የታመመውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አክመው ኢትጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት ያስፈነደቀ ብስራት ምክንያት ሆነዋል። የስፖርት አፍቃሪያን አደባባይ አስቀጥቶ ያስጨፈረ ክስተት የረጅም ዘመናት የሀገር ህልም ያሳካ ገጠመኝ ከፊት ሆነው መርተዋል። ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሥራች ሆና ለዓመታት ከራቀችበት መድረክ መልሳ እንድትገናኝ ያደረጉ ታላቅ ሰው።
እግር ኳስ ከፊት ሆነው መርተው ዋንጫ እንዳስገኙት ሁሉ በወጣትነት ዘመናቸው ለክለቦች ተጫውተው ዋንጫ አስገኝተዋል። ከወረዳ ጀምሮ እስከ ታላላቅ ክለቦች በአገር ደረጃ ከታዳጊ እስከ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ድረስ በማሰልጠን አዳዲስ የአጨዋወት ስልትን በማላመድ የሚመሩትን ቡድን ውጤታማ ያደረጉ የአገር ባለውለታ። በሥራቸው ስኬት ተጎናፅፈው ታላቅ አድናቆትን ያተረፉትና የበጎ ሥራዎች አምባሳደር የሆኑት መምህርና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በዛሬ የዝነኞች የዕረፍት ውሎ አምዳችን ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ሥራ ስኬትና የግል ጥረታቸው፣ የዕረፍት ጊዜያቸውን በምንና እንዴት እንደሚያሳልፉ አጫውተውናል።
የስኬት መንገድገና የሦስት ዓመት ታዳጊ ልጅ ሳሉ የተወለዱበትን ምዕራብ ጎጃም አግኒ ጊዮርጊስ የተሰኘው አካባቢ በአክስታቸው አማካኝነት ለቀው ደብረ ማርቆስ ከተማ መኖሪያቸው ሆነ። ንቁና ቀልጣፋ ልጅነታቸውን የተረዱት አክስታቸው ወይዘሮ ውዴ ገሰሰ የተማረና ታላቅ ሰው እንዲሆን በመመኘት ትምህርት ቤት አስገቧቸው። በትምህርት ቤት ቆይታቸው ታላቅ ህልምን አለሙ። ለዚያውም ሁለት ታላላቅ ህልሞችን ማሳካት በብርቱ ፈለጉ። በብዙ ጥረትና ትጋት ሁለቱንም ህልማቸውን ማሳካት የቻሉ ጠንካራ፣ ብርቱና ዕድለኛው ሰው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው።
በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይጫወቱ የነበሩት እነ መንግሥቱ ወርቁና ኢታሎ፣ የሚያደርጉት የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በሬዲዮ በመስማት በእግር ኳሱ ዘርፍ ታላቅ ቦታ ለመድረስ ተመኙ።ሌላኛው ህልማቸው ደግሞ በወቅቱ የታላቅነት መሰረት የሆነውን መምህር መሆንን ነበር። መምህር በመሆን ለተማሪዎቻቸው የቀለም ጥማት መፍትሔ ሆነው ብዙዎችን አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል። ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ሁለተኛ ህልማቸውን የማሳካት ጥረታቸው ፍሬ አፈራና ሙሉ ሥራቸው አድርገውት ጀርመን አገር ለሁለት ጊዜያት በመሄድ በእግር ኳስ ጥበብ ትምህርት ቀስመዋል። ይህን ወደ ተግባር በመለወጥ አገር አቀፋዊና አህጉራዊ እውቅናና ከበሬታ ለመጎናፀፍ አስችሏቸዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ለአህጉራዊና ዓለምአቀፍ ውድድሮች አብቅተውት በርካታ ወጣቶች ከማስመዝገባቸው በፊት የታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ምክትልና ዋና አስልጣኝ በመሆን ለአህጉር አቀፍ ተወዳዳሪ ብሎም ዋንጫ አስገኝተዋል። ክለቦችን ደግሞ መብራት ኃይልን (የአሁኑ ኤሌትሪክ የእግር ኳስ ክለብ)፣ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ሙገር ሲሚንቶንና ኒያላ የተባሉ የእግር ኳስ ክለቦች በማሰልጠን ለትላልቅ ስኬቶች አብቅተዋል።
በብሄራዊ ቡድን አስልጣኝነት ብሄራዊ ቡድኑን ለዓመታት ከራቀ በት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር አገናኝተ ውታል፣ በሴካፋ የዋንጫ ባለቤት አድርገውታል፣ ለቻን ውድድር አብቅተ ውታል፣ ከአፍሪካ ሦስት ምርጥ ቡድኖች አንዱ አድርገውታል። በአጉር አቀፍና ዓለምአቀፍ ውድድሮች ብሄራዊ ቡድ ኑን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።
የአሰልጣኙ የዕረፍት ጊዜ መዝናኛ ቦታዎች ከመገኘት ይልቅ የዕረፍት ጊዜያቸውን ከቤተሰባቸው ጋር ቤት ውስጥ በመጫወትና ጥሩ ቆይታን ማድረግ እንደሚመርጡ ይናገራሉ፤ ስኬታማና ታታሪው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው። ቤት ውስጥ እግር ኳስን ተመለከቱ መፅሐፍትን ማንበብና በቴሌቪዥን የእግር ኳስ ጨዋታን መመልከት የሚያስደስታቸው የዕረፍት ሰዓት ተግባራቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
በአብዛኛው በእረፍት ቀናት በሚዘወተረው እግር ኳስ ጨዋታ ስታዲየም ተገኝቶ መመልከትም ከሌሎች መዝናኛዎች አብልጠው የሚወዱት ልምዳቸው ነው። ለረጅም ዘመናት አብረዋቸው ከዘለቁት ጓደኞቻቸው ጋር ሻይ ቡና እያሉ መጨዋወትና ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ የሚመርጡት ሌላው የዕረፍት ቀንና ጊዜ ተግባራቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ተጫዋች ቁም ነገረኛና በሥራቸው ስኬታማ በመሆናቸው ተወዳጅና ሁሉም ሊቀርባቸው የሚፈልጋቸው ናቸው። ከቀረባቸው ጋር ሁሉ በፍቅር እና በመተሳሰብ ውሎ ማደርንም ያውቁበታል።
በማህበራዊ ተሳትፎም ቢሆን ንቁ ተሳታፊ ናቸው። “በተጠራሁበት ማህበራዊ ጉዳይ ሁሉ ተገኝቼ የሚጠበቅብኝን ማድረግ ያስደስተኛል።” የሚሉት አሰልጣን ሰውነት በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ላይ ለሚሠሩ ማህበራትና ተቋማት በአምባሳደርነት በመሳተፍ ለበጎ ተግባሩ የራሳቸውን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ለደም ባንክ፣ ለስለ እናት የወደቁትን ማንሳት ማህበርና በመሳሳሉ ማህበራት ውስጥ በአምባሳደርነትና በአስተባባሪነት በማገልገል ላይ ይገኛል።
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት መሰረት ሊሆን የሚገባው ከስር ሕፃናትን እግር ኳስ በማሰልጠን መጀመር ነው ብለው እንደሚያምኑ የሚያስረዱት አሰልጣኝ ሰውነት በአሁኑ ሰዓት በግላቸው ታዳጊ ሕፃናት እግር ኳስ በማሰልጠን ለእግር ኳስ እድገቱ ታላቅ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
መልዕክት ለኢትጵያዊያን
“የሰው ልጅ የተገደበ ዕድሜ ያለው ፍጥረት ነው። ይህንን አጭር ጊዜው መልካም በሆነ ሁኔታ ይኖረው ዘንድ እርስ በርሱ በመፈቃቀርና በመደጋገፍ አንደኛው ለሌላው ማሰብና መተሳሰብ ይገባዋል። ሰከን ብለን ወደ ልቦናችን በመመለስ ይችን መልካም ሀገራችንን ሰላሟን በማስጠበቅ ወደበለፀጉት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ የሁላችን ኃላፊነት ነውና በፍቅር እንኑር” በማለት መልዕክታቸውን እነሆ ብለዋል። እኛም ለነበረን ቆይታ አመስግነን በዚሁ አበቃን። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
ተገኝ ብሩ