ድሬዳዋ፡- በከተማዋ እየተስተዋለ የሚገኘው የህብረተሰቡ መዘናጋት የኮሮ ቫይረስ ስርጭት እንዳያስፋፋው ስጋት እያሳደረ መሆኑን የከተማው መስተዳድር ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር የጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ አስተባባሪ ወይዘሮ ስንታየሁ ደባሱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ፤ በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ መምጣቱ የሚያመላክት በመሆኑ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑን ያሳያል ነገር ግን አሁን ላይ እየታየ ያለው የህብረተሰቡ መዘናጋት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳያስፋፋው ስጋት እየሆነ ይገኛል ፡:
ምርምራ በሚካሄድበት ወቅት ብዙ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው እንዲሁ በአስከሬን ምርመራ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች መገኘታቸው ቫይረሱ እየተሰራጨ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ መጀመሪያ አካባቢ ያሳይ የነበረውን የመከላከልና የጥንቃቄ ስራ በመተው የመላመድ ሁኔታዎች እየታዩ መሆናቸውን አመልክተ ዋል።
ምርምራውን ለማስፋት ወደ ጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች ከሚመጡ ታማሚዎች እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ፤ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ካላቸው ሰዎች ናሙና በመውሰድ የምርመራ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስተባባሪዋ ይናገራሉ።
በዚህ ወቅት ያለው የመመርመሪያ ጣቢያ አንድ ሲሆን በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በላብራቶሪ ባለሙያዎች አማካይነት ናሙና የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመው፤ ለላብራቶሪ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ናሙና የሚወስድበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን አመልክተዋል።
አክለውም፤ ድሬዳዋ በጁቡቲ መንገደኞች በኩል የስጋት ቀጠና በመሆኗ፤ ከሌሎች ከተሞች በተለየ
መልኩ የተለያዩ የመከላከል ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን በድንበሮች ፣ የትራንስፖርት መግቢያና መውጫዎች አካባቢዎች ከሹፌሮች ናሙና እየተወሰደ የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ፤ የጅቡቲ ተመላሽ ዜጎች ደወሌ ለይቶ ማቆያና ህክምና ማዕከል ምቹ ባለመሆኑ ወደ ድሬዳዋ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል። እንዲዘዋወሩ የተደረጉትም ቫይረሱ የተገኘባቸው፤ ገና ከጁቡቲ የገቡ ምርመራ የተደረገላቸውንና ያልተደ ረገላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል። በዚህም በአንድ ቀን ከተወሰደ 80 ናሙና ውስጥ 78 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 75 ሰዎች ከደወሌ ለይቶ ማቆያ የመጡ ሲሆን ሌሎች 3 ሰዎች ከማህበረሰቡ መገኘታቸው እጅግ አስደንጋጭ ክስተት መሆኑን አስታውሰዋል።
ምርመራውን ለማስፋት ተጨማሪ መመርመሪያ ማሽን የተጠየቀ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁኑ ግን ባለው አቅምና የሰው ሃይል ተጠቅሞ ለመመርመር ጥረት በማድረግ ናሙና የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚደረገው የቤት ለቤት ልየታ ስራ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በኤሌክት ሮኒክ ሥርዓት በመታገዝ የቤት ለቤት የሙቀት ልየታ የሚሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ዳታ አያያዝ ሥር ዓቱን በማዘመን በታብሌት የተደገፈ መረጃን በመሰብሰብ የሪፖርት አሰጣጥ ሥርዓቱ የተናበበና የተሳለጠ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
ህብረተሰቡም ጥንቃቄ ሳይለየው ኮሮናን በመከላከል አጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን የሚጠቁሙት አስተባባሪዋ፤ ከዚህ ጎን ለጎን ሌሎች የህክምና የክትባት አገልግሎቶች በአግባቡ እየተሰጡ ይገኛሉ በመሆኑ ህብረተሰቡም ያለምንም ስጋት ጤናውን መከታተል እንዳለበት አመልክተዋል።
በድሬዳዋ ከዚህ ሌላ ተጨማሪ እንደ ወባ ያሉ ስጋቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የመከላከል ስራ አብሮነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ህብረተሰቡም ሆነ ባለድርሻ አካላት የጤና ስራውን ማገዝ እንደ ሚጠበቅባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
ወርቅነሽ ደምሰው