኛ ኢትዮጵያችን በዕምነት ሳንለያይ፣ በጎሳ ሳንነጣጠል ለረጅም ጊዜ የኖርን ነን። ዛሬ ይህንን ልማድና ባህላችንን የሚንዱ ተግባራት እየታየ ነው። ይህ ደግሞ አገርን ይጎዳል። አገር ደግሞ ከሁሉ ነገር ይቀድማል። ስለ ኢትዮጵያ ደህንነት ስንል በምክንያት ማመንን ባህል እናድርግ። የምናደርገውንና አድርጉ የምንባለውን በትክክል ከለየን፤ ምክንያታዊነት ካስቀደምን እንግባባለን” በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበረውን ቆይታ ይቋጫል። ቸር ይግጠመን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
ተገኝ ብሩ