ሁልጊዜም ዓይኔን በገለጥኩና እግሮቼን ባንቀሳቀስኩ ቁጥር የሚያስገርሙኝ ገጠመኞች ይበረክታሉ። ዓይነቱና ብዛቱ እንደአዋዋሌ እንደሚወሰን ልብ በሉልኝ። ምክንያቱም እኔ ማለት የአዋዋሌ ነጸብራቅ ነኝና። እንደአዋዋሌ ነው የማስበው፣ እንዳዋዋሌም ነው የምረዳው፤ የምተነፍሰውም እንደአዋዋሌ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ‹‹ነገሮች ሲዘበራረቁ ፈር ሊይዙ ነው›› ይሏት አባባል ይመስጠኛል። በመዘበራረቅ መሃል ነገሮች ሲስተካከሉ ያልተጠበቁ ስለሚሆኑ ያስደስታሉ። በአንጻሩ ደግሞ የሚስተካከሉ ነገሮች እንደሚኖሩ ሁሉ ተዘበራርቀው የሚቀሩት ሊበዙ ይችላሉና ግራ ያጋባሉ።
ለማንኛውም ወደ ዛሬው ትዝብቴ ልምራችሁ። ሁልጊዜም ሰኔ ግም ሲል የሚከሰት ዘመቻ መሰል ድርጊት አለ። የችግኝ ተከላ። መልካም ነው አሻራውን ማስቀመጥ ማን ይጠላል። በተለይም ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ተብሎ እንደ ሩጫው ሪከርድ ለመስበር የተደረገው ጥረት በምን እንደተቋጨ ባላውቅም ጥረቱና ዘመቻው የሚደንቅ ነበር። ችግር የሚሆነው በእውቀትና በእምነት ያልታገዘ ዘመቻ ከሆነ ብቻ ነው።
ያው እንደተለመደው ‹‹ይህን ያህል ፐርሰን ጸድቋል›› የሚል ሪፖርት ወጥቶ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ይህ ስሌት ብዙም አይገባኝም፤ምክንያቱም የት እና እንዴት? የሚሉትን ጥያቄዎች አይመልሱልኝምና። የገጠሩን ባላውቅም የእኔ ዓይን ያረጋገጠው ሪፖርት ግን ለተከታታይ አምስት ዓመታት መቶ በመቶ ያልጸደቁትን የመንገድ ዳር ችግኞች ነው።
ልብ ብላችኋል በመንገድ ዳርና ዳር ላይ የሚተከሉትን ተስፋቢስ ችግኞች? ለእቅድ ማስፈጸሚያ በዘመቻ ስለሚተከሉ ነው መሰል ዕድሜያቸው ከክረምቱ ዝናብ ጋር አብሮ ያከትማል።
ላይጸድቁ ክረምቱ በመጣ ቁጥር በዘመቻ የሚተከሉ ችግኞች ጉዳይ ይገርመኛል። አንዳንድ ጊዜ እነሱን እሆንና ‹‹ላታጸድቁ አትትከሉኝ›› እያልኩ መጮህ ይዳዳኛል። እነሱም አፍ ቢኖራቸው የመጀመሪያው ጩኸታቸው ‹‹ላታጸድቁ አትትከሉኝ፤ ከተከላችሁ ተንከባከቡኝ›› እንደሚሆንም አልጠራጠርም።
የሚገርም እኮ ነው ጎበዝ! አንድ ቦታ ላይ፣ እንድ ጉድጓድ ላይ እንዴት ክረምት በመጣ ቁጥር ለዓመታት ችግኝ ይተከላል። ለምን እንደማይጸድቅ የሚጠይቅ እንዴትስ ይጠፋል? እውነት እውነት እላችኋለሁ አምስት ዓመት በተመላለስኩበት መንገድ ላይ በየዓመቱ ችግኝ ሲተከል አይቻለሁ። እንክብካቤ ሲደረግ ግን ያየሁበትን ቀን አላስታውስም።
ያው የክረምትን ዝናብ ታሳቢ ተደርጎ ይተከላል፤ዝናቡ ሲቆም ችግኞቹም ደርቀው ይጠፋሉ። ከአቅማቸው በላይ የሚደረግላቸው መከለያም ለመድረቃቸው አንዱ ምክንያት እንደሚሆን አስባለሁ። ሁሉም ነገር ልክ ደርዝ ኖሮት በኃላፊነት መንፈስ ሲሠራ ደስ ይላል። ምንድነው ለይስሙላ ወይም አደረኩ ለማለት ብቻ መዝመት። እውነቴን ነው ለግብር ይውጣ ከሚሠራ ጥንቅር ቢል ይሻላል። መቼም በአስማት እንደማይጸድቁ ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ አይጠይቅም።
ነገርን ነገር ያነሳው የለ። ሌላው የገረመኝን ነገር ልንገራቸሁ። ችግኞቹ የተተከሉባቸው አካባቢዎች ችግኞቹን ሳይሆን ቦታውን ለማስታወቂያነት ይፈልጉትና የማስታወቂያ አዋጁ የሚከለክለቸው ማስታወቂያዎች ሳይቀሩ መለጠፋቸው ነው። በሱስ አሲያዥነታቸው የተፈረጁት ሳይቀሩ ማስታወቂያ ይሠራባቸዋል። ለመሆኑ ይህን የፈቀደው አካል ማን ይሆን? ከፈቀደስ ማስታወቂያውን ያስተላለፉት አካላት አብሮ ችግኞቹን እንዲንከባከቡ ኃላፊነቱን ቢሰጣቸው ምን ነበረበት?
ይህው ክረምት መግባቱን ተከትሎ የመንግሥትን ትዕዛዝ ለመፈጸም ጉድጓዶች እየተቆፈሩ ነው። ታዲያ እስከመች ነው። በየዓመቱ ላይጸድቁ የሚተከሉ ችግኞችን እያየን የምንቀጥለው። ለነገሩ መጠየቅ እንጅ ምላሽ መጠበቅ ‹‹ሱም›› እንደሆነ ስለማውቀው ለጥያቄዎች ሁሉ ራሴ ምላሽ እየሰጠሁ ‹‹ላታጸድቁ አትትከሉኝ›› እያልኩ መታዘቤን እቀጥላለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012