የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ፎረሙ መሪዎች ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊና ኢንዱስትሪያዊ አጀንዳዎች ላይ በአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ተገናኝተው በጋራ የሚያዩበትና አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት ነው። ኢትዮጵያ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረምን “የአፍሪካን መዋቅራዊ ሽግግር መልክ ማስያዝ” በሚል መሪ ሃሳብ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2012 በአዲስ አበባ አስተናግዳ ነበር፡፡_ በዚህ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ሀገራት እያሳዩት ያለው እድገትና በኢኮኖሚው ዘርፍ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡
ኢትዮጵያም ካለፉት አመታት ጀምሮ በዚህ ኮንፍረንስ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡ ከከባቢ አየር ጋር በተያያዘ በሰራቻቸው ስራዎችና በሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን በምታደርጋቸው ጥረቶች ከአፍሪካ ሀገራት ተመርጣ በፎረሙ እንድትሳተፍ ካደረጓት ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በአርባ ሰምንተኛው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ተሳትፈው ሲመለሱ ፎረሙ ላይ በርካታ የሀገራት መሪዎች፣ ታዋቂ ባለሀብቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በጋራ የሚሰባሰቡበት መሆኑ ከሌሎች ስብሰባዎች የተለየ እንደሚያደርገው ጠቅሰው ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በፎረሙ መሳተፏ ሀገሪቱን ለማስተዋወቅና ባለሀብቶችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚን ከመፍጠር ባሻገር አህጉራዊ አጀንዳዎችን በማንሳት ለአፍሪካ ድምጽ እንድትሆን ዕድል ከፍቷል፡፡
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ “በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በአገራችን እየተካሄደ ያለውን የልማት የዲሞክራሲና አጠቃላይ የአገር ግንባታን ጉዳይ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ራዳር ውስጥ መኖራችንን ማሳወቅ ትልቁ ጉዳይ ነው፡፡ ለሀገራችን ጥራት ያላቸው ባለሀብቶችን መሳብ፤ አፍሪካን ወክሎ በተለያዩ መድረኮች ስለ አፍሪካ መናገርና ማሳወቅ ሌላኛው ተልዕኳችን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ መድረኮችም ጭምር ውጤታማ የሆንበት በተለያዩ መድረኮች ሊገኙ የማይችሉ ኢንቨስተሮችን አግኝቶ በሀገራችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባት ጉዳይ ነው፡፡ ስለሀገራችን ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙና ትክክለኛውን ስዕል እንዲይዙ ማድረግ ነው›› ሲሉ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
‹‹በ47ኛው የፎረሙ ስብሰባ ላይም በኃይል ማመንጫ፣ በቱሪዝምና በሌሎች መስኮች በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ካላቸው ባለሀብቶች ጋር የተደረጉ ውይይቶች ውጤታማ ነበሩ፡፡ በኃይል ማመንጨት ስራ ላይ በርካቶች ለመሳተፍ ዝግጁነታቸውን የገጹበት፣ እስካሁንም ማጥናት የጀመሩ ባወጣናቸው ጨረታዎች መሳተፍ የጀመሩ በርካታ ባለሀብቶች አግኝተናል፡፡ እነዚህ ተበረታተው በሀገራችን መዋለ ነዋያቸውን ማፍሰስ እንዲቀጥሉ የማድረግ ስራ ሰርተናል፤ በዚህ ውጤታማ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው በቱሪዝም ዘርፍ በሆቴል ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን አግኝተን አናግረናል “ብለውም ነበር፡፡
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በነበራቸው ተሳትፎ በተለይ በመሰረተ ልማትና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በተሰናዱ መድረኮች ላይ ተሳትፈው አፍሪካን በመወከል የተሳካ ተሳትፎ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ በመድረኩም የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባት ስራዎችን በመስራት ረገድ የተሳካላቸው እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው 49ኛው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረምም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በእስካሁኑ ቆይታቸውም ከበርካታ አገሮች ከተመረጡ ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች ጋር የግል ኢንቨስትመንት መሳብ የሚቻልባቸው ዕድሎችን ለመለየት የሚያስችል የኢንቨስትመንት ስትራቴጂክ ውይይት አካሂደዋል። ይህ ጠንካራ ውይይት በኢትዮጵያ ያለውን ያልተነካና እምቅ የኢንቨስትመንት ሀብትና የፖሊሲ ቅድሚያ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ያመላከተ እንደነበር የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዱባይ ኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሀመድ አል ሼይባን ጋርም ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅትም የኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ በመስተንግዶና በእርሻ ቢዝነስ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት ያለው መሆኑን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም ላይ ፈጣን ኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ባለፉት አስር ዓመታት በአማካይ ዘጠኝ በመቶ እድገት ማስመዝገቧን በማውሳት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በሀገሪቱ ድህነት መቀነሱንና የትምህርት ተደራሽነት እመርታ ማሳየቱንም አንስተዋል።
በሀገሪቱ ካሉ መልካም አጋጣሚዎችና ስኬቶች ባሻገር ግን በተለይም ለወጣቶች በቂ የስራ እድል ከመፍጠርና እድገቱን ከማስቀጠል አንጻር አሁንም ፈተናዎች መኖራቸውንም አልሸሸጉም።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንትና አብሮ ለመስራት ምቹ መሆኗን ገልጸው፣ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመረኮዘና በሶስት ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰዋል። የመጀመሪያው ምሶሶ ዴሞክራሲውን ማስፋት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ የፖለቲካ እስረኞች መፍታትን ጨምሮ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ለአብነትም መቀመጫቸውን በውጭ አገር ያደረጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውንም አንስተዋል።
ሁለተኛው የፍልስፍናው ማሳኪያ መንገድ ደግሞ ኢኮኖሚውን ማሳደግና ማበልጸግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም በተለይ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል። በተጨማሪም በመንግስት የካቢኔ አወቃቀር ውስጥ ሴቶችን በውሳኔ ሰጭነት በማሳተፍ ለውጡን ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአገሪቱ መከላከያ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ አዲስ የተቋቋመው የሰላም እና የትራንስፖርት ሚኒስትሮችን ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የሃገሪቱ ርዕሰ ብሄር ሴቶች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ክፍት በማድረግ ባለሃብቶች በመንግስት ብቻ ይተዳደሩ በነበሩ ሴክተሮች ላይ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል።
ሶስተኛው ምሰሶ ቀጣናዊ ውህደትን ማምጣት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ውህደቱ ለልማትና እድገት ብቻ ሳይሆን ሰላምን ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ውህደቱ ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ለቅቀው ዶክተር አብይ አህመድ ከተተኩ በኋላ ባለፉት 10 ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ በተከነወነው ለውጥ ላይ ትኩረቱን ባደረገው ንግግራቸው የተደረጉ ለውጦችን በዝርዝር አቅርበዋል። ኢኮኖሚውን ክፍት ማድረግ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ የህዝብ አጀንዳ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠትና የሚዲያ ነፃነትን ማረጋገጥ መቻሉን ዘርዝረዋል።
በሀገሪቱ ለታየው ለውጥም መሪው ድርጅት ኢህአዴግ በርካታ ማሻሻያዎችን ማድረጉ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች በመለየት የህዝቡን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ ማሻያዎች ተደርገዋል፤ ይህም የህዝቡን ይሁንታ ለማግኘት አስችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ራዕይ ሰንቃ በለውጥ ላይ እንደምትገኝ በመጥቀስ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ትልቅ ትኩረት እንደተሰጣቸውም አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
የትናየት ፈሩ