እንጦጦ ቁስቋም አካባቢ ተወልደው፣ አድገውና ተምረው በርካቶች ለቁምነገር በቅተዋል፤ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ኑሯቸውን ያደረጉትም በርካቶች ናቸው:: እነዚህ የእንጦጦ ልጆች ግን በአንድም በሌላ መልኩ ቤተሰቦቻቸውን መርዳታቸው፤ ስለ አገራቸውም ማሰባቸው አልቀረም:: ወደ አገራቸው ሲመጡም ከቤተሰብ ባለፈ ወዳጅ ዘመድ መጠየቅና መርዳታቸው አልቀረም:: ይሁን እንጂ ይህ ተግባራቸው ከቤተሰብ ባለፈ አካባቢያቸውን፣ ተወልደው ያደጉበትን ሰፈር፤ እንደ ልጁ ተንከባክቦና ጠብቆ ያሳደጋቸውን ኅብረተሰብ ሕይወት ሊለውጥ አልቻለም::
እናም እነዚህ የእንጦጦ ልጆች በያሉበት ሆነው በተናጠል ከሚሮጡ ሰብሰብ ብለው በአንድ ላይ ላደጉበት አካባቢና ላሳደጋቸው ኅብረተሰብ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ያስባሉ:: ሀሳባቸውን በተግባር ለመቀየርም በሰነድ ያሰፍራሉ፤ በሰነድ ያሰፈሩትን ሀሳብም ወደ ተግባር ለመቀየር ይወስኑና እንደ እህት ወንድም ከሚቆጥሯቸው አገር ውስጥ ካሉ የሰፈራቸው ልጆች ጋር ተቀናጅተው ለመስራት ይወስናሉ:: እናም በሀሳብ የተጠነሰሰው የትብብር ሥራ ጉዳይ «የእንጦጦ ቁስቋም በጎ አድራጎት ማህበር» በሚል ስያሜ እውን ሆነ::
በዚህ መልኩ እውቅናና ፍቃድ አግኝቶ የተመሰረተው ይህ ማህበር የአካባቢውንም ሆነ የኅብረተሰቡን ችግር ከመፍታት አንጻር የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መስራት መሠረታዊ ዓላማው ነበር:: በተለይም ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከትምህርት እና ጤና ድጋፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ቀዳሚ ትኩረቶቹ ነበር:: ይሄን ዓላማውን ለማሳካት በእንቅስቃሴ ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ ግን እንደ አገርም እንደ ከተማም ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችን ይዞ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እያዩ ዝም ማለትን አልፈለጉም:: እናም በውጭ ያሉትም የአገር ውስጦቹም ተነጋግረው የሥራ ጅማሮአቸውን ከ150ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ130 ቤተሰቦች(አባወራዎች) የምግብ ፍጆታ ድጋፍ በማድረግ አንድ አሉ::
ወይዘሮ ጉዴሴ ጎቴ፣ የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ ከሆኑ እናቶች መካከል አንዷ ናቸው:: ወይዘሮዋ፣ አንድ እግራቸው በአደጋ በመቆረጡ ምክንያት በክራንች የሚንቀሳቀሱ በዕድሜ ገፋ ያሉ እናት ናቸው:: መኖር የግድ ነውናም ጥጥ እየፈተሉ ኑሮን የሚገፉ እናት ናቸው:: በዚህ ሁኔታ ደግሞ የዕድሜ መግፋት ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተዳምሮ ሕይወትን ፈታኝ አድርጎባቸዋል:: በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም፤ የከበደውን ኑሯቸውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የበለጠ እንዲከብድ እርሳቸውም ኑሮ እንዲታክታቸው አደረገ:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከኑሮ ጋር ግብ ግብ ገጥመው እንዳሉ ነበር ማህበሩ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገላቸው:: እርሳቸውም በተሰጣቸው ድጋፍ ደስተኛ ሲሆኑ፤ ድጋፉን ላደረጉላቸው የማህበሩ አባላትም ምስጋናን ከምርቃት ጋር አድርሰዋል::
ይህ ድጋፍ በዚህ የኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ ላሉ እናትና አባቶች፣ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖች እፎይታን የሰጠ ነበር:: የዚህ እውነት አብይ ማሳያ ደግሞ የድጋፉ ተቋዳሽ የሆኑት አቶ አንካላ ዋቃ ናቸው:: አቶ አንካላ፣ ልጅ የሌላቸው ከመሆኑ ባለፈ፣ ዕድሜያቸው የገፋ መሆኑ እንደ ልብ ወጥቶ ሰርቶ መግባት ስላላስቻላቸው ኑሮ ዳገት ሆኖ ሕይወት ፈትናቸዋለች:: ይሄን ድጋፍ ማግኘታቸውም ቢያንስ ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ቀን መግፊያ የሚሆናቸው ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ያለው የሕይወት ጉዟቸው ግን በፈጣሪ ፈቃድ የሚሆን እንጂ በእርሳቸው አቅም የሚገፋ አይሆንም:: እርሳቸውንም ሆነ ሌሎች እንደርሳቸው በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ፈልገው ለደገፉ ወገኖችም ምስጋናም፣ ምርቃትም በማድረስ፤ ችግር ጊዜ አይሰጥምና በርካታ በችግር ውስጥ ያሉ ሌሎች ወገኖችንም ማሰብ ተገቢ እንደሆነ ነው መልዕክት ያስተላለፉት::
ቀለሟ ደሳለኝ፣ ከዕለቱ ተደጋፊዎች መካከል አንዷ ስትሆን፤ ለዓመታት ከቤት ተቀምጣ የኖረችበትን ታሪክ የሚቀይርላትንና በቀላሉ በራሷም ሆነ በሰዎች ጥቂት እገዛ ወጥታ ልትገባ የምትችልበትን የዘመናዊ ዊልቸር ድጋፍ ነው ከማህበሩ የተደረገላት:: ግለሰቧ ስለነበረችበት ሁኔታም ሆነ ስለተደረገላት ድጋፍ እንዲህ ስትል ተናግራለች:: በእግሬ መራመድ ባለመቻሌ እንደሰው መውጣት መግባት አልችልም፤ በዚህም ምን አለበት እንደሰው ቆሜ መሄድ ካልሆነም ወጥቼ የምገባበትን ዕድል ባገኝ እላለሁ:: ዛሬ
ላይ ይሄን ድጋፍ በማግኘቴ ድጋሜ እንደተወለድኩ ያህል ተሰምቶኛል፤ ይሄን ላደረጉልኝ ደግሞ ፈጣሪ ብድራታቸውን ይክፈላቸው፤ ስትል ነበር ሳግ እየተናነቃት በእንባ ታጅባ ስሜቷን የገለጸችው::
የቀድሞው ፖሊስ ሠራዊት አባል የሆኑት የቀለሟ አባት ሻምበል ባሻ ደሳለኝ ስለ ልጃቸውና ስለ ድጋፉ ሲያስረዱም፤ ጡረታ ከወጣሁ 27 ዓመት ሆኖኛል:: ልጄ ደግሞ በ1964 ዓ.ም የተወለደች ቢሆንም፤ ራሷን ችላ መራመድ ስለማትችልም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ፊት አላሳይም ብዬ ደግፌያት ነበር:: አሁን ግን አቅም ስላነሰኝ እሷን መደገፍ ስለደከመኝ ለማን እንደምሰጣት ግራ ገብቶኝ ነበር:: አሁን ግን ተመስገን ተረካቢ አግኝቻለሁ፤ መንግሥትም ካወቀልኝ ብሞትም አይቆጨኝም:: ምክንያቱም እስከዛሬ በሐኪምም በድጋፍም ብዬ ሳግዛት ነበር፤ አሁን ግን ደከመኝ፣ አቃተኝም፤ አሁን ግን እንዲህ የሚያስታውሳት ካገኘሁና መንግሥትም ከተረከበኝ ለእኔ እረፍቴ ነው፤ ተመስገን ብዬ አርፋለሁም፤ ፈጣሪም እንደርሷ ሁሉ ሌሎች እንደዚህ የሚደገፉበት ዕድል እንዲፈጠርላቸውም አገራችንን ሰላም አድርጎ መንግሥትን ያዝልቅልን፤ ሲሉ ነበር የእፎይታ ስሜት ውስጥ ሆነው ሀሳባቸውን የገለጹት::
ወጣት ኤልሳቤጥ ወልደማርያም፣ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል ናት:: እንደ ወጣት ኤልሳቤጥ አባባል፤ ማህበሩ የተመሰረተው በጎ ዓላማ ባላቸው የአካባቢው ተወላጆች ሲሆን፤ እነዚህ የማህበሩ መስራቾችም አብረው ያደጉና በሥራ ምክንያት የተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩና በውጭ አገራትም ያሉ ናቸው:: የማህበሩ መመስረት ዓላማም በአካባቢው ያሉ በተለይም አቅማቸው ደከም ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ፣ የአካባቢው ወጣቶችን በሥራ ለማበርታትና በርካቶች በአመለካከትም በተግባርም እርዳታ የሚፈልጉ ወገኖች ከተረጂነት ስሜት እንዲወጡ ማስቻል ነው::
ማህበሩ ይሄን ዓላማ አድርጎ ቢመሰረትም፤ ዛሬ ላይ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ችግር በጋራ ቆሞ መደጋገፍና መቋቋም እንደሚገባ በማመን በአካባቢው ችግር ላይ ያሉና ሊደገፉ የሚገባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመለየት እየደገፈ ይገኛል:: እነዚህ ቤተሰቦችን ለመደገፍ ሲባልም በማህበሩ አባላትም፣ በኅብረተሰቡ ተሳትፎም ተገቢው አሰሳና ተደጋጋሚ ማጣራት ተደርጎ በችግር ውስጥ መሆናቸውም ችግሩ የጠነከረባቸው መሆኑም ተረጋግጦ የተመለመሉ ቤተሰቦች ናቸው:: ይሄው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም በጤናው፣ በትምህርት እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የአካባቢውን ኅብረተሰብም ሆነ ሌሎች ወገኖችንና ትውልድ ተክተው ያሳደጉ እናትና አባቶችን መርዳትን ማዕከል አድርጎ ይሰራል::
ይህ ሥራም ጊዜያዊ ድጋፍን ሳይሆን ተደጋፊዎች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙበትን አቅም መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው:: ማህበሩ በድርጅትነት ተጠናክሮ ይሄን እንዲያደርግ ብቻ ሳይሆን በዚህ መልኩ ሥራውን እንዲጀምር ምክንያትም አቅምም የሆኑት ደግሞ በውጭ አገራት የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ሲሆኑ፤ እነዚህ እህትና ወንድሞች ደግሞ ማህበሩን ከማሰብ ጀምሮ እቅድና መተዳደሪያውን በማውጣትም ሆነ በገንዘብ በመደገፍ ብዙ የተሳተፉ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ ያሉት ወጣቶች በውጭ ካሉት ጋር ተዳምረው የሚፈጥሩት ጠንካራ ትብብር ለሥራው ስኬታማነት የሚያግዝ ነው::
ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ በጤናም ሆነ በትምህርት ዘርፎች ላይ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ከአካባቢው ኅብረተሰብ ብሎም አስተዳደር ጋር በጋራ ተቀናጅቶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ ይህ ጥምረትና ትብብርም ማህበሩን ለስኬትና ያሰበውን ለማሳካት የሚያስችሉት እንደሚሆን ይታመናል::
የእንጦጦ ቁስቋም የበጎ አድራጎት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ወርቁ በበኩሉ እንደሚለው፤ ማህበሩ በእንጦጦ ቁስቋም አካባቢ ተወላጅ በሆኑ ወንድምና እህቶች በጎ ፍላጎት የተመሰረተ ሲሆን፤ የመመስረቱ መሠረታዊ ዓላማ በእንጦጦ ቁስቋምና አካባቢው ባሉ መንደሮችና ሰፈሮች ላይ እንደ አካባቢው ተወላጆች በአንዳንድ በጎ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ነው:: በዚህ መካከል አንዱ በአካባቢው ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ የሚያስችሉ በተለይም ወጣቶችና ሴቶችን መሠረት ያደረጉ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ከመንግሥት ጋር በመሆን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ተግባራት ማከናወን ነው:: ጤናን መሠረት ያደረገው የሥራ ትኩረታቸው ሌላኛው የማህበሩ ዓላማ ሲሆን፤ በዚህም ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ በሌሎችም የጤና ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመርዳት ዓላማም አለው::
በትምህርት ዙሪያም በተለይ በአካባቢው ያሉ የትምህርት ቁሳቁሶችንና ሌሎችንም አሟልተው መማር ለማይችሉ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የእስክሪብቶ፣ ደብተርና ሌሎችም የትምህርት ቁሳቁሶችን በመግዛት የማገዝ፤ እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት አቅምና ተሰጥዖ ያላቸውን ተማሪዎችንም በክፍያ የተሻለ ትምህርት የሚያገኙበትን ዕድል ማመቻቸትንም ዓላማ ያደረገ ነው:: የወጣቶችን ሥነምግባርና አዕምሮ ቀረጻ ላይ በመስራትም ለራሱም ለወገኑም ሆነ ለአገር ትልቅ ሥራ መስራት የሚችል የተሻለ ወጣት የመፍጠር፤ የአቅም ግንባታ ብሎም ሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በበጎ ተግባር መቅረፍ ላይ አተኩሮ መስራትን ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ ነው::
ይህ ማህበር እውን ለመሆኑ መሠረቱ በውጭ ያሉ የአካባቢው ተወላጆች ሲሆኑ፤ ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ በዚህ ደረጃ ደግፎ ወደ ተግባር እንዲገባ ያደረጉትም እነርሱው ናቸው:: ይሄን የማድረጋቸው መሠረታዊ ምክንያትም ቤተሰብ ጥየቃ ወደ አገር ቤት ሲመጡ በተናጠል ከሚያደርጉት ድጋፍ ይልቅ ሰብሰብ ብሎ በአካባቢው ያሉ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፉ የተሻለ ውጤትም ትርጉምም አለው ብሎ በማሰብ ነው:: እነዚህን ዓላማዎች ይዞ የተቋቋመው ይህ ማህበር ወደሥራ ለመግባት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ እውቅናና ፈቃድ ያገኘውም በቅርቡ እንደመሆኑ ወቅታዊና አገራዊ ችግር ሆኖ ባለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን በማገዝም ነው ሥራውን አንድ ብሎ በዚህ መልኩ የጀመረው::
በዚህ መልኩ ሥራ ሲጀምርም አቅም ለሌላቸውና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 130 ቤተሰቦች (አባወራዎች) 150ሺህ 450 ብር ዋጋ ያላቸው የምግብ ፍጆታዎች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ በድጋፉም ለእያንዳንዳቸው የሃያ ኪሎ ፉርኖ ዱቄት፣ ሦስት ሊትር ዘይት፣ አምስት ፓስታ እና ሦስት ሳሙናዎችን መስጠት ተችሏል:: ከዚህ በተጨማሪም ለረዥም ጊዜ መውጣት ብትናፍቅም መውጣት ያልቻለችን አንዲት ሴት በቀላል ድጋፍ መንቀሳቀስ የምትችልበትን ዘመናዊ ዊልቸር ለግሷል:: ከዚህ ባለፈ ግን በአካባቢው ያለ
እንዲሁም በአንድ ቦታ በርካታ ወገኖችን ይረዳ ለነበረውና ከእነርሱ የተሻለ ቢሆንም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዘርዘር ማለት ስላለባቸው ተጨማሪ ቦታ ለመከራየት ለተገደደው ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አጋርነታቸውን ለመግለጽ ግምታቸው 10ሺህ ብር የሆኑ 13 ፍራሾች ድጋፍ ተደርጓል::
በዚህ መልኩ ሥራውን አንድ ብሎ የጀመረው ማህበር የያዘውን ዓላማ ከማሳካት አንጻር በእንጦጦ ቁስቋምና አካባቢው ላይ ያሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ከሕዝቡም ከአስተዳደሩም ጎን ሆኖ የሚሰራ ሲሆን፤ በትምህርቱም፣ በጤናውም፣ በአቅም ግንባታውም፣ በአረንጓዴ አሻራውም፣ በማዕድ ማጋራትም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ በሆኑ ማህበራዊም ኢኮኖሚያዊም ጉድለቶች በመሳተፍ የሚችለውን ሁሉ ለመደገፍና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚንቀሳቀስ ይሆናል:: ለዚህ ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እስከሚያቆም ችግሩን መቋቋም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራና ድጋፉንም በዚሁ አግባብ የሚቀጥል ሲሆን፤ ወረርሽኙ ከቆመ በኋላ ግን ትኩረታቸውን ትምህርት ቤቶች ላይ፣ ጤና ላይ፣ ሥራ አጥነት ላይና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በማድረግ ከመንግሥት ጋር የሚሰሩ ይሆናል::
በዚህ ሂደት የአካባቢው ወጣቶችና ተወላጆች በገንዘብም በጉልበትም ለመስራት ማህበሩን የማጠናከርና ተምሳሌት በማድረግ ጭምር ኅብረተሰቡን የመደገፍ ሥራ የሚያከናውኑ ሲሆን፤ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችም ማህበሩን እውን እንዲሆን ከሀሳብ ጥንስስ እዚህ እስኪደርስ የሰሩና የማህበሩ ቀዳሚ አባል እንደመሆናቸው መጠን ማህበሩ እንዲጠናከርና ያስቀመጠውን ዓላማ እንዲያሳካ ከማድረግ አንጻር የማይተካ ድርሻቸውን እየተወጡ ነው፤ ይሄንኑም አጠናክረው ይቀጥላሉ:: ይህ እቅድና ምኞት ግን የበለጠ ስር ሰድዶ ሊጓዝና ችግሮችንም ከመሠረታቸው ለመፍታት የሚያግዝ አንድ አካል የሚሆነው በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት ሲታገዝ እንደመሆኑ፤ የመንግሥት አካላት በተለይም የአካባቢው አስተዳደር የማህበሩን እንቅስቃሴ ተገንዝቦ ሊያግዝ እና በተለይም ከቢሮና ተያያዥ ነገሮች ጋር የሚያጋጥመውን ችግር ከወዲሁ ከግምት አስገብቶ መልስ ሊሰጠው ያስፈልጋል::
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤፍሬም አሩሲ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የኮቮድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ አራት ወራት እየሆነው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወረርሽኙ እንደ አገርም ሆነ እንደ ከተማ የሚፈጥረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖን ለመቋቋም መንግሥት የበኩሉን እየተወጣ ነው:: ሆኖም የመንግሥት ሥራ ብቻውን ምንም ስላልሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በምክትል ከንቲባው የተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ ዜጎች በየቦታው እየተደራጁና ማህበራትም እያገዙ በየአካባቢያቸው ያሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖችን እያገዙና ማዕድም እያጋሩ ይገኛል:: በእንጦጦ አካባቢም ተመሳሳይ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ የእንጦጦ ቁስቋም በጎ አድራጎት ማህበር ያከናወነው ተግባርም የዚህ አንድ ማሳያ ነው::
ማህበሩ በአካባቢው ላሉ ችግር ላይ ለወደቁ ዜጎች ያደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግነው አባላቱንም የሚያስመርቅ ተግባር ሲሆን፤ በአካባቢው ካለው የኅብረተሰብ ክፍል አኳያ ሲታይ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ወገኖችን የመደገፍ ሥራው በአንድና ሁለት አካላት ብሎም ማህበራት ብቻ ሳይሆን በርካቶች ተሳትፈው ሊያከናውኑት የሚገባ ነው:: በዚህም በወረዳው ያሉ አቅም ያላቸው ሰዎች ቢያንስ አንድ ጎረቤት ይዘው ማገዝ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር የሚገባቸው እንደመሆኑ፤ እርሳቸውም እንደ አንድ የወረዳው አመራር ለቀጣይ ሦስት ወራት ከ500 እስከ 800 ብር የሚገመት አስቤዛ ለቀለሟ ደሳለኝ ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል::
ይህ ተግባር ከሁሉም አመራርና ኅብረተሰብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ሌሎች መሰል ድጋፎችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል:: ከጅምሩ በዚህ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ጉዞውን አንድ ብሎ የጀመረው የእንጦጦ ቁስቋም በጎ አድራጎት ማህበርም ከጥንስሱ ጀምሮ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በቅርበት እየተመካከረ እየተጓዘ ለዚህ የደረሰ ሲሆን፤ እነዚህን መሰል ማህበራት ደግሞ በርካታ የመንግሥት ሥራዎችን አግዘው የሚያከናውኑ መሆናቸው ይታወቃል:: በመሆኑም የወረዳው አስተዳደርም ለዚህ ማህበርም ሆነ ሌሎች በመሰል ተግባር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን እንደየ ሥራ ባህሪያቸውና እንቅስቃሴያቸው እያየና እየተመካከረ ከቢሮ ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ወንድወሰን ሽመልስ