“ጋሹ .. ጋሹ ..” ሲነጋ የሰማሁት የመጀመሪያው ጥሪ ነው።ባለቤቴ ሳምሪ ያለወትሮዋ ቀድማኝ ተነስታ እኔን መቀስቀስዋ ነበር።ቤተሰብ ጋሻ እንድሆን በመመኘት ያወጣልኝ ጋሻው የተሰኘ ስሜ ሚስቴ ደጋግማ ጋሹ በማለት መጥራትዋ መደበኛ ስሜ እስኪመስለኝ ተላምጄዋለሁ።አዳዲስ ሰዎችን ሳገኝ ጋሹ እያልኩ ነው የምተዋወቀው።እኔና ሳምሪ ብዙ የምንግባባባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም አልፎ አልፎ ሳይበዛ ቅራኔ ውስጥ የሚከቱን ጉዳዮች መፈጠራቸው አይቀርም።
እራስ ወዳድ ናት።እንኳን ለሌላው ለኔ እንኳን ግድ የሌላት መሆኗን ያወቅኩት ዘግይቼ ነበር።በተለይ ከሰዎች ጋር ያላት ግንኙነት ጥሩ አለመሆን ከኔ ጋር ሁሌም የሚያጋጨን ዋነኛ ሰበብ ነው።ተግባቢ አይደለችም። በዚያ ላይ ቤታችን ለመጣ ሁሉ ጥሩ መስተንግዶ አለማድረግዋ ቅር ያሰኘኛል።በጣም የሚገርመው ከእርስዋ ቤተሰቦች ጋር ከእርስዋ ይልቅ እኔ ነኝ ይበልጥ የምግባባው።ስልክ ደውለው ስለእስዋ ደህንነት መጠየቅ የሚቀላቸው እሷን አይደለም።
እንደ ነገሩ ተጣጥቤ ልብሴን ከለባበስኩ በኋላ የሰራችውን ፍርፍር አብሬያት መብላት ጀመርኩ።ሳምሪ ባለሙያ ናት።የሰራቸውን ምግብ አጣጥሜ ነው የምበላው።እስዋን ካገባሁ ወዲህ የውጭ ምግብ ዞር ብዬ አይቼ አላውቅም።እየተመገብን ዝምታችንን “ጋሹ እንዴት ነህልኝ ስራስ እንዴት ይዞሀል?” በማለት ሰበረችው።ሳምራዊት አብዝታ የምትንከባከበኝ የሆነ
ጉዳይ ከኔ ስትፈልግ በመሆኑ አውቃለሁ።በጥርጣሬ ተመለከትኳት።በእርግጥ ፍቅርን አጉድላብኝ አታውቅም፤ ታማኝ ሚስቴም ናት። ግን እራስ ወዳድነትዋን በጣም እጠላዋለሁ።
እንደተጋባን አንድ ቀን ገበያ ይዣት ወጥቼ አንድ ምርጥ ስጦታ ለእናቴ ልሰጥ አስቤያለሁና አንቺ ምረጪልኝ ብዬ የወደደችውን ነገር ገዝታ አስጠቅልላ እንድታመጣልኝ ወደ አንድ የስጦታ ዕቃ መሸጫ መደብር ላኳት። እናቶች በጣም የሚወዱት ውድ ነገር ነው ብላ ያስጠቀለለችውን ሰጠችኝ።የገዛቸውን ስጦታ ለራስዋ ሰርፕራይዝ ላደርጋት ፈልጌ ነበርና ምሽት ላይ እቤት እጅዋን ይዤ ሰጠኋት።እኔ በጣም ትደሰታለች ብዬ ጠብቄ ነበር። ነገር ግን ደነገጠችና በማደርገው ነገር ግራ ተጋባች። በኋላ እንድትከፍተው ነግሪያት ስትከፍተው አንድ ተራ ነገር መሆኑን ሳይ እኔ እስዋን ታዘብኩ፤ እስዋ ደግሞ ባደረገችው ነገር አፈረች።ይህን አጋጣሚ ሳስበው ሁሌም የሳምሪ ቀና አለመሆን ይታሰበኛል።
ሻይ መድገም ፈልጌ ነበርና የጨለጥኩትን ብርጭቆ ተቀብላ ቀድታ እያቀረበችልኝ በተለመደው ስሜን “ጋሹ” ብላ ስትጠራኝ ቀና ብዬ ተመለከትኳት።አቤት የማለት ያህል። “ዛሬ ምሽት ከጓደኞቼ ጋር አንድ ፕሮግራም አለኝ አምሽቼ ነው የምመጣው። ከሥራ ስትመለስ ካጣኸኝ እንዳይከፋህ ”አመሻለሁ ማለትዋን ባልወደውም ጥያቄዋ ቅሬታ አልተሰማኝም።ነፃ ሆና የፍላጎትዋን እንድትፈፅም እፈቅድላታለሁ።አንድም ቀን ነፃነቷን ተጋፍቼ አላውቅም።ምክንያቱም ሰው ነፃ ፍጡር በመሆኑ ያሻውን
ያለ ጣልቃ ገብነት እንዲፈፅም ሊፈቀድለት ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አባቴ ‹‹ሴት ልጅ የቤት ብርሀን ናት፤ ሲመሽ የቤቱን ጭለማ የምትገፍ፣ ቤት የምታደምቅ ብርሀን ናት። ስለዚህ ሲመሽ እቤትዋ መገኘት አለባት የሚል ፍልስፍናን ያራምድ ነበር።”በመሆኑም “ሴት ልጅ ከመሸ በኋላ ውጪ ማምሸት የለባትም፤ ለደህንነትዋ ጥሩ አይደለም።በጊዜ ቤትዋ መገኘት አለባት።” በማለት ደጋግሞ ይናገር ነበር።እኔም ከአባቴ ልምድ ቀስሜ ለሳምሪ ደጋግሜ ማምሸት ተገቢ አለመሆኑን ስለምነግራት ትገረምብኛለች።በእርግጥ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ስለማልወደው ማምሸትን አትፈልግም።
“ሳምርዬ ምሽት እኮ …” አቋረጠችኝ “ከጓደኞቼ ጋር ነው ሌላ ሰው አይኖርም።” ከብዙ ማግባባት በኋላ እንድትጠነቀቅ ደጋግሜ በመንገር ቅር እያለኝ በእጄ የጠቀለልኩት እንጀራ ጎርሼ አንገቴን በእሽታ ነቀነኩላት። መስማማቴን ለመግለፅ ነበር። በእርግጥ እሷም ፍቃድ
ሳይሆን እንዳውቀው ብቻ ነበር የነገረችኝ ባልፈቅድላትም እንደምታደርገው አውቃለሁ።
“እሺ ነገ ቅዳሜ አይደል ቤተሰቦቼ ይመጣሉ። ለመስተንግዶ የሚሆን አንዳንድ ነገሮች ዛሬ መገዛዛት ይኖርብሻል መሰለኝ ከመሄድሽ በፊት እሱን አድርጊ።” ፊትዋን ቅጭም አድርጋ ተመለከተችኝ።ቤተሰቦቼ እቤቴ እኔን ሊጠይቁ መምጣታቸውን አትወድም።ፊት እንደምትነሳቸውም አውቃለሁ።“ምንም የምገዛው ነገር የለም።ቤት ያፈራውን እናቀርባለን።” ከእርስዋ የሰማሁት
ምላሽ ነበር።“ሳምሪ ከመጡ በጣም ቆይተዋል እኮ ትንሽ ብር ልስጥሽና ….” አሁንም አቋርጣኝ “ይምጡ ቡና ይፈላል፤ እኛ የምንመገበውን በልተው እንሸኛቸዋለን።ምንም የሚገዛ ነገር አያስፈልግም።” ሌላ ቃላት አልተለዋወጥንም።
በንግግርዋ ምክንያት ጣዕሙ የቀነሰብኝ አጣፍጣ የሰራችውን ፍርፍር ሶስት ጊዜ ያህል ጎርሼ እየተቻኮልኩ ከቤት ወጣሁ።በንጋታው የሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ሳምሪ ደወልኩላት “ቤተሰቦቼ እየመጡ ስለሆነ ተቀበያቸው ብዬ ስልኩን ዘጋሁ።ለማምሸት መምጣታቸው ነበር።ከሥራ ወጥቼ ወደ ቤት የሚያደርሰኝን ታክሲ ያዝኩኝ።አብዛኛው መንገድ ስለኔና ባለቤቴ ሳምራዊት እያሰብኩ ሳላውቀው መጓዜን ስልኬ ጠርቶ ከኪሴ አውጥቼው ሳምራዊትን አቤት ብዬ ያለሁበትን ስትጠይቀኝ ቀና ብዬ አይቼ ነበር።
ሳምሪ በስል ማውራትዋን ቀጥላለች፤ እኔም መመለሴን “ሀሎ ጋሹ የት ነው ያለኸው? የት ደረስክ? መተዋል እኮ ” ብላ የተጨነቀች በሚመስል ድምፅ አወራችኝ።ጥሩ ነዋ ታዲያ እንኳን ሰላም ተገናኛችሁ።ደስ ይላል።እኔም እየመጣሁ ነው ።ደሞ ቤተሰቦቼ ናቸው አላልከኝም ነበር እንዴ?” አዎ ምነው የመጡት ሌሎች ሰዎች ናቸው እንዴ?” አልኳት፤ በጥያቄዋ ግራ እየተጋባሁ “የኔ ቤተሰቦች መሆናቸውን ለምን አልነገርከኝም ?” በማለት ጥያቄዋን አስከተለች።ይሄኔ ቅሬታ ባሻከረው ድምፅ እንዴ ባልና ሚስት አይደለን እንዴ ያንቺ ቤተሰቦች የኔ ቤተሰብ አይደሉም እንዴ? ቤተሰቦቼ ይመጣሉ ያልኩሽ እኮ ቤተሰቦቼ ናቸው ብዬ ስለማምን ነው።” የሚል ምላሽ ሰጠኋት።
ለአፍታ ጽሞና ሰጥታ ካዳመጠችኝ በኋላ “እሺ አሁን ተሎ ና ብር ምንም የለም። አንዳንድ ነገር ልገዛዛ በባዶ ቤት እንዴት ነው የማስተናግዳቸው?” ይሄኔ ጠዋት ያለችኝ ታሰበኝና “ ሳምሪ ምንም የተለየ ነገር መግዛት አያስፈልግም፤ ቤት ባፈራው አስተናግጃቸው።” አልኳት።“እንዴ ቤተሰቦቼ እኮ ናቸው እንዴት በተራ ነገር እቀበላቸዋለሁ?” የስዋ ያልጣመኝ ሀሳብ ነበር።
“አዎ ቤት ባፈራው አስተናግጃቸው ጠዋት ቤተሰቦቼ ይመጣሉ ስልሽ የመለሽልኝ ምላሽ ይሄ ነበር።” ብዬ ስልኩን ዘጋሁት።ከታክሲ ወርጄ ወደ ቤት ሳይሆን ጓደኛዬ ጋር ደውዬ ዘወትር ወደማመሽበት ካፌ አመራሁ።ሳምራዊት ባደረገችው ነገር በደንብ እንድትቀጣ እቤት ገብቼ ስትንጎዳጎድ ላለማየትና ሀሳብና ጭንቀትዋን ላለመጋራት ብዬ።..ተፈፀመ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012
ተገኝ ብሩ