ከተሞች ህይወት ያላቸው የሰው ልጆች መኖሪያ፣ መዝናኛና የሥራ ቦታ እንደ መሆናቸው መጠን ለአንድ ከተማ ነዋሪዎች አረንጓዴ ሥፍራዎችና መዝናኛ ቦታዎች የሳንባ ያህል የሚቆጠሩ ቢሆኑም፤ በአገሪቱ እየታየ ካለው የከተሞች እድገት ጎን ለጎን ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ በመስፋፋቱ የአረንጓዴ ሥፍራዎችና ኳስ መጫዎቻ ሜዳዎች ጭምር ሳይቀሩ በካሬ ሜትር እየተሸነሸኑ ተሽጠው ሕንፃ ተገንብቶባቸው ወጣቶች መዝናኛ አጥተው ለሱስ ተጋላጭ በመሆናቸው በየከተሞች ወንጀል ተበራክቷል። በከተሞች ሕፃናትና ጡረተኞችም የሚዝናኑባቸው ሥፍራዎች አጥተው እንደ ቤት እንስሳ ታስረው ይውላሉ፡፡
ይህ ችግር ጎልቶ የሚታይባት አዲስ አበባ ዛሬም እንደትናንቱ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ መጥቷል በተባለበት ወቅት በከተማዋ የህግ አግባብነት የሌላቸው ህገ ወጥ የቤቶች ግንባታና የመሬት ወረራ በከፍተኛ ሁኔታ ከለውጡ በኋላም ተጧጡፎ የቀጠለ ሲሆን፤ የመዲናዋ ነዋሪዎች በከተማዋ የሚስተዋለውን ይህን ህገወጥ የመሬት ወረራና የቤቶች ግንባታ ከተማ አስተዳደሩ እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።
የከተማ አስተዳደሩም በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን ከማፍረስ በተጨማሪ ውስን የሆነውን የህዝብ ሃብት ከህገወጦች ለመከላከልና በህገወጦች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተደጋጋሚ ቢናገርም እስካሁን በተጨባጭ የተወሰደ አስተማሪ እርምጃ አልታየም።
በመሆኑም በመዲናዋ ከመቼውም ጊዜ በላይ በባለሃብቶች፣ በመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ በደላሎችና የፖለቲካ አጀንዳ ባላቸው ኃይሎች ተዋናኝነት ጭምር ህገወጥ የመሬት ቅርምቱና የቤት ግንባታው ተጧጡፎ መቀጠሉን አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከነዚህ መካከል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ቀጠና አምስት በተለምዶ ኢንዱስትሪ ሰፈር የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ከ25 ዓመት በላይ በኳስ ሜዳነትና በአረንጓዴ ልማት ሲገለገሉበት የነበረውን ቦታ ያለአግባብ ለግለሰቦች ተሰጥቶብናል በሚል ቅሬታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበውልናል።
የዝግጅት ክፍላችንም ነዋሪዎቹ ከ25 ዓመታት በላይ ሲገለገሉበት የነበረው ኳስ ሜዳ በምን አግባብ ለግለሰቦች እንደተሰጠ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽና የቅሬታ አቅራቢዎቹን እሮሮ እንዲሁም የጽሁፍ ማስረጃዎችን ፈትሸን ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች እሮሮ
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ቀጠና አምስት የወጣቶች ተወካይ ወጣት ሮቤል ፀጋዬ እንደተናገረው፤ ኳስ ሜዳው በአካባቢው ያለ ብቸኛ ሜዳ በመሆኑ የአካባቢው ወጣቶች ከልጅነት እስከ እውቀት በሜዳው እየተጫወቱ ማደጋቸውን ይናገራል። ከ15 ዓመታት በላይ በዚህ ኳስሜዳ ጧት ማታ እየተጫወቱ ሲያድግ ቦታው ላይ ቤት እንዳልነበረበት ጠቁሞ፤ በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭትን ለመግታት ወጣቱ በቤቱ ተወስኖ በተቀመጠበት ወቅት ሶስት ግለሰቦች በአሳቻ ሰዓት መጥተው በአንድ ቀን ሙሉ ለሙሉ ኳስ ሜዳውን አጥረው ግንባታ እንደጀመሩበት ይናገራል።
ወጣት ሮቤል ግለሰቦቹ ኳስ ሜዳውን እንዳጠሩት ወዲያውኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ከልጅ አስከ አዛውንት ተሰባስቦ በምን አግባብ ለዘመናት በኳስ ሜዳነትና በአረንጓዴ ልማት ሲገለገሉበት የነበረን ቦታ ለግለሰቦች ተሰጠ የሚለውን ጥያቄ ይዘው ክፍለ ከተማውን መጠየቃቸውን ገልጿል።
ክፍለ ከተማውም ቦታው ለግለሰቦቹ በምን አግባብ እንደተሰጠ መልስ የምታገኙት ወረዳው ላይ ነው የሚል መልስ እንደሰጣቸው ወጣት ሮቤል ጠቁሞ፤ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ በቃናን አግኝተው ወረዳው ኳስ ሜዳውን በምን አግባብ ለግለሰቦቹ እንደሰጠ በተደጋጋሚ ባቀረቡት ጥያቄ፤ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሰዎቹ ህጋዊ ናቸው ከሚል ውጭ ምንም ተጨባጭ መረጃ ሊሰጡ አለመቻላቸውን ተናግሯል።
ወጣቶችም እነዚህ ግለሰቦች ባለፉት 25 ዓመታት
የት ቆይተው ነው? አሁን ላይ ድንገት መጥተው ከ1997 ዓ.ም በፊት ቤት ሰርተው ይኖሩበት እንደነበርና አሁንም እየተዳደሩበት እንደሚገኝ የሚገልጽ መረጃና ካርታ ይዘው የመጡት ብለው የወረዳውን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲጠይቁ፤ ዋና ስራ አስፈጻሚውም አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ በሚል ቦታውን በምትክ እንደተሰጣቸው መናገራቸውን ወጣት ሮቤል ገልጿል።
ወጣት ሮቤል ኳስ ሜዳው ከአንድ ሺ በላይ ካሬ ሜትር እንደሚሆን ጠቁሞ፤ ወጣቶችም አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆች እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ ይውደቁ አይባልም። ነገር ግን በአካባቢው ወጣቶች የሚዝናኑበት ምንም ሌላ አማራጭ መጫዎቻ ኳስ ሜዳ ስለሌለ ለአርሶ አደሮቹ ሌላ ምትክ ለምን መስጠት አልተቻለም? ለአካባቢው ማህበረሰብ ለአረንጓዴ ልማትና ለኳስ ሜዳ የተሰጠውን ቦታ ለገበሬ ልጅ ምትክ ብሎ መስጠት ተገቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
የተለያዩ አማራጮች እያሉ ወጣቶችን ከአልባሌ ቦታ የሚታደግ የስፖርት ማዘውተሪያ ለልማት ተነሺዎች ምትክ በሚል ወጣቶችን በትኖ ለሶስት ግለሰቦች መስጠት ወጣቱ ጫትና ሺሻ ቤት እንዲውል መገፋፋት ነው፤ የሚለው ወጣት ሮቤል፤ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቦታውን ወርደው ቢያዩም ወጣቶች ያቀረቡትን ጥያቄ ወደ ጎን በማለት ሰዎቹ ህጋዊ ናቸው ያልሙበት እንቅፋት እንዳትፈጥሩ። ለወጣቶች ኳስ መጫዎቻ ሌላ ምትክ ቦታ እናፈላልጋለን የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ተናግሯል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ለወጣቶች ኳስ መጫወቻ ምትክ ቦታ እንሰጣለን ብለው ያነሱት ሃሳብ ወጣቱን ለማዘናጋትና የወጣቶችን ጥያቄ ለማደናቀፍ እንጂ ማረጋገጫ የሌለው ነው የሚለው ወጣት ሮቤል፤ ግለሰቦቹ የሚያከናውኑት ግንባታ ቆሞ የቦታው ፕላንና ግለሰቦቹ ቦታውን በምን አግባብ እንደተሰጣቸው ህጋዊነቱ ይጣራልን የሚል ጥያቄ የአካባቢው ማህበረሰብ ቢያነሳም የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ግለሰቦቹ ህጋዊ ናቸው ልማት አታደናቅፉ የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ወጣቱ ይናገራል።
ሌላኛው የአካባቢው ወጣቶች ተወካይ ወጣት ኤርሚያስ ታጠቅ በአካባቢው ወጣቶች ስፖርት የሚያዘወትሩበት ሌላ አማራጭ ኳስ ሜዳ አለመኖሩን ገልጾ፤ ሜዳው የአካባቢው ወጣቶች ከልጅነት እስከ እውቀት ኳስ እየተጫወቱ ያደጉበት መሆኑን ይናገራል።
ነገር ግን ወጣቱ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆን ቤቱ በከተተበት ወቅት ኳስ ሜዳውን ሶስት ግለሰቦች በአሳቻ ሰዓት አጥረው ግንባታ እንደጀመሩበት የሚናገረው ወጣት ኤርሚያስ፤ የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ ወጥቶ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ቅሬታ ያቀረበ ሲሆን፤ ጽህፈት ቤቱ ወረዳው መሬቱ የማን እንደሆነ ያጣራ የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው ወደ ወረዳው ተመልሰው ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
ወጣት ኤርሚያስ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ለግለሰቦቹ የክፍለ ከተማው መሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ስለሰጣቸው ግለሰቦቹ የተሰጣቸው ካርታ ህጋዊ መሆኑን አረጋግጦ የግንባታ ፈቃድ ወረዳው መስጠቱን ገልጿል።
የቦታው ፕላን ምን እንደሚል ይጣራልን የሚል ጥያቄ ወጣቶቹ ቢያነሱም፤ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ኳስ ሜዳው መደበኛ የኳስ ሜዳ መስፈርት የማያሟላ ነው። ለወጣቶች ሌላ ምትክ ቦታ እንሰጣለን። ስለዚህ ሰዎቹ ህጋዊ ናቸው ግንባታቸውን እንዳታደናቅፉ የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ወጣት ኤርሚያስ ተናግሯል።
ግለሰቦቹ የሚያከናውኑት ግንባታ ቆሞ የቦታው ፕላን ይጣራልን የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ የአካባቢው ማህበረሰብ ቢያቀርብም ይሄ ነው የሚል ምላሽ እስካሁን ስላልተገኘ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጣርቶ ፍትህ እንዲሰጠን ሲል ወጣቱ ያሳስባል።
ወጣቱ አንዳንድ የወረዳው ሰራተኞች እናንተ ብቻችሁን አትጋፈጡ። እነዚህ ሰዎች እጃቸው እረጅም ስለሆነ ነገ አንድ ነገር ብትሆኑ ማንም የሚደርስላችሁ የለም የሚል ማስፈራሪያዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንደደረሰው ጠቁሞ፤ እርሱም የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኑ አሁን ላይ መልስ የሚሰጥ አካል ሲጠፋ ጥያቄውን ወደ ኋላ እያለ መምጣቱን ይናገራል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ከ30 ዓመት በላይ ቤት ሰርተው የሚኖሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከ25 ዓመት በፊት ሜዳው ላይ ኳስ ይጫወቱ የነበሩ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተመርቀው ወጥተው ዛሬ በስራ ዓለም ሆነውም በስፖርት ማዘውተሪያነት የሚጠቀሙት የአካባቢው ብቸኛ ኳስ ሜዳ መሆኑን ይናገራሉ።
እርሳቸውም ከዚህ በፊት በ2005 ዓ.ም ኳስ ሜዳውን በተመሳሳይ ለግለሰቦች ልማት ሊሰጥ ሲል ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለአረንጓዴ ስፍራና ለስፖርት ማዘውተሪያ እንዲውል በጠየቀው መሰረት፤ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከአካባቢው ማህብረሰብ ጋር ተነጋግረው፣ ቦታውንም በአካል አይተው ኳስ ሜዳው ለወጣቶች መጫወቻነት እንዲውልና እዛው አጠገብ የሚገኘውን ክፍት ቦታ ትምህርት ቤት እንዲሆን ለህብረተሰቡ መሰጠቱን ይናገራሉ።
ነገር ግን አሁን ላይ ልጆች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከቤት እንዳይወጡ በተከለከሉበት ወቅት ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በአሳቻ ሰዓት ኳስ ሜዳውን በማጠር ህገ ወጥ ግንባታ እያከናወኑበት እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ግለሰቦቹ ሜዳውን ወዲያውኑ እንዳጠሩት የአካባቢው ማህበረሰብ ተሰብስቦ ክፍለ ከተማ ሂዶ ሲያመለክት፤ ክፍለ ከተማው ወረዳውን ጠይቁ ብሎ እንደመለሳቸው ያስረዳሉ።
እርሳቸውም የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ የህብረተሰቡን ጥያቄ በውል ሳያደምጡ ግለሰቦቹ ህጋዊ ስለሆኑ ልማት እንዳታደናቅፉ ይስሩበት የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸው፤ የቦታው ፕላን ምንድነው የሚያሳየው? ግለሰቦቹ ህጋዊ መሆናቸውን በምን አረጋገጡ? ስለዚህ ህጋዊነቱ እስኪጣራ ድረስ ግንባታው ይታገድልን የሚል ጥያቄ ህብረተሰቡ ቢያነሳም በደፈናው ሰዎቹ ህጋዊ ናቸው ልማት አታደናቅፉ የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ከወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ግለሰቦቹ በምን አግባብ የግንባታ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ህብረተሰቡ ጥያቄ ሲያቀርብ ላቸውም፤ ግለሰቦቹ ከክፍለ ከተማው የመሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ይዘው በመምጣታቸው ወረዳው ለግለሰቦቹ የተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ህጋዊ መሆኑን አረጋግጦ የግንባታ ፍቃድ ብቻ ሰጥቷል። ከዚህ ባለፈ ወረዳው ቦታውን እንዳልሰጠና የሚያውቀው ነገር እንደሌለ መግልጹን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ወጣቶቹ ጠንከር ብለው በህግ እንጠይቃለን የሚል ሃሳብ ሲያነሱ፤ ወጣቶቹን ለማባበል የመንገድ ፕላን የወጣበት 15 ካሬ ሜትር የማይሞላ ቦታ ላይ ተጫወቱ። ኳስ ሜዳው ያበቃለት ጉዳይ ስለሆነ ይሄንን አትጠይቁ የሚል ምላሽ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሰጡ፤ ወጣቶቹም ህጋዊ የስፖርት ማዘውተሪያችንን በህገወጥ መንገድ አሳልፎ ከተሰጠ በኋላ ሌላ ምትክ ቦታ እሰጣለሁ ማለት የተነሳውን ጥያቄ ለማዘናጋት በመሆኑ፤ በህጋዊ መንገድ ኳስ ሜዳችንን እናስመልሳለን በሚል ምትክ ቦታ የሚለውን ወጣቶች እንዳልተቀበሉ ተናግረዋል።
የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ በአሻጥር ለግለሰቦች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ተሰጥቷል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ፤ ባገኙት መረጃ ግለሰቦቹ የተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ ከ1997 ዓ.ም በፊት ቤት ሰርተው ይኖሩበትና በአሁን ጊዜም እየተዳደሩበት እንደሚገኝ የሚገልጽ መሆኑን ጠቁመው፤ እርሳቸው እስከሚያውቁት ድረስ ኳስ ሜዳው ላይ ከ25 ዓመት በላይ ምንም አይነት ቤት የሌለበትና ግለሰቦቹ ከቀናቶች በፊት እስከሚያጥሩት ድረስ ወጣቶች ጠዋት ማታ ኳስ የሚጫወቱበት ቦታ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ግለሰቦቹ የያዙት መረጃ ከዕውነት የራቀ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በማጣራት ኳስ ሜዳውን ለአካባቢው ማህበረስብ እንዲያስመልስላቸው አቤቱታቸውን ገልጸው፤ በአካባቢው የሚገኙ ክፍት ቦታዎች በህገወጥ መንገድ እየታጠረ ወጣቶች መዝናኛ አጥተዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ መውጫ መግቢያ አጥቷል ሲሉ በአካባቢው የተስፋፋውን የመሬት ወረራ ያስረዳሉ።
ኳስ ሜዳው የኔ ነው የሚሉ ግለሰቦች
በሌላ በኩል ወጣቶች ኳስ የሚጫወቱበት ቦታ በወረዳው አርሶ አደር የሆኑት የአስር አለቃ በለጠ ፈለቀ ቀደምት የግል ይዞታቸው መሆኑን የአስር አለቃ በለጠ ልጅና ህጋዊ ወኪል ወይዘሮ ጸዳለማሪያም በለጠ ይናገራሉ።
አስር አለቃ በለጠ እድሜያቸው በመግፋቱ ላይ ታች ብለው ጉዳያቸውን ማስጨረስ ባለመቻላቸው ወይዘሮ ጸዳለማሪያም ጉዳያቸውን ይዘው እየተከራከሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ቦታው አባታቸው አስር አለቃ በለጠ ከወታድርና በጡረታ ሲገለሉ ቀበሌው ለመተዳደሪያነት በ1971 ዓ.ም በእርሻ መሬትነት እንደሰጣቸው ገልጸው፤ ከተጠቀሰው ጊዜ አንስቶ አባታቸው እያረሱ ሲጠቀሙበት እንደነበርና መሬቱ ወደ ከተማ ልማት እስኪገባ ድረስ በገበሬ ማህበር የእርሻ ግብር ሲከፍሉበት እንደነበር ይናገራሉ። በገበሬ ማህበር የእርሻ ግብር ከ1971 እስከ 1982 ዓ.ም ሲከፍሉበት የነበረውን መረጃም አቅርበዋል።
እርሳቸውም በ1985 ዓ.ም መንግስት ለኢንዱስትሪ ልማት 14 ቀርጥ ሄክታሩን መሬት ሲወስድ፤ መንግስት ለልማት በወሰደው ቦታ ብቻ አባታቸው 51 ሺብር ካሳ ሲያገኙ፤ ነገር ግን ወጣቶች ኳስ የሚጫወቱበትን ቦታ ለአውድማና ለገለባ መከመሪያ አጥረው ሲጠቀሙበት ስለነበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት የታጠረ ቦታ ስለማይለካ በቦታው ግምት ባያገኙበትም እንደሚያለሙበት ተነግሯቸው 1ሺ 600 ካሬ ሜትር የሚሆን ቦታ ግምት ሳያገኙበት በእጃቸው መቅረቱን ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ጸዳለማሪያም መንግስት በ1985 ዓ.ም ለልማት ከወሰደው ውጭ ቀሪውን 1ሺ 600 ካሬ ሜትር የሚጠጋውን ቦታ ከ1971 ዓ.ም አንስቶ አባታቸው እያስተዳደሩት እንደሚገኝ ጠቁመው፤ አባታቸው በወቅቱ ቦታውን አልሙበት ሲባሉ ለማልመት አቅም በማጣታቸው አጥሩን ሌባ ወስዶት ክፍት ሆኖ ሲቆይ ወጣቶች ቦታው ላይ ኳስ መጫወት እንደጀመሩ ይናገራሉ።
እርሳቸውም ቦታው ላይ ኳስ የሚጫወቱት የአካባቢው ወጣቶቹ በመሆናቸው እስኪያለሙበት ድረስ ይጫወቱበት ማለታቸውን ገልጸው፤ ወጣቶች ኳስ እየተጫወቱበት እያለ በመሃል ግለሰቦች ቦታውን መጥተው እንዳጠሩት ያስረዳሉ።
ግለሰቦቹ ቦታውን ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም በአሳቻ ሰዓት መጥተው ሲያጥሩ ደንብ አስከባሪና ፖሊስ ይዘው ለማስቆም ቦታው ላይ ሲሄዱ፤ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ በወቅቱ ቦታው ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን እንኳን በደንብ ሳያደምጡ ሰዎቹ ህጋዊ ናቸው። ማንም ሰው እንዳያግዳቸው። ያልሙበት ብለው ደንቦችንና ፖሊሶችን እንደመለሷቸው ይናገራሉ።
የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰዎቹ ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አላቸው አንቺ ምን አለሽ ብለው እንደጠየቋቸው ጠቁመው፤ የአባታቸው የእርሻ መሬት መሆኑን የሰው ምስክርና ከ1971 ዓ.ም አንስቶ የመሬት ግብር የከፈሉበትን ደረሰኝ ሲያቀርቡላቸው፤ ቦታውን ከአሁን በኋላ አታገኙትም። ባይሆን ግምት ሊሰጣችሁ ይችላል የሚል መልስ ከወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
እርሳቸውም ህጋዊነቱ እስኪጣራ ድረስ ቦታው ላይ ግለሰቦቹ የሚያካሂዱት ግንባታ ይታገድልኝ ብለው ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቅሬታቸውን በጽሁፍ ቢያቀርቡም፤ ያቀረቡትን ቅሬታ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊቀበላቸው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ቅሬታቸውን በጽሁፍ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ማቅረባቸውን ያስረዳሉ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊም ያቀረቡትን ህጋዊ ማስረጃ አይተው ህጋዊነቱ እስኪጣራ ድረስ ቦታው ላይ ግለሰቦቹ የሚያካሂዱት ግንባታ ይታገድላቸው ብለው ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ መሰረት ግለሰቦቹ ሲያካሂዱት የነበረው ግንባታ መታገዱን ጠቁመው፤ ነገር ግን ግለሰቦቹ በአንድ ቀን በቆርቆሮ ቤት እንደሰሩበትና የመሬቱ ባለቤት እያለ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ በሚል ሀሰተኛ መረጃ አዘጋጅቶ ለግለሰቦቹ ቦታውን በህገወጥ መንገድ ስለሰጠ መንግስት አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ ቦታውን እንዲያስመልስላቸውና በህገወጦች ላይም ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ በቃና እንደገለጹት፤ ወጣቶች ኳስ ሜዳችን ተወስዶብናል በሚል እርሳቸው ዘንድ ቀርበው ቅሬታ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ወጣቶቹ ዝምብለው በደፈናው ስንጫወትበት የኖርንበት ቦታ ነው ከማለት ውጭ ኳስ ሜዳው የእነርሱ ስለመሆኑ ተጨባጭ መረጃ የላቸውም። እንዲሁም ኳስ ሜዳው የኳስ ሜዳ መስፈርትን የማያሟላ ከመሆኑ ባሻገር የቦታው ፕላን ለአካባቢው ማህበረሰብ ለስፖርት ማዘውተሪያነትም ሆነ ለአረንገዴ ልማት የተፈቀደ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን ወጣቶች ኳስ የሚጫወቱበት ሜዳ እንዳያጡ ከክፍለ ከተማው ጋር ተነጋግረው ሌላ ተለዋጭ የመጫወቻ ሜዳ የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመው፤ ወጣቶች የተሰጠውን መልስ ካላመኑበት ክፍለ ከተማ ሄደው የቦታውን ፕላን ማየት ይችላሉ። አይ ካሉም በህግ መጠየቅ ይችላሉ ብለዋል።
ወጣቶቹ ግለሰቦቹ የሚያደርጉት ግንባታ ይታገድልን ብለው ሲጠይቁ ግለሰቦቹ ህጋዊ በመሆናቸው ግንባታቸውን ለማገድ እንዳልቻሉ አቶ መልካሙ አስረድተው፤ ቦታው ለልማት ተነሺዎች ከመሰጠቱ በፊት የአካባቢው ማህበረሰብ ቦታው ወደ መሬት ባንክ ሲገባ የት ሂዶ ነው? ዛሬ ላይ ቦታው ላይ ልማት ሲከናወን ቅሬታ የሚያነሱት ሲሉ ሞግተዋል።
በአጠቃላይ ግለሰቦቹ ከክፍለ ከተማው መሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይዘው ሲመጡ ወረዳው ህጋዊነቱን አረጋግጦ የግንባታ ፈቃድ መስጠቱን አቶ መልካሙ ጠቁመው፤ ለግለሰቦቹ ቦታውን በምን አግባብ እንደተሰጠ ክፍለ ከተማውን ጠይቃችሁ መረዳት ትችላላችሁ የሚል ምላሽ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሰጥተዋል።
የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ለልማት ተነሺዎች ከመስጠት ሌላ ምትክ ቦታ መስጠት አይቻልም ነበር ወይ? እንዲሁም እራሳቸው የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው ቦታውን ለግለሰቦቹ የሸጡት የሚል ሐሜት አለ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ መልካሙ እንደገለጹት፤ ወረዳው ቦታ የመስጠትም ሆነ የመንሳት ስልጣን እንደሌለው ጠቁመው፤ ነገር ግን የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ተወስዶባቸዋል ብለው ክፍለ ከተማውን ጠይቀው ሌላ ምትክ ቦታ እንዲያገኙ እንሰራለን። ሌላው የወረዳው አስተዳዳሪ በስልጣኑ ቦታውን ሰጥቷል ለሚለው ሐሜት፤ ህጋዊ ሆኖ ለሚመጣ አካል ህጉ በሚፈቅደው እናስተናግዳለን። ነገር ግን ከህግ ውጭ የተሰራ ስራ ካለ ማንኛውም ሰው መረጃ ይዞ በህግ መጠየቅ እንደሚችል አስረድተዋል።
የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ምን አለ?
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቁምላቸው ዳምጤ እንደገለጹት፤ ወረዳ 11 ቀጠና አምስት በተለምዶ ኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወጣቶች ኳስ ሲጫወቱበት የነበረውን ቦታ ሶስት ግለሰቦች ህጋዊ ካርታ ተሰርቶላቸው ግንባታ እያከናወኑበት ነው። እነዚህ ሰዎች ምን ህጋዊ ማረጋገጫ አላቸው ተብሎ ከጋዜጠኞች ጥቆማ ከደረሰን ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዳጣሩ ይናገራሉ።
መንግስት አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ2006 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ መሰረት፤ ወረዳዎች በዚህ መመሪያ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች በእርሻ በሚተዳደሩበት ቦታ ላይ ከ1997 ዓ.ም በፊት ቤት ሰርተውበትና በአሁኑ ጊዜ እየተዳደሩበት መሆኑን የአርሶ አደር ኮሚቴዎችን አዋቅረው ካረጋገጡ በኋላ ለክፍለ ከተማው ለአርሶ አደሮቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰራላቸው ፋይል አደራጅተው እንደሚልኩ ያስረዳሉ።
ክፍለ ከተማው ደግሞ ወረዳው በላከው ፋይል መሰረት አርሶ አደሮቹ ቦታው ላይ ቤት ሰርተው እየኖሩበት ነው ወይ? ግለሰቦቹ በትክክል አርሶ አደሮች ናቸው ወይ? ምን ህጋዊ መረጃ አላቸው? የቦታው ፕላን ምን ያሳያል? የሚሉ ቴክኒካል ጉዳዮችን ካጣራ በኋላ ለግለሰቦቹ የይዞታ ማረጋገጫ እንደሚሰጥ አቶ ቁምላቸው ያስረዳሉ።
ነገር ግን ጥቆማው ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ ወጣቶች በኳስ ሜዳነት ከ15 ዓመታት በላይ ሲገለገሉበት የነበረውን ቦታ በምን አግባብ ለግለሰቦቹ እንደተሰጠ ባደረጉት ማጣራት፤ በ18/2006 መመሪያ መሰረት ወረዳው በተሰጠው ስልጣን ግለሰቦቹ ከ1997 ዓ.ም በፊት ቤት ሰርተውበትና በአሁኑ ጊዜ እየተዳደሩበት መሆኑን የአርሶ አደር ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ካረጋገጠ በኋላ፤ ለክፍለ ከተማው አርሶ አደሮቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰራላቸው ፋይል አደራጅቶ በላከው መሰረት ክፍለ ከተማው የይዞታ ማረጋገጫ ሰርቶ መስጠቱን ገልጸዋል።
እርሳቸውም ፋይል አገላብጠው እንዳጣሩት የቦታው ፕላን በከፊል ለአረንጓዴ ልማት የሚል መሆኑን ጠቁመው፤ ወረዳው አርሶ አደር ናቸው በሚል ፋይል አደራጅቶ ቢልክም ክፍለ ከተማው ግለሰቦቹ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆች ናቸው የሚለውን በትክክል ሳያጣራ፤ ከ1997 ዓ.ም በፊት ቤት ሰርተውበትና በአሁኑ ጊዜ እየተዳደሩበት ስለመሆኑ ሳያጣራ፤ ቦታው የሶስተኛ ወገን የይገባኝል ጥያቄ የሌለበት መሆኑን ሳያረጋግጥ፤ በተጨማሪም ግለሰቦቹ የውሃ፣ የስልክና የመብራት አገልግሎት ሲያገኙበት የነበሩ መረጃዎችን ሳይመረምርና የቦታው ፕላን ምን እንደሆነ ሳያረጋግጥ ለግለሰቦቹ የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠቱን ማረጋገጣቸውንና ይህም ትልቅ ስህተት መሆኑን አስረድተዋል።
ክፍለ ከተማው የሰራው ስህተት እንዳለ ሆኖ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ግለሰቦቹ ከክፍለ ከተማው መሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይዘው ሲመጡ ወረዳው ህጋዊነቱን አረጋግጦ የግንባታ ፈቃድ ብቻ ነው የሰጠው ብሎ የተሰጠው ምላሽ ከእውነት የራቀ መሆኑን አቶ ቁምላቸው ገልጸዋል።
እርሳቸውም ወረዳው የአርሶ አደር ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ግለሰቦቹ የመሬት ግብር የከፈሉበት መረጃ ያላቸው፣ ከ1997 ዓ.ም በፊት ቤት ሰርተውበትና በአሁኑ ጊዜ እየተዳደሩበት የሚገኙ፣ ቦታው የሶስተኛ ወገን የይገባኝል ጥያቄ የሌለበትና ግለሰቦቹ የውሃ፣ የስልክና የመብራት አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ የሚገልጽ ፋይል አዘጋጅቶ በማቅረቡ ለግለሰቦቹ ክፍለ ከተማው የይዞታ ማረጋገጫ መስጠቱን ያስረዳሉ።
አቶ ቁምላቸው ወረዳው ለሶስት ግለሰቦች የአርሶ አደር ይዞታቸው ነው በሚል ፋይል አደራጅቶ ካርታ እንዲወጣላቸው ለክፍለ ከተማው ሲልክ፤ የክፍለ ከተማው የቴክኒክና የህግ ባለሙያዎች ነባራዊ ሁኔታውን ቦታው ድረስ ወርደው አይተው አረጋግጠው ካርታውን መስጠት ሲገባቸው፤ ተገቢውን የቴክኒክ ምርመራ ሳያደርጉ በተለመደ መንገድ ካርታ ሰርቶ መስጠቱ ስህተት ቢሆንም፤ ወረዳው ከ15 ዓመት በላይ ወጣቶች በኳስ ሜዳነት ሲገለገሉበት የነበረና በከፊል ፕላኑ ላይ ለአረንጓዴ ቦታ የሚልን ቦታ የአርሶ አደር ይዞታ ነው በሚል ፋይል አደራጅቶ ለክፍለ ከተማው መላኩ ዋናው ስህተት መሆኑን ያስረዳሉ።
ኃላፊው የአካባቢው ማህበረሰብ ለስፖርት ማዘውተሪያነትና ለአረንጓዴ ልማት ከ15 ዓመት በላይ ስንጠቀምበት የነበረ ቦታ ያላአግባብ በግለሰቦች ተወስዶብናል ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ በመሆኑ፤ የግለሰቦቹ ካርታዎች ታግደው ምርመራ እንዲደረግባቸው የማድረግ ስራ ተሰርቷል። ምንም አይነት የግንባታ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ለግለሰቦቹ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ግለሰቦቹ ሲያካሂዱት የነበረውን ግንባታ አግደናል ብለዋል።
አቶ ቁምላቸው አሰራሩንና ህጉን ባልጠበቀ መንገድ ለአርሶ አደሮቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰርቶ የተሰጠ በመሆኑና ከዚህ በፊት ወጣቶች ለረጅም ጊዜ በኳስ ሜዳነት ሲገለገሉበት እንደነበር መረጃዎች ስለሚያሳዩ ካርታውን የማምከን ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ካርታውን ለግለሰቦች ሰርቶ የሰጠው አስተባባሪው አካል ከዚህ ቀደም በሰራው ጥፋት በህግ ጥላ ስር የሚገኝ ስለሆነ ቀድሞ ከተጠየቀበት ወንጀሎች በተጨማሪ በዚህኛው ጉዳይም በህግ እንዲጠየቅ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።
እርሳቸውም ሆኑ የክፍለ ከተማው የመሬት የይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊው ለግለሰቦቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ሲሰጥ ክፍለ ከተማው ላይ በስራ እንዳልነበሩ አቶ ቁምላቸው ጠቁመው፤ ወደ ክፍለ ከተማው በኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ ግን ከህግ አግባብ ውጭ የሰሩ 11 ባለሙያዎችን በህግ እንዲጠየቁ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ተገቢውን ማጣራት ሳያደርጉ ለግለሰቦቹ የይዞታ ማረጋገጫውን የሰጡ ባለሙያዎች አሁን ላይ በስራ መደባቸው ላይ ካሉ እንዲሁ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በአጠቃላይ ማህበረሰቡ በስፖርት ማዘውተሪያነትና ለአረንጓዴ ልማት ለረጅም ጊዜ ስንገለገልበት ነበር የሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ቢሆንም ቦታው በግለሰብ ሲተዳደር የነበረ ነው ለማለት ለጊዜው ማረጋገጥ ባይቻልም ቦታው የኔነው የሚል ጥያቄ አንድ ግለሰብ እንዲሁ ማንሳታቸውን አቶ ቁምላቸው ጠቁመው፤ አሁን ላይ ለግለሰቦች የተሰጠውን ካርታ የማገድና ግለሰቦቹ ሲያከናውኑት የነበረውን ግንባታ የማቆም ስራ የተሰራ ሲሆን፤ በቀጣይ ደግሞ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ቦታውን ወደ ነበረበት ይዞታ የመመለስ ስራ ይሰራል ብለዋል።
እንዲሁም አንድ ቦታ ማስተር ፕላኑ ላይ የአረንጓዴ ልማት ወይም ለኳስ ሜዳነት የሚውል ነው ብሎ ከተቀመጠ ክፍለ ከተማው ለሌላ ልማት መቀየርም ሆነ መስጠት በህግ የሚያስጠይቅ ስለሆነ የትኛውም ግለሰብ ህጉን ባልጠበቀ መንገድ ግንባታ ቢያከናውንም በህግ አግባብ ግንባታውን ከማፍረስ ወደ ኋላ እንደማይሉ አቶ ቁምላቸው ገልጸው፤ አሰራሩ በሚፈቅደው መልኩ ተጣርቶ ተገቢው ውሳኔ ይሰጣል። ካርታውንም የማምከን ስራ ይሰራል። መጠየቅ ያለበት አካልም እንዲጠየቅ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
ሶሎሞን በየነ