ለረጅም ዘመን ሳይደፈር በኖረው ወንዛችን ዓባይ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው ሲጀመር ከመሪዎቻችን የተሰጠን አገርንና ህዝብን የማሳደግ ምኞት አገር ወዳድ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሰነቀው ተስፋ ከፍተኛ ተነሳሽነትን ፈጥሮ ከሃምሳ ብር ጀምሮ በቢሊዮን የሚቆጠር የቦንድ ግዢ በማከናወን የግድቡን ግንባታ እኛው ኢትዮጵያውያን እንድናከናውን አደራ ተቀበልን፡፡
ከከተማ እስከ ገጠር የሚናፈቀው የኤሌክትሪክ ኃይል በግድቡ ግንባታ ዕውን ሲሆን በማገዶ እንጨት ሸክም የእናቶች ድካም ሊወገድ፤ ኃይል የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎችና መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ የሁሉም ምኞት ነበር፡፡ ከኅብረተሰቡ የተሰጠው ምላሽ እጅግ አስደሳች ስለነበር የቦንድ ግዢው ተጠናክሮ ከመቀጠሉም በላይ በ8100 አጭር መልዕክት ጭምር ድጋፉ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡
በወቅቱ አንድ የሃይማኖት አባት እንደገለጹት በመቃብር ካሉ ሙታን እና በማኅጸን ካሉ ህጻናት ውጪ ሁሉም ኢትዮጰያውያን ያለምንም የብሄር፣ የጾታ፣ የሃይማኖትና የገቢ ልዩነት ድጋፋቸውን ችረዋል። ጫማ በመጥረግና ከሰል በመቸርቸር ከሚተዳደሩ ዜጎች አንስቶ ጡረተኞችና ቢሊየነሮች በአንድ ልብ በገንዘብም፣ በሀሳብም በሞራልም ለግድባቸው ያበረከቱት ድጋፍ የሚያኮራና በታሪካችን ልዩ ቦታን የሚይዝ ነው።
ይሁን እንጂ የግድቡ ግንባታ በተያዘለት የመጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ እንዳይከናወን የተለያዩ እንቅፋቶች ሲፈጠሩና ህብረተሰቡ ይህንን ሲረዳ ኃላፊነት በጎደላቸው አመራሮች የተፈጸመው አሳዛኝ ሁኔታ ህብረተሰቡ ለግንባታው የሚዘረጋው እጅ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ይሁንና በዘራፊዎች እንጂ በዓባይ ላይ ተስፋ ያልቆረጠው ህዝባችን ለግድቡ ሲሰጥ የነበረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ግን ፈጽሞ ሊነጥፍ አልቻለም። አብዛኛው ህዝብ የግድቡ ግንባታ ውጤታማ እስኪሆን ድረስ በትዕግሥት መጠበቁን መርጦ እነሆ ዛሬ ላይ የግድቡ ግንባታ ውጤት ላይ ደርሶ የውሃ ሙሌቱ ሲጀመርና የትዕግሥቱን ፍሬ ለማየት ሲበቃ ይህ ድል ያነቃቃቸው ዜጎቻችን ከአምስት እጥፍ በላይ ጨምረው የቦንድ ግዢ ለመፈጸም እንደቆረጡ በግልጽ አይተናል፡፡ በ8100 የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያም የዜጎች ድጋፍ በበለጠ መጋጋል ስለመቀጠሉ ከማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የተሰማው ዜና አረጋግጧል።
ሰሞኑን እንኳ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሲሉ በልደት ወጪያቸው ቦንድ የገዙ ታዳጊዎች መኖራቸውን እየሰማን ነው፡፡ በርግጥማ “አባቴ ሁልጊዜ ስለ አባይ ይነግረኝ ነበረ፤ እናም የልደቴን ወጪ ቀንሼ ለዓባይ ግድብ ቦንድ መግዛቴ ያስደስተኛል›› የሚሉት ህጻናት በግድቡ ግንባታ አሻራቸውን በማኖራቸው የታሪክ ድርሻ አላቸው፡፡
ለግድቡ ግንባታ ከውጭና ከአገር ውስጥ ኢትዮጵያውያን በሰኔ ወር ብቻ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ፤ በ2012ዓ.ም ብቻ 745ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ በ8100A ደንበኞች አንድ ሚሊየን 290ሺ ደንበኞች የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ ባላት ቁርጠኛነትና በወሰደችው እርምጃ በተገኘው ድል በታየው የግድቡ የውሃ ሙሌት በመነሳሳት በ22 ቀናት ብቻ 290ሺ ኢትዮጵያውያን የ8100A ደንበኞች በመሆን ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆኑ የማይፈጽሙት አኩሪ ገድል እንደሌለና ከግድቡ ላይ ለአፍታም ቢሆን ዓይናቸውን እንደማይነቅሉ ነውና ይህን መሰል ራስንም ወገንንም የሚያኮራ ተግባር እስከግድቡ ፍጻሜ ተሟሙቆ ሊቀጥል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012