የትኛውም አሁነኛ ማህበረሰብ በትውልዶች ቅብብል፣ በዘመናት መካከል በማያቋርጥ ትስስር ህያው ሆኖ የመጣና የሚሄድ ነው። በዚህ ዘመናትን በሚያስተሳስር፤ እንደ ወንዝ ውሃ በሚፈስ የትውልዶች ፍሰት ውስጥ እያንዳንዱ ትውልድ በዘመኑ ራሱን አሻጋሪ ትውልድ አድርጎ በማሰብ የሚጠበቅበትን ትውልዳዊ ኃላፊነት እየተወጣ በትውልዶች ፍሰት ውስጥ የራሱን አሻራ አስቀምጦ እውነቱን አጽንቶ ያልፋል።
ይህ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ያለ የነበረና የሚኖር እውነታ ነው። ከዚህ እውነታ ያፈነገጠ የማህበረሰብ የህያውነት ጉዞ በአብዛኛው ያንን ማህበረሰብ አደጋ ውስጥ የሚከት፤ የተደራረቡ ትውልድ ተሻጋሪ ማህበራዊ ችግሮች ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም የቀደሙ ታሪኮች በተጨባጭ የሚያሳዩት ነው።
አንድ ትውልድ በቀደመው ትውልድ መሰረት ላይ ሆኖ አሁነኛ እውነታዎች የሚፈጥሩትን አዳዲስ ፍላጎቶችን አውቆና ተረድቶ እራሱን በትውልዱ ውስጥ አሻጋሪ አድርጎ በመቅረጽ፣ በተፈጠሩ አሻጋሪ እውነታዎች በመታገዝ የማህበረሰቡን ቀጣይነት አጽንቶ ማለፍ ይጠበቅበታል።
ያደጉ አሁነኛ ፍላጎቶች ሁል ጊዜ ማህበረሰብ በለውጥ ውስጥ እንዲኖር ያደርጉታል። ከዚህም የተነሳ የለውጥ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ይሆናል። ለውጥ ከአሁነኛ ፍላጎት የሚመነጭ መሻት ነው። አሁነኛ ፍላጎት ከተጨባጭ ከባቢያዊ እውነታዎች ጋር ከሚኖረው ትስስር አንጻር ሲታይ ደግሞ የህልውና ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ይሆናል።
ይህንን ተፈጥሯዊ ሂደት መረዳት የቻለ ማህበረሰብ ምንም ዓይነት ተግዳሮት ቢያጋጥመው፣ የቱንም ያህል የዛሬ እውነታዎች ጫና ቢፈጥሩበትም በለውጥ ሂደት ውስጥ ህልውናውን እያስጠበቀ በአሸናፊነት ዘመናትን ለመሻገር የሚያስችል አቅም ባለቤት ስለመሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፤ የማህበረሰብ ታሪክም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው።
ይህንን ከሀገራችን ተጨባጭ ታሪካዊ እውነታ አንጻር ለማየት ስንሞክር ብዙ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንገደዳለን። ሀገራችን በቀደሙት ዘመን የትላልቅ ስልጣኔዎች ባለቤት ስለመሆኗ ብዙ የሚያጠያይቅና ግር የሚያሰኝ እውነታ አይደለም። ለዚህ የሚሆኑ ዘመን ገላጭ የታሪክ አሻራዎች በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ብዙ ሳንቸገር ማግኘት ይቻላል። እነዚህን የቀደመው ትውልድ የታሪክ ቅርሶች በአግባቡ ማጥናት ከተቻለ ደግሞ ያ ትውልድ ያደገ አዕምሮ እና የመሥራት ጽናት ባለቤት እንደነበረው ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም።
የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናትን ቋጥኝ ፈልፍሎ የሠራ ፤ የአክሱም ሐውልትን ከአንድ ወጥ ቋጥኝ ፈልፍሎ ያቆመ ወዘተ እያልን የቀደመውን ትውልድ የፈጠራ አቅምና የመሥራት ጽናት ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት፣ በተለይ ደግሞ በዚህ ዘመን ላለው ትውልድ ከባድ አይደለም።
እንቆቅልሽ የሚሆነው ግን እኛ የዚያ ማህበረሰብ አካል ሆነን ስለምን ያንን የፈጠራና የመሥራት ጽናት ማስቀጠል አልቻልንም የሚለው ነው። ስለምን እኛ ከኛም በፊት የነበሩ ትውልዶች እንደ ትውልድ ያንን ትልቅ ማህበራዊ እሴት ባለቤት መሆን አልቻልንም፤ አልቻሉም? ያንን ትልቅ ሀብት ምን ወሰደብን? የት ጋር ጣልነው? እንዴትስ ጣልነው? ከሁሉም በላይ በታሪኩ ከመኩራራት እና ከመፎከር ባለፈ ለምን በቀደሙ ትውልዶች ታሪክ ውስጥ እራሳችንን ለማየት አልቻልንም? ቁጭት እና መነሳሳትን በሚፈጥር መልኩ ያንን ትውልድ እንዳናስብ ምን ዓይነት አዚም ወደቀብን?
ለእነዚህ ጥያቆዎች አግባብ ባለው ሁኔታ ምላሽ መስጠት ካልቻልን ቀጣዩን የብልጽግና ጉዞ ጀምሮ ለመጨረስ የሚያስችለን አቅም ሊኖረን አይችልም። በቀደሙት ዘመናት የነቃን መስሎን በብዙ መፈክሮች የጀመርናቸው የለውጥ መንገዶች ብዙ መንገድ እንዳላስኬዱን እንዲሁ እንዳይሆን ቆም ብለን ልናስብ ይገባል።
በዘመናት መካከል ከተኛንበት ጥልቅ እንቅልፍ ሊያነቃን የሚያስችለን ፤በነቃ ማንነት ዘመን ተሸጋሪ የህይወት ምዕራፍ ውስጥ ሊከተን የሚችለው በታማኝነት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላስ መስጠት ስንችል ነው። መሰረቃችንን ብቻ ሳይሆን ማን እና እንዴት እንደተሰረቅንም ስናውቅ ነው።
ይህ ለቀጣይ እንደ ትውልድ ልንሠራው ላሰብነውም ሆነ ልንሄድበት ለመረጥነው የብልጽግና መንገድ ስኬት አልፋና ኦሜጋ ነው። ለጉዟችን አቅም የሚሆን አውነተኛ ቁጭትና አራማጅ ስንቅ ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2012