አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የወጪ ንግድ እቅድ አፈፃፀም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ135 ነጥብ 82 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መቀነሱንና ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ትናንት የሚኒስቴሩን የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ፤ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 1 ነጥብ 96 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው 1 ነጥብ 21 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 1 ነጥብ 35 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር 135 ነጥብ 82 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል በዋናነት የግብርና ምርት በሚፈለገው መጠንና ጥራት ያለመመረት፣ ህገወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን በሚፈለገው ደረጃ መግታት ያለመቻል፣ በዓለም የገበያ ዋጋ መውረድ ምክንያት የታጣውን ገቢ በመጠን ለማካካስ የሚያስችል ስራ በበቂ ቅንጅት ማከናወን ያለመቻሉ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ዝቅ ባለ ዋጋ ምርትን መሸጥና በአንዳንድ አካባቢዎች በነበሩ የፀጥታ ችግሮች በገዢዎች ዘንድ ስጋት በመፍጠሩ የምርት ግዢው መቀዛቀዙን አስረድተው፤ የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎች በማፈላለግና ትስስር በመፍጠር ረገድ የተሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ፣ ጠንካራና የተቀናጀ የኮንትራት አስተዳደር ስራ ባለመሰራቱ የወጭ ንግዱ አፈፀፃም ከሚጠበቀው በታች እንዲሆን ያደረገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የግብዓት አቅርቦት እጥረት ያለባቸው መሆኑ፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም መዘግየት፣ የአስተዳደር፣ የቴክኒክና የግብይት ውስንነት ችግሮች ለዘርፉ መቀዛቀዝ አሉታዊ ሚና እንደነበራቸውም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
እንደሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የወጪ ንግድ ተዋንያን ኮንትራት በወቅቱና በጥራት ካለመፈፀም ባሻገር ውልን በማፍረሳቸው የአገር የወጪ ንግድ ገፅታን እየጎዳ ይገኛል፡፡ የወጪ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ በጠንካራ የብቃት ማረጋገጫ ያልተደገፈ በመሆኑ ያለበቂ ዝግጅት እውቀትና ልምድ ወደ ዘርፉ በመግባት አሰራሩ እንዲዛባ አድርጎታል፡፡ የወጪ ንግድ ልማትና ግብይት ስትራቴጂ ባለመኖሩም የወጪ ምርቶችን በዓይነት፣ በብዛት፣ በተወዳዳሪ ዋጋና በተከታታይነት ካለማቅረብ አኳያም ውስንነት ይስተዋላል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምስጋናው አበራ በበኩላቸው የወጭ ንግዱ አፈፃፀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ ማበርከት የሚገባው አስተዋፅኦ እንዳይኖር ያደረገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ አኳያም የዘርፉ እድገት አራት በመቶ ብቻ መሆኑን አቶ ምስጋናው ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ውስጥ እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርና ምርቶች 75 በመቶ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ደግሞ 13 በመቶ ድርሻ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
«የአገራችን ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ እያለ ማመንጨት ከሚገባው አኳያ በጣም ዝቅ ያለ ስለሆነ ይህንን ለማሳደግ በከፍተኛ ርብርብ መስራት ይጠይቃል» ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ስራው በተለያየ አካላት የሚሰራ ከመሆኑ ጋር በሚፈለገው ልክ በቅንጅት መስራቱ ላይ የሁሉም ርብርብ እንደሚያሻው ያሳሰቡት ሃላፊው፤ የዓለም አቀፍ ገበያን ሰብሮ ለመግባት ከተፈለገም ከኋላ ቀር ግብይትና አሰራር መላቀቅ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመፍታት የወጪ ንግዱን ለማሳደግ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባና ለአፈፃፀሙ እያሽቆለቆለ መምጣት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ከመለየት ባሻገር ራሱ የትክልትና የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም ፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ ፣ ሰም ፣ ማዕድናት፣ የተፈጥሮ ሙጫና እጣን ከእቅዱ ከ50 በመቶ በተታች ካስመዘገቡ የወጭ ምርቶች መከካል ይገኙበታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2011
በማህሌት አብዱል