
ምንም ዓይነት ህግ በሌለበት ሀገር ከሚገዛ ዴሞክራት መሪ ህግ ባለበት ሀገር የሚመራ አምባገነን መሪ ቢኖር እንደሚመረጥ የህግ ፍልስፍናዎች ያስቀምጣሉ። ይህ ሀሳብ የሚንጸባረቀው አምባገነንነትን ለማሞገስ ሳይሆን የህግን አስፈላጊነት ለማጉላት ነው። እውነት ነው ህግ በሌለበት ሰላም ወጥቶ ሰላም መግባት፣ ሰርቶ መኖር፣ ነግዶ ማትረፍ፣ መማር፣ መዳር ወዘተ ፈጽሞ አይታሰቡም። የህግ የበላይነት በሌለበት ሀገር ስርኣት አልበኝነት ይሰፍንና ወንጀል ይስፋፋል፣ ሀገር ይታመስና በህይወት መኖር ፈተና ውስጥ ይወድቃል።
ብዙዎቻችን በበቂ መጠን እንዲሰፍን የምንፈልገውና የምንናፍቀው ዴሞክራሲም ያለ የህግ የበላይነት ህልውናው ፈጽሞ ሊረጋገጥ አይችልም። በዴሞክራሲ መስፈንና በህገ-ወጥነት መካከል ሰፊ ልዩነት አለና። ለዚህም ነው ከዴሞክራሲ ምሰሶዎች ውስጥ የህግ የበላይነት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው። የእያንዳንዳችን መብት እንዲከበር እኛም የሌላውን መብት ማክበር ይኖርብናል። ይህ ዓይነቱ መልካም አካሄድ ሲዛባም ማረሚያ የሚሆነው የህግ የበላይነትን ማስከበሩ ይሆናል።
ሀገራችን ለረጅም ዘመናት በህግ ስትተዳደር የቆየች ሀገር ናት። ህዝቧም በህግ የበላይነት የሚያምንና በጭቆና ውስጥም እየኖረ እንኳ ህግንና የህግ የበላይነትን በማክበር ጨዋነቱን ያስመሰከረ ኩሩ ህዝብ ነው። ህግ የመጣስ አዝማሚያና ተግባር ሲገጥመው እንኳን ለማስቆም የሚጠቀመው ቃል “በህግ አምላክ” የሚል ነው። ይህም ለህግና የህግ የበላይነት የሚሰጠውን ከፍተኛ ዋጋ የሚያሳይ ነው።
የህግ የበላይነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጠውም የህግ አስከባሪ አካላትና አስፈጻሚዎች በቅድሚያ ራሳቸው ለህግ የበላይነት ተገዥ መሆናቸውን ሲያስመሰክሩና ህግንና ህግን ብቻ መሰረት አድረገው ሲሰሩ ነው። ይህ መሆኑ ቀርቶ ህግ በመንግስት ሹመኞች የሚጣስ ከሆነ፣ ሙስና የፍርድን ሚዛን ካጣመመና አድልዎ ከነገሰ ሊሰፍን የሚችለው ጭቆና ይሆናል።
ለሁላችንም ግልጽ እንደሆነው በሀገሪቱ ሰፍኖ የቆየውን ጭቆናና ኢፍትሃዊነት በመቃወም በወጣቱ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ህዝቦች ባደረጉት ትግል በሀገራችን የለውጥ አየር መንፈስ ከጀመረ 10 ወራትን አስቆጥሯል። በዚህም የህዝቦች ስቃይ እንዲቆም፣ ዜጎች በሀገራቸው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ የሚሆንበት ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲያከትም መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጎ ጅምር ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በአስተሳሰባቸው ምክንያት ተገፍተው የነበሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው ገብተው በሰላም እንዲንቀሳቀሱ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸውና ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ምክንያት ወደ ማረሚያ የወረዱ ዜጎች እንዲለቀቁና የታገዱ ሚዲያዎችና ብሎገሮች ያለምንም ተጽዕኖ እንዲንቀሳቀሱ የተደረገበት ሁኔታ ከላይ ያነሳነውን ሀሳብ ትክክለኝነት የሚያረጋግጡ ሁነኛ ማስረጃዎች ናቸው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከሰሞኑ በዳቮስ ባደረጉት ንግግር በእስር ቤትም ሆነ በውጪ ሀገር የቀረ አንድም ጋዜጠኛና ተፎካካሪ ፓርቲ የለም በማለት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን ለማስፈን የተሄደውን ረጅም ጉዞ ለማሳየት ሞክረዋል።
አሁን ከህዝቡም ሆነ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቀው ዋነኛ ቁም ነገር ብርግድ ብሎ በተከፈተው የዴሞክራሲ ሜዳ ላይ ለመጫወት የጫዋታ ህጎቹን አክብሮ መንቀሳቀስ ብቻ ነው። ከጨዋታ ህጎቹ ቀዳሚው ደግሞ የህግ የበላይነት ማክበርና ማስከበር ይሆናል። ይህን እንዳላደርግ ይህ አካል ከለከለኝ የሚለው ምክንያት ለጊዜው ተዘግቷል። በሽግግር ወቅት ላይ እንደመሆኑ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ተነጋግሮ መፍትሄ ለመስጠት በሩ ክፍት መሆኑን መንግስት ደጋግሞ አስታውቋል። ህጋዊና ህገ-ወጥ መስመርን እያጣቀሱ ለመሄድ ጊዜውም ሀገሪቱም ምቹ አለመሆናቸውን መገንዘብ ብልህነት ነው።
ለዴሞክራሲው ማበብ ያለውን ምቹ ሁኔታ ለማስፋትም መንግስት በህግ የበላይነት ላይ የማይታለፍ ቀይ መስመር አስምሮ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑም እየታየ ነው። ይህንንም ደግሞ ጉምቱ ጉምቱ ባለስልጣኖቹን በህግ ፊት በማቅረብና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላም ያደፈረሱ የተለያዩ ኃይሎችን በማስታገስ እያረጋገጠ ይገኛል። በዚህም ሰርቆ መደበቅና ግፍ ሰርቶ መንደላቀቅ እንደማይቻል በተግባር አስመስክሯል ማለት ይቻላል።
በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩና በዜጎች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በችሎት ፊት ቀርበው ጉዳያቸው በመታየት ላይ ሲሆን በተረጋጋ ሁኔታ መረጃዎችን በማሰባሰብም ጥፋት የፈጸሙ ተጨማሪ ግለሰቦች በቀጣይ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉም ይጠበቃል።
ይህ ተግባር በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ መሰረት እንዲይዝ ትልቅ አቅም ከመሆኑም በላይ ሰላማችንን በማረጋገጥ ዕድገታችንን እንድናፋጥን ምቹ ጥርጊያ እንደሚሆነን ይታመናል። ስለሆነም የሰላማችንና የእድገታችን አልፋና ኦሜጋ የሆነውን የህግን የበላይነት ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011