በአጋጣሚ ሳይሆን አገልግሎት ለማግኘት በማሰብ በመዲናችን አንጋፋ ወደ ሆኑ ሆስፒታሎቻችን አቀናሁ።ወደ ሀኪም ቤቶቻችን ከመሄዴ በፊት ሃሳብ የሆነብኝና ያስጨነቀኝ የኮቪድ 19 ጉዳይ ነበር።ሆኖም ሆስፒታል አይደለ እንዴ?እዛማ የተሻለ ጥንቃቄ ይኖራል፤ መፍራትም ሆነ መጠራጠር የለብኝም ብዬ ተነሳሁ። እንዳውም ሊያሳስበኝ የሚገባው አገልግሎት ላይ የሚኖረው እንግልት ነው እያልኩ ራሴን በስነልቦና ለማዘጋጀት ሞከርኩ። ያው ግን ፈራ ተባ ማለቱ እንዳለ ነው። ህክምናውን ማግኘት የግድ ነውና በማለዳ ተነስቼ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል አቀናሁ።በቦታው እንደደረስኩ የጥበቃ ሰራተኛው ፈጠን ብሎ “ኮሮና ይዞህ ነው?” ሲል ጠየቀኝ።ድንግጥ ብዬ አይ!አልኩና የመጣሁበትን ጉዳይ ማስረዳት ቀጠልኩ። “በ5ኛ በር ከቶታል ቀጥሎ ያለው ህንፃ ሂድ” ብሎ ሸኘኝ። የኮቪድ ጉዳይ እንዲህ ቀላል ነው እንዴ? ኮሮና ይዞኝ ነው እየተባለ ሆስፒታል ይኬዳል እንዴ? በውስጤ የማነሳው የምጥለው ጥያቄ ነበር። በግርምት ይሄንኑ እያወጣሁና እያወረድኩ ወደ ተባለው ቦታ ደረስኩ። ካፍቴሪያው በሰዎች ደምቋል፤ተሟሙቋል። ከሚያካፋው ዝናብ ለመሸሽ መጠለያና ማረፊያ ወንበር አጥቶ የሚሰቃየው ሰው ደግሞ በርካታ ነው። ይህን ስመለከት የኮሮና ስጋቴ ሁሉ ጠፋ።
ሆስፒታሉ ግቢ ቁጭ ብዬ የሚንገላታውን ታማሚና አስታማሚ ስመለከት ሁሉም ሰው በቅንነት ለምን አያገለግልም? ከትንሽ እስከ ትልቁ የተሰጠውን የስራ ድርሻ ለምን አይወጣም? ይሄ ቢሆን እኮ የሚንገላታ ፣ የሚማረር ሰው አይኖርም ነበር እያልኩ ለራሴው እነግረው ጀመር። ለሀገራችን ምንም እያበረከትን እንዳልሆነ የገባኝም ያኔ ነው። መተዛዘን የለም፣ መረዳዳት ያንሰናል። ሆስፒታል ሲሆን ደግሞ እነዚህ በትክክል በተግባር መታየት ያለባቸው ናቸው። እንኳን አገልግሎት መስጠት ለሚገባቸው ሌላውም በአጋጣሚ በእዛ ስፍራ ቢገኝ የተቸገረን መርዳት አለበት ።
ታካሚው መጥቶ ጊዜውን ካባከነ በኋላ አንዱ ይመጣና በዚህ አይደለም ይለዋል።ምንም ሳይል ወደ ተባለበት ለመሄድ የሰዎችን እርዳታ ይፈልግና ያቀናል።አፍታ ሳይቆይ ተመልሶ ይመጣና በዚህ ነው ተብያለው ይላል።በድጋሚ ሌላው መጥቶ በሌላ በኩል ሂድ ብሎ ይሸኘዋል። ሌላው ይመጣና የፈለገውን አገልግሎት ሲናገር በዚህ አይደለም ይባላል።በዚህ ተብየ ነበር ሲለው የራስህ ጉዳይ ብሎ ጥሎት ይሄዳል።ሁሉም ነገር በዚህና በዚያ ።
ከሀገራችን የገጠር አካባቢ በሪፈራል የመጡ ሰዎችን በዚህ መልክ ማየት እራሱ ሌላ በሽታ መሸመት ሳይሆን ቀረ ብላችሁ ነው ።የሰው ትርምስ የአዲስ አመት ዋዜማ የገበያ ስፍራ አስመስሎታል። የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በወጉ ያደረጉት ጥቂቶች ናቸው። አካላዊ መራራቅ የነጠላ ዜማ ያህል እየሰማን የምናልፈው ነው በእዛ ስፍራ። የመታከሚያ ካርድ አውጪዎቹ እስከ አራት ሰአት ድረስ አይጨርሱም።ሀኪሞቹ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ሰአት ደርሷል ብለው ይወጣሉ።ታካሚው ለከሰአት ይቀጠራል።ማንኛውም ሰው በየት በኩል መሄድ እንዳለበት የአቅጣጫም ሆነ የሰው ጠቋሚ የለም።እኔም በዚሁ መልኩ እስከ ሦስት ሰአት ካርድ ሳልቆርጥ ከቆየሁ በኋላ ለመስተናገድ የሚያስችለኝን ቅድመ ሁኔታ አላሟላህም ተብዬ ተመለስኩ።
በማግስቱ ደግሞ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል አቀናሁ። የጥበቃ ሰራተኛው “ የቀጠሮና የሪፈራል ወረቀት ያልያዘ ሰው መግባት አይችልም” እያለ ይናገራል።ከሁለት አንዱን የያዘ ይገባል።በር ላይ ያለው ግርግርና ክርክር ደግሞ “ኮሮና ታሪክ ሆኗል” ብለን እንድናስብ ያስገድዳል።በተለይ ደግሞ አብዛኛው ተገልጋይ ከገጠር የመጣ በመሆኑ በሆነ ባልሆነው ጭቅጭቅ እንዲበዛ አድርጎታል።ይህን ሂደት አልፈን ወደ ውስጥ ስንገባ ዩኒሴፍ ተብሎ የተፃፈባት አንዲት ድንኳን ተቀበለችን።የህሙማን ማረፊያ ቦታ መሆኗ ነው። ተገልጋዩ ከድንኳኑ ተርፎ በየደረጃውና እንደነገሩ በተሰሩ ወንበሮች ተነባብሮ ተቀምጧል።ማረፊያ ያጣው ደግሞ ጀርባ ለጀርባ ተሰጣጥቶ ቆሟል።ያለሁበትን ቦታ ለማመን ከብዶኛል። ይሄ ኮሮና የለም እንዴ? በየመገናኛ ብዙሀን የማየውና የምሰማው ሁሉ አጠራጠረኝ። ምክንያቱም ያለሁት ሆስፒታል ነዋ! ትልቁ ጥንቃቄ የሚደረግበት፣ መካሪና አስተማሪ ባለሙያዎች ያሉበት…።
እኔም የዚሁ ትዕይንት አካል ነኝ። በአጋጣሚ አንድ ለየት ያለ ዩኒፎርም የለበሰ ሰው ብቅ ካለ በተገልጋዮች ይከበባል።በተገልጋይ ተከባ እያነጋገረች ያለችን አንዲት የሆስፒታሉን ሰራተኛ ያየ አንድ ባልደረባዋ “ለምን በአስለቃሽ ጭስ አትበትኛቸውም” ብሎ ሲቀልድ ጆሮዬ ደረሰ ። ግን እዛ መድረስ ሳያስፈልጋት ከከበቧት ሰዎች ሹልክ ብላ ወጣች።ይህ ሁሉ የሚሆነው ተገልጋዩ በጊዜው ባለመስተናገዱ ነው።
በቀጠሮ መጥቶ የሚያናግረው ያጣ፣ የካርድና የመድሃኒት ቤት ጠፍቶት ግቢው የሚያስሰው፣ መጸዳጃ ቤትና የላብራቶሪ ክፍሉን የሚጠቁመው ያጣው እንግልት ብዙ ነው። በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ መጥተው ያለመፍትሄ ቀናትን የቆጠሩ የደከሙ ድምጾችን መስማት አዲስ አይደለም።የታመመን ለማዳን በቅድሚያ ሀኪም ቤቶቻችን ከያዛቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ቢድኑ።
ለህሙማን ማረፊያ በቂ ወንበር የሌለው ሆስፒታል፣ታማሚን በሰዓቱ አገልግሎት የማይሰጥ ሆስፒታል፣ተላላፊ በሽታ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ እንዲደረግ የማያደርግ ሆስፒታል… ራሱ ታማሚ ነው ለማለት ተገድጃለሁ።የያዘውን ህመም ለመዳን ሄዶ ሌላ በሽታ የሚሸምትባቸው ሆስፒታሎቻችን ይታከሙ። ህሙማንን የሚያንገላቱት ሀኪም ቤቶቻችን ቶሎ ካልታከሙ ህሙማኑን ማዳን አይችሉም።አሁንም እላለሁ ቀድመው ይታከሙ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም
በሞገስ ፀጋዬ