የኮቪድ 19 ወደ አገራችን መግባትና መስፋፋት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ጊዜና ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የህዝባችን መዘናጋት እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ ሁኔታው እጅግ ያሳሰባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ይሄን መልዕክት አስተላልፈው ነበር። “የኮሮና ወዳጅ ማን እንደሆነ ደርሰንበታል፣ መዘናጋት ይባላል፣ ኮሮና ከመዘናጋት ጋር ከተባበረ አንችለውም፣ ሁለቱን መነጣጠል አለብን። ሰሞኑን በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት ኮሮናና መዘናጋት ግንባር ፈጥረዋል ማለት ነው። ኮሮና ማንን እንደሚጠላና እንደሚፈራ አውቀነዋል፤ ኮሮና ጥንቃቄ የሚባለውን ፈጽሞ አይወደውም፣ ጥንቃቄ ባለበት ቦታም አይደርስም፤ ወይም የከፋ ጉዳት አያደርስም። በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሁለት፣ ሦስት፣ ዐሥር፣ ሠላሳ፣ ሰባ፣ እያለ መቶ መግባቱ የሚያሳየው ኮሮና እያመረረ፣ እኛ እየተዘናጋን መምጣታችንን ነው፡፡ ኮሮና ተዘናግቶ እኛ ብናመርር ጥሩ ነበር ፤ ወይ ተባብረን እንነሣበት፤ አሊያም ኮሮናና መዘናጋት ተባብረው ይደቁሱን፤ ምርጫው ከሁለቱ አንዱ ነው፡፡ ሁኔታው ሳይመርብን፣ እኛ እናምርበት። ኮሮና ሳያሸንፈን እናሸንፈው። ኮሮናን የማሸነፊያ ቀን ዛሬ፣ የማሸነፊያ ሰዓቱ አሁን፣ የሚያሸንፈውም ሰው እርስዎ ነዎት፡፡”
ይህ መልዕክት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ላይ እጅግ አስፈላጊና አንገብጋቢ ሆኖ ተገኝቷል። ቫይረሱ በአገራችን መገኘቱ ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 4/2012 ዓ/ም ወዲህ የኮሮና ወረርሽኝ እያደገ እያደገ መጥቶ እስከትናትናው ዕለት ድረስ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ለ357 ሺህ 58 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 993 ደርሷል። 5 ሺህ 645 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገግሙ፤ አሁን ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 89 ነው ፥ ከእነዚህም ውስጥ 65 ሰዎች በጽኑ የታመሙ መሆናቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የ197 ሰዎች ህይወት አልፎ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውም ይታወሳል።
ከዚህ አኃዝ በላቀም ባለፈው እሁድ በአንድ ቀን ብቻ ከ700 በላይ ሰው በቫይረሱ መያዙን መሰማቱም እኛ የዘነጋነው ኮሮና እርሱ ሳይዘናጋ ይልቁኑ ከመዘናጋታችን ጋር አብሮ ውስጥ ውስጡን እየገዘገዘን መሆኑን ያሳያል።
ስርጭቱ ይህ በሆነበት አግባብ በገበያና በትራንስፖርት መያዣዎች አካባቢ ያለው ግፊያና ትርምስ፤ በመዝናኛዎችና ካፍቴሪያዎች የሚታየው ጥግግት፤ የእጅ መታጠብና ማስታጠቡ መቀዛቀዝ ወዘተ ከዕለት ዕለት እየባሰበት መሄዱ ኮሮናን በአገራችን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል። አሁን ላይ ቆም ብለን ካልተነጋገርና የጥንቃቄ እርምጃዎችንም በከፍተኛ ዲስፕሊን ካልፈጸምንም ነገ ሊያስከፍልን የሚችለው ዋጋም እጅጉን ያሳስባል።
የታላቁ ህዳሴ ግድባችንን የመጀመሪያውን ውሃ ሙሌት ተመልክተን በደስታ እንደፈነደቅነው ፍጻሜውን አይተን የበለጠ ሀሴት ለማድረግ፤ ሃሳቦቻችንን ተግብረን ፍሬውን ለመቋደስ፤ ቤተሰብ ለመመስረትም ሆነ የመሰረትነውን ቤተሰብ ለፍሬ ለማብቃት ዋናው ጉዳይ ጤና እንደመሆኑና ኮሮና ደግሞ በአሁኑ ወቅት አንደኛው የጤናና የህልውና ጠላታችን እንደመሆኑ ከመዘናጋታችን ተቆጥበን ይህንን ወረርሽኝ በመከላከሉ ሂደት የድርሻችንን መወጣት ለነገ ይደር የሚባል ተግባር ሊሆን አይገባም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012