አባይ ስበት አለው፤ የአገሪቱን ሕዝቦች በገመድ አስተሳስሯል፤ በፍቅር ልባቸውን አሸንፏል፤ ተስፋቸውን በእሱ ላይ እንዲጥሉ አድርጓል፣ የቤታቸው ኩራዝ እንዲለወጥ፣ የሥራቸው ዓይነት እንዲቀየር፣ አመራረታ ቸው በመስኖ በዓመት ሁለት ሦስቴ እንዲሆን፣ የገቢ አቅማቸው እንዲጎለብት በእሱ ምኞታቸውን ያሳደሩ ዜጎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ተስፋቸው መፍካት ጀምሯል የጉባ ተራሮች ጎዝጉዘው የአባይን ውኃ በሥራቸው አስተኝተዋል። ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ተመራማሪ የየድርሻቸውን በማበርከታቸው ኮርተዋል ከጉሊት እስከ ሱቅ በደረቴ፣ ከሊስትሮ እስከ ቆራሊዮ ድረስ ደስታቸውን ይገልጹ ይዘዋልሐሳባቸውንም ለአዲስ ዘመን ተንፍሰዋል።
በጉሊት ሥራ የሚተዳደሩት የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ አዳነች አባተ እንደተናገሩት፤ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌትን ዜና ስሰማ እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ ሲሉ ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም የኮሮና ቫይረስ ባይኖር ኖሮ ከመሰሎቼ ጋር ወደ አስፋልት በመውጣት እልል ብዬ መንግሥትን እያመሰገንኩ የኢትዮ ጵያን ሕዝብ እንኳን ደስ አለን ማለት እፈለግ ነበር ይላሉ።
ግድቡ ሲጀመር በጉሊት ገበያ ከማገኛት ገቢ በቤታችን ከሚገኘው ሕፃን ልጅ ጀምሮ ለግድቡ የበኩላችንን ስናደርግ ቆይተናል ብለውናል። ነገር ግን ግድቡ በአምስት ዓመት ያልቃል ተብሎ በተግባር በጊዜው ባለማለቁ ተከፍቼ ነበር ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ ቀኑ ቢረዝምም በአዲሱ መንግሥት በጥቂት ዓመታት ውስጥ የግድቡን መሞላት በመስማቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በክረምት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት አደርጋለሁ ብሎ የገባውን ቃል በመፈጸሙ መደሰታቸውን ወይዘሮ አዳነች አመላክተው፤ ይህን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል ሲፈፅም ሳይ በመንግሥት ላይ ተስፋ እንዲኖረኝ አድርጎኛል ሲሉ ይናገራሉ።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜ እስኪደርስ ድረስ እንደበፊቱ ትንሹም፤ ትልቁም ሁሉም የአቅሙን በማድረግ፤ መተባበር ይኖርበታል ሲሉ ወይዘሮ አዳነች የትብብር መንፈስን ይዘራሉ ሌላዋ በጉሊት ሥራ የሚተዳደሩት የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ የአብ ስራ አያልነህ ግድቡ ለኔም፣ ለልጄም፣ ለቤተሰቦቼም፣ ለሀገርም የተሻለ ነገር ይዞ እንደሚመጣ
ተስፋ አደርግ ስለነበር ትናንት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሙሌቱን ዜና ስሰማ ደስታዬ ወደር አልነበረውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በፓርላማ የተናገረውን ቃሉን ጠብቆ ግድቡ መሞላቱ በመንግሥት ላይ የሚኖረኝን አመኔታ ከፍ እንዲል አድርጎታል ሲሉ ወይዘሮ የአብ ስራ አመላክተዋል፤ ወደ ፊትም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ትን ሹም ትልቁም ተባብሮ የግድቡን ፈጻሜ ከዳር ማድረስ ይኖርበታል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው እና ጫማ በማፅዳት ሥራ የተሰማራው ወጣት አሰላ አበበ የመጀመሪያው ዙር ሙሌት መጠናቀቁን ስሰማ ደስታዬን በቃላት ለመግለጽ ከባድ ነበር ሲል መደሰቱን ተናግሯል፤ አሁንም የጀመርነውን ተባብረን የአቅማችንን በማድረግ እንጨርሰዋለን የሚለው ወጣት አሰላ አበበ፤ መገናኛ ብዙኃንም በርትተው በመስራት ማህበረሰቡን ማንቀሳቀስ ይገባቸዋል ሲል ጠቁሟል።
አንዳንድ አካላት ስለግድቡ የተለያየ ነገር ሲያወሩ ይሰማል፤ እነዚህን አካላት መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ሊያስቆማቸው ይገባልም፡፡ ምክንያቱም እነኝህ አካላት የሰውን የመተባበር መንፈስ ስለሚሸረሽሩት የመተባበር መንፈስ ከተሸረሸረ ግድቡን በታቀደው ጊዜ አጠናቆ ለተፈለገለት አላማ ማዋል አይቻልም የሚለው ወጣት አሰላ አበበ ወጣቱም እነዚህን አካላት በንቃት መጠበቅ አለበት ሲል አሳስቧል።
የአባይ ግድብ የእኛ የኢትዮጵያኖች ተስፋ ስለሆነ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለን መጨረስ ይገባናል ነው ያለው ወጣቱ።
ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ጫማ በማፅዳት ሥራ የተሰማሩት አቶ ሃይሉ ዘለቀ በራሳቸው እና በትምህርት ቤት ደግሞ በልጆቻቸው ስም ጭምር ጫማ ጠርገው ከሚያገኙት ገቢ ከዕለት ጉርሳቸው በመቀነስ ለአባይ ግድብ ያቅማቸውን ማበርከታቸውን ይገልጻሉ ግድቡም ከዚህ ደረጃ ደርሶ በማየቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ ሀገሬ ስታድግ ሀገሬ ስትለማ ጥሩ ደረጃ ላይ ስትደርስ በጣም ደስታ ይሰማኛል የሚሉት አቶ ሃይሉ ዘለቀ የህዳሴው ግድብ ውሃ ሞልቶ ከማየት በላይ ለእኔ ደስታ ሊፈጥርልኝ የሚችል ነገር የለም ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ሀገራችን የጀመረችውን ግድብ ለመጨረስ ልክ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጣጥሮ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አቶ ሃይሉ ተናግረዋል። አንዳንድ የኢትዮጵያን ማደግ የማይፈልጉ ኃይሎች ስላሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሀገሩን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
አሸብር ሃይሉ