ለምን እንደሆነ አላውቅም የመከላከያ ልብስ የለበሱ ወታደሮችን ሳይ ድንገት የሆነ ነገር ውርር ያደርገኛል። የሆነ ኩራት ነገር ይሰማኛል። እኔ ምንም አድርጌ የማላውቅ ሰው ነኝ ! አገራቸውን በተለያየ መንገድ ያገለገሉ ሰዎች ደግሞ ምን ይሰማቸው ይሆን ? እላለሁ።
ወታደር አገር ማለት ነው፤ የአገር ሉዓላዊነት ማለት ነው። በወታደር ላይ መቀለድም ሆነ ማሾፍ በቀጥታ አገር ላይ መቀለድ ማለት ነው።
ሰሞኑን በማህበራዊ የትስስር ገጾች ወታደራዊ ልብስ በማልበስ የሚሰሩ የቀልድ ፎቶሾፖች አሉ። እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ልብ እንበል። ቀልዶች የተሰሩት የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ለመቀለድ ሳይሆን በሌሎች ታዋቂ ሰዎች እየተሰራ ‹‹እነ እገሌ ቢሆኑ..›› ለማለት ነው። ቢሆንም ግን ወታደሮችን የሚመለከቱ ቀልዶችም ነበሩ። ትክክለኛው የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ያልሆነ በፎቶሾፕ የተሰራ ደግሞ ‹‹ወታደሮች ሲጠጡ›› እየተባለ ሲዘዋወር ነበር። በረሃ ውስጥ የጉድጓድ ውሃ እየጠጣ የአገሩን ዳር ድንበር የሚጠብቅ ወታደር ላይ ጃምቦ ቤት ቁጭ ብሎ መቀለድ በጣም ሲበዛ ነውር ነው።
የማህበራዊ ገፆች ቀልድ ይሁን ብለን በቀልድ መልክ እናልፈዋለን፤ ደግሞም አብዛኛው ለቀልድ ነው እንጂ ከዛ ያለፈ ፋይዳ የለውም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደር ተገቢውን ክብር እንደማያገኝ የምናውቀው ግን መሬት ላይ ባለው ሀቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የፖለቲካው ጣጣ ነው። ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር ለወታደሮች የሚሰጠው ክብር ይቀያየራል። የአገሩን ዳር ድንበር ሲያስከብር እግሩን ያጣ ጀግና ጎዳና ላይ ሲለምን ማየት ሞራል ይሰብራል። ‹‹የአገር ፍቅር ዋጋው ይሄ ነው እንዴ!›› ያሰኛል። ተተኪ ትውልድ ላይ የተስፋ መቁረጥ ጠባሳ ያሳርፋል። ‹‹እንዲህ ከሆነ ሽንት እየጠጣሁ በበረሃ የምቃጠለው ለምንድነው?›› የሚል ስሜት ይፈጥራል።
እርግጥ ነው የወታደር መገለጫ ሀብትና የተንደላቀቀ ኑሮ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ደሙን በገበረላት አገር ውስጥ
ጎዳና ላይ ሊወድቅ ግን አይገባም፤ የህዝብ ሀብት ሰርቆ ባገኘው ገንዘብ በመኪና ከሚሄድ ሰው በታች ግን መሆን የለበትም። ኮሽ ሲል የሚያንቀጠቅጠው ፈሪ ሊሳለቅበት ግን አይገባም። ወታደር ከማንም በላይ ክብርና ሞገስ ያለው ነውና!
በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች፣ በሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች፤ ያነበብነው፣ የሰማነውና ያየነው ታሪክ አለ። በውትድርና ዘመናቸው የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ለልመና የተዳረጉ ብዙ ዕንቁ ኢትዮጵያውያን በየጎዳናው ወድቀው እንደቀልድ መታየታቸው ምን ያህሎቻችንን ያስቆጨን ይሆን። ለእነዚህ ሰዎች ትልቅ ክብር መስጠት ነው የዛሬውን ወጣት አገር ወዳድ የሚያደርገው። አገር ወዳድ ወጣት ማለት የግድ ወታደር መሆን ማለት ብቻ አይደለም፤ ዳሩ ግን ለአገሩ ወታደር ክብር የሚሰጥ አገር የመውደድ ስሜት ያለው ሰው ነው። አገሩን ይወድ ዘንድ ደግሞ እንዲወድ የሚያደርገው ነገር መኖር አለበት። እነዚህ ጀግኖች ለአገራቸው የከፈሉት ዋጋ ቢነገረውና ሲከበሩ ቢያይ የአገር ምንነት ይገባዋል። አለበለዚያ ግን ፌስቡክ ላይ ከመቀለድና ባስ ሲልም ከመሳደብ
አያልፍም።
የወታደር ህይወት ከየትኛውም ህይወት የተለየ መሆኑ ለማንም ሰው ግልጽ ነው። የውትድርና ህይወት ያሳለፉ ሰዎች የጻፏቸውን መጻሕፍት አንብቢያለሁ። ሲጀመር ዝም ብለን ብንገምት ራሱ የወታደር ህይወት ግልጽ ነው። አንዳንድ ገጠመኞቻቸው ደግሞ ለማመን የሚከብዱ ናቸው። በፊልም የሚታዩ አስማታዊ ክስተቶችን ነው የሚመስሉት። ከሚነድ እሳት ውስጥ ማምለጥ፣ በጨለማ ገደል ከገባ መኪና ውስጥ መትረፍ፣ ከአውሬ መንጋጋ ማምለጥ፣ ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ መትረፍ፣ ከጥይት ሀሩር መዳን…. በወታዳራዊ ብቃት የተወጧቸው ናቸው። ገደል እየገባ ካለ መኪና ላይ ራስን ማትረፍ መቻል ማንም የሚያደርገው አይደለም። የሚያዝ የሚጨበጥ የሌለው ገደል ላይ መንጠላጠል የሰው ልጅ ብቃት አይደለም፤ ወታደሮች ግን አድርገውታል።
በዚህ ሁሉ ስቃይና መከራ ውስጥ የሚያስደንቀው ደግሞ የወታደር የህግ ተገዥነት ነው። ወታደር ከማንም በላይ ትዕዛዝ አክባሪ ነው። በስነ ምግባር የታነጹ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት
የተመሰከረለት ነው። ይሄ የስነ ምግባር ልዕልናቸው ብቻ እንድናከብራቸው ያስገድደናል።
የወታደር የአገር ፍቅር ከማንም በላይ ነው፤ የታማኝነት ጥግ ያለው ወታደር ዘንድ ነው። ልብ በሉ! የአገር ፍቅርና የሙያ ታማኝነት ባይሆን ኖሮ እንደማንኛውም ቦዘኔ እየሰረቁም ሆነ እያጭበረበሩ መኖር ይችሉ ነበር፤ በየመዝናኛ ቤቱ ማኪያቶ እየጠጡና ፊልም እያዩ ለስሜት መገዛት ይችሉ ነበር። ማጭበርበሩና መስረቁ ይቅር! የቀን ሥራ እየሰሩ የተንደላቀቀ እና የተዝናና ኑሮ መኖር ይችሉ ነበር። ግን የአገር ስሜቱ፣ የሙያ ታማኝነቱ፣ የህሊና ፅናቱ አለ! ይሄ ብቻ እንድናከብራቸው አያስገድደንም?
ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ማንኛውም ሰው ያውቀዋል። ወታደር እንግዲህ ያንን ነው እየተጋፈጠ ያለው። ህይወቱን ነው የሚገብረው። አንድ ወታደር ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሞቶ ጨርሷል። ሞት ለእርሱ ምንም ነው። ለወታደር አገር ከህይወት በላይ ናት።
እነዚህ ወታደሮቻችንን አለማክበር፣ ውለታቸውን አለመዘከር፣ ውለታቸውን መክዳት በራሱ የአገር ክህደት ነው። የወታደር ቤተሰቦች ቀና ብለው በኩራት የሚሄዱ እንጂ ለልመና የሚዳረጉ መሆን የለባቸውም። የአንድ ወታደር ውለታም አገልግሎት ላይ እያለ ብቻ አይደለም፤ በጡረታም ይሁን በሞት ከአገልግሎት ውጭ ሲሆን ቤተሰቦቹ ጭምር ውለታቸው ሊከፈል ይገባል።
እንግዲህ ሰሞኑን ‹‹ወታደር ወታደር›› ያጫወተን የግብጽ ፕሮፖጋንዳ ነው። አያችሁ የአገር ነገር እንዴት እንደሚያደርግ? አረብኛ የሚናገሩ ሙስሊም እህትና ወንድሞቻችን ሰሞኑን በየሚዲያው መነጋገርያ ርዕስ ሆነው ነበር፤ ከብዙዎችም አድናቆት ተችሯቸዋል፤ ለምን አደነቅናቸው? ለምን የማህደራችን ፎቶ አደረግናቸው? ለምን የስልኮቻችንና የኮምፒተሮቻችን ስክሪን ሴቨር አደረግናቸው? የአገር ጉዳይ ስለሆነ ነው። እነርሱስ ለምን ሽንጣቸውን ገትረው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተከራከሩ? ምን ጥቅም የሚያገኙ ሆኖ ይሆን? የአገር ጉዳይ ሆኖባቸው አይደለምን? እንዲህ ነው እንግዲህ የራስ የሆነ ነገር የሚያንገበግብ!
ክብር ለወታደሮቻችንና ለአገር ወዳዶች!
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
ዋለልኝ አየለ