ክረምቱ ጨክኗል ጠዋት ማታ የሚጥለው ዶፍ ለመንገደኞች፣ በተለይ ትራንስፖርት ለሚጠቀሙ ወገኖች አዳጋች መሆን ጀምሯል፤ ወቅታዊው የኮቪድ 19 ስጋት ደግሞ እንደቀድሞው አማራጭ የሚሰጥ አልሆነም።
በርካቶች ማልደው በሚቆሙበት ጎዳና ብቅ የሚል ታክሲና አውቶቡስን እየናፈቁ ያንጋጥጣሉ፤ መጨረሻቸውን ለማግኘት በሚያታክቱ ረጃጅም ሰልፎች የተደረደሩ ተሳፋሪዎች ያለመታከት ሰዓታትን ቆመው ይገፋሉ በሰልፉ መሀል ነፍሰጡሮች፣ ህፃናት የያዙ እናቶች ፣ አቅመ ደካማዎችና ሌሎችም ይታያሉ።
ተራ ጠብቀው የሚደርሱ አንዳንድ ታክሲዎች እልፍ ሆነው ከተደረደሩት ጥቂት ያህሉን ብቻ ዘግነው እብስ ይላሉ፤ ቀጣዩን የሚጠብቁ ሌሎች ደግሞ በቀደሟቸው ተሳፋሪዎች ዕድለኝነት እየጎመጁ የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ ይናፍቃሉ፡፡ ታክሲዎች እንደታሰበው በጊዜው አይደርሱም ይሄኔ በዳመናው መክበድ የሰጉ ሰልፈኞቹ ተስፋ ይቆር ጣሉ፣ ከፊት ያለው ሳይሸኝ ከኋላ በኩል ያለው ሰልፍ በእጥፍ ይጨምራል።
አቶ አሰፋ ቢተው የግል ድርጅት ተቀጣሪ ናቸው። በርካቶች ቤት በዋሉበት በዚህ ዘመን እሳቸው ይህን ማድረግ አልተቻላቸውም፤ የሥራ ባህሪያቸው ከቤት የሚያውል አይደለም። ይህ እንኳን ባይሆን እጃቸውን ናፍቀው ለሚያድሩ ልጆቻቸው የዕለት ዳቦ ሊያጎርሱ ግድ ይላል።
በሚኖሩበት የቱሉዲምቱ አካባቢ በርካታ አውቶቡስና ታክሲዎች አገልግሎት ይሰጣሉ። እሳቸው አብዛኛውን ጊዜ
በሚጠቀሙበት የታክሲ ትራንስፖርትም በረጃጅም ሰልፎች ላይ መቆምን ልምድ አድርገዋል። አሰፋ ይህ እንዳይሆን ማልደው ይወጣሉ እንዳሰቡት ሆኖ ግን ከችግሩ ማምለጥ አይቻላቸውም፤ ጠዋት ማታ በረጃጅም ሰልፎች ታድመው ከቤት ወደ ሥራ፣ ከሥራም ወደ ቤት ለመመላለሰ ተገደ ዋል።
የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ በኋላ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። በርካታ ሠራተኞችም ቤት ሆነው ሥራዎቻቸውን እንዲከውኑ ተወስኗል። እንዲህ መደረጉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ታሰቦ ነበር።
ዛሬም ግን ‹‹ቤትህ ተቀመጥ›› የተባለ ነዋሪ ኑሮ አስገድዶት ወደውጪ በመውጣቱ ትራንስፖርቱና የሰው ቁጥር ሊመጣጠን አልቻለም፤ እንዲህ መሆኑ ደግሞ እንደ አቶ አሰፋ በመሰሉ ለፍቶ አዳሪዎች ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ላቅ እንዲል አድርጎታል።
እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ተጠቃሚዎች እንደሚሉት የትራንስፖርት ዋጋውና የተጠቃሚዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። መፍትሔ የለሹ የከተማችን የትራንስፖርት ጉዳይም እልባት ካልተበጀለት የችግሩ ስፋት በአሳሳቢነቱ ይቀጥላል።
ከጀሞ አየር ጤና፣ ወደ ጦር ኃይሎች በየቀኑ የሚመላለሱት ወይዘሮ ወርቅነሽ በርካቶች የሚያነሱትን ችግር ይጋራሉ። ከጡረታ በኋላ በጥቂት ክፍያ ተቀጥረው የሚሠሩበት የግል ድርጅት ከኮቪድ መከሰት በኋላ ተዘግቶ ቢቆይም በቅርቡ ሥራ ጀምሯል፤ ይህ መሆኑ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሠራተኞች በትራንስፖርት እጦት እንዲንገላቱ አስገድዷቸዋል።
ወይዘሮዋ ቀደም ሲል ለታክሲ በቀን ይከፍሉት የነበረው ሰባት ብር አሁን ላይ በእጥፍ ጨምሮ ሃያ ስምንት ብር እያስወጣቸው መሆኑን ይናገራሉ፤ በሰዓቱ ለመድረስና ተመልሶ ለመምጣትም የሚገጥማቸው ውጣውረድ በእጅጉ እየፈተናቸው ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሐመድ ከኮቪድ መከሰት በኋላ ህብረተሰቡ ቤቱ እንዲቀመጥ መወሰኑን ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በርካታው የከተማ ነዋሪ ያለማቋረጥ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ መሆኑም በትራንስፖርት አቅርቦቱና አጠቃቀሙ ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እንደ ኮማንደር አህመድ ገለጻ ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ የታክሲዎች የመጫን አቅም በሃምሳ ፐርሰንት መቀነሱ ለረጃጅም ሰልፎች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚኖረው የመንገድ መዘጋጋትም የታክሲዎች ምልልስ እንዲቀንስና በተጠቃሚው ላይ ተጽዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል
ቀደም ሲል ህብረተሰቡ ቤት የመዋል ልምድን አዳብሮ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ መስሪያቤቶች ሥራ ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ በርካታ ሠራተኞች ትራንስፖርት ፈላጊዎች ሆነዋል፡፡ ይህ እውነታም ቀደም ሲል በነበረው ልክ እንቅስቃሴው እንዳይ ቀጥልና የሚስተዋለው ችግር እንዲባባስ አስገድዷል።
በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ ቦታዎች ወደ መሀል ከተማ የሚገቡ ሰዎች መበራከታቸውን የገለጹት ኮማንደሩ እነሱን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከወትሮው በባሰ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች መሆናቸው ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ ያለውን የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ቁጥር መፍትሔ ለመስጠት ጥናት በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ኮማንደር አህመድ፣ በቅርበት በመቀመጥ ካለው ስጋት ይልቅ ተጠጋግቶ በመቆም የሚመጣው ችግር እንደሚብስ በመታመኑ በጉዳዩ ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በሃምሳ ፐርሰንት መሆኑ ቀርቶ በወንበር ልክ ይጫን የሚለው ሃሳብ የህብረተሰቡ ጥያቄ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው ጉዳዩ አሳማኝ በመሆኑ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያበት መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜ ተጨማሪ አስር የከተማ አውቶቡሶች ርክክብ መካሄዱን የተናገሩት ኮማንደር አህመድ ይህ መሆኑ የትራንስፖርቱን ችግር ለማቃለል በቂ እንደማይሆንና ቀደምሲል የተጀመረውን የሦስት ሺህ አውቶቡሶች ግዢን የማጠናቀቅ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በአሁኑ ጊዜ በተወሰኑ አካባቢዎች ለአውቶቡስ መጓጓዣነት ብቻ የተለዩ መንገዶችን በመጠቀም የሚስተ ዋለውን መጨናነቅ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
ችግሩ በዘላቂነት እስኪፈታ ሕብረተሰቡ ሊተባበር ይገባል ያሉት ኮማንደር አህመድ በተለይ አሽከርካሪዎች በእነዚህ መንገዶች ላይ መኪና ባለማቆም፣ የተበላሹትን ፈጥኖ በማንሳትና በተመሳሳይ ሰዓት ባለመውጣት የመንገዱን መጨናነቅ ሊቀንሱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
መልካምስራ አፈወርቅ