በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ እና በተለይም ቤተሰብ የሌላቸው በርካታ ወጣቶች ለዓመታት ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተሰባሰቡ በአንድ ማዕከል ተሰባስበው የማደግ አጋጣሚን አገኙ።እነዚህ ልጆች ዛሬያቸው በችግር ጨልሞ ይታይ እንጂ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባለወላጅ ልጅ ድጋፍና እገዛ ቢያገኙ ነገ የት ሊደርሱ እንደሚችሉ ማን ያውቃል? እናም በአገር ልጅ ሳይሆን በሰው ልጅ ይሄን እድል ለማግኘት ቻሉ፤ ነጋቸውንም በራሳቸው እንዲወስኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ አገኙ።
በበርካታ የዓለማችን አገራት መሰል ስራ ሲሰራና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ይሄን ተግባር ሲፈጽም የነበረው ይህ ተቋም ደግሞ በፕሮፌሰር ሄርማን ግሬይነር ከ40 ዓመት በፊት እውን የሆነው ኤስ.ኦ.ኤስ ነው።ይህ ማዕከል መጀመሪያ መቐሌ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እና በሂደትም ሐረር፣ ሐዋሳ፣ አዲስ አበባና ሌሎችም ተጠቃሽ በኢትዮጵያ እውን የሆኑ የኤስ.ኦ.እስ የልጆች ማዕከላት መሆናቸውን በህጻናት መንደሩ ቀዳሚ ልጆች አንዱ የሆነው አቶ ኃይለሚካኤል ዋሲሁን ያስረዳል።
አቶ ኃይለሚካኤል እንደሚያስረዳው፤ በማዕከሉ ማደግ ብቻ ሳይሆን ተምሮ ለወግ ማዕረግ መብቃት የምስራቹ ዓላማ ነው።በዚህም የማዕከሉ ልጆች እንደ እህትና ወንድም ሆነ በፍቅርና እንክብካቤ እንዲያድጉ ብቻ ሳይሆን፤ ተምረው ለቁም ነገር እንዲደርሱ ትልቅ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።በዚህም በየአካባቢው አሉ በተባሉ ትምህርት ቤቶች እየተከፈለላቸው እንዲማሩ ይደረጋል።
ከዚህ ባለፈም፤ ማዕከሉ ልጆቹን በካምፕ ውስጥ የሚያሳድግ እንደመሆኑ ልጆቹ ማህበራዊ ግንኙነታቸው በሚፈለገው ልክ ላይሆን ይችላል።ምክንያቱም አብረው ከሚያድጓቸው እህትና ወንድሞቻቸው ውጪ ማህበራዊ ግንኙነት የሚኖራቸው በትምህርት ቤት ካላቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያሉ ተማሪዎች ጋር ነው።እናም ልጆቹ የተወሰነ ሲያድጉና ራሳቸውን ማገዝ በሚችሉበት የዘጠነኛና በዛ ደረጃ ክፍል ላይ ሲደርሱ ማዕከሉ ቤት ተከራይቶ ከማዕከሉ ውጪ እንዲኖሩና ማህበራዊ ህይወትን እንዲለማመዱ እድል ይፈጥርላቸዋል።ይህ እድሜያቸው ደግሞ የተለያየ ነገርን ማየትና መሞከር የሚፈልጉበት እንደመሆኑ ልጆቹ ነጻና ከህብረተሰቡ ጋር መልካም መስተጋብር የሚፈጥሩበት እንደሚሆንም ይገመታል።
እኔም በማዕከሉ ካደጉ ልጆች የመጀመሪያዎቹ ውስጥ እንደመሆኔ፣ በእንክብካቤ ከማደግም በላይ ተምሬ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪነት በቅቻለሁ የሚለው አቶ ኃይለማርያም፤ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ግን የመኪና አደጋ ደረሰብኝ።እንኳን በስኬት ጎዳና እያሉ ሲቸገሩ የመደገፍ ቀርቶ ባልሆነ መንገድ የተጓዙትን ብሎም የሞቱ የማዕከሉን ልጆች የማይጥለው ይህ ድርጅት እሳቸውንም በተለያዩ የውጭ አገራት ወስዶ አሳክሞኛል።ከዓመታት የውጭ ቆይታ በኋላ ግን ወደ አገሬ ተመልሼ በግል ስራ ላይ ተሰማርቼ እየሰራሁ እገኛለሁ ሲልም የማዕከሉን ለሚያሳድጋቸው ልጆች የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል መልካም እንቅስቃሴ ያስረዳል።
በዚህ መልኩ ልጆች በቻሉት ልክ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሲያደርግ፤ የቻሉ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡና አስተምሮ ሲያስመርቃቸው፤ ካልቻሉም በሚፈልጉት መስክ ተሰማርተው እንዲሰሩ የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ጭምር ደግፎ ለስራ ሲያበቃቸው፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የመኖር ፍላጎታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱም እንዲኖሩም ሲያደርጋቸው ቆይቷል።በዚህም በርካታ ልጆች በተለያየ የሙያ ዘርፍ ገብተው ለአገርና ህዝባቸው እንዲያገለግሉ ሆነዋል፤ በርካቶችም ከአገር ውጪ የሚኖሩበት እድል ተፈጥሮላቸው በውጭ አገራት ይገኛሉ።
ይሄን በፍቅር እና በአንድነት እንደ እህትና ወንድም ሆነው ያደጉ እነዚህ የኤስ.ኦ.ኤስ ልጆች ታዲያ ፍቅርና መተሳሰብን፤ በደማመጥና መተጋገዝን፤ ትጋትና የተሻለ ሆኖ የተሻለ ማድረግን ተምረው አድገዋል እና ከማዕከሉ ወጥተው የየራሳቸውን ህይወት ከመሩም በኋላ ይህ የመተሳሰብና የቤተሰባዊ መጠያየቅ ባህሪያቸው አብሯቸው ቀጥሏል።በተለይ ሰው ሁሉ በተሰማራበት የተሳካ ጉዞ ይጠብቀዋል ማለት ስለማይቻል፤ በዚህ መልኩ ያሉ
ወገኖቻቸውን ብሎም እህትና ወንድሞቻቸውን ማገዝና መጠየቅ እንዳለባቸው ልቡናቸው ይነግራቸዋል።እናም የቀድሞ የኤስ.ኦ.ኤስ ልጆች ማህበር በሚል የመሰባሰብና የመረዳዳት ህልማቸውን የሚያሳልጡበት ማህበር ይመሰርታሉ።
በማዕከሉ ያደጉ ወጣቶች እርስ በእርስ ለመደጋገፍና ለመረዳዳት አስበው ያቋቋሙት ይህ ማህበርም ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ሆኖታል። ማህበሩን ሲመሰርቱት ከዚህ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ዓላማው በተጓዳኝ የሄርማንን ወይም የኤስ.ኦ.ኤስ ትምህርት ቤት ለማዕከሉ ማስተማሪያ ይውል ካልሆነም ቢያንስ ከፍተኛ 23 የሚለውን ስያሜ ትቶ ቢያንስ የቀድሞ ስያሜውን እንዲይዝ ወይም ሌላ ታሪክ በሚያስታውስ ስያሜ እንዲጠራ የማድረግ፤ የፕሮፌሰር ሄርማንን መታሰቢያ ሐውልት እንዲሰራ የማስፈቀድ፤ እንዲሁም የማዕከሉ አዳጊ ልጆች በተለያየ ምክንያት በተለይም ከመታወቂያ እና ሌሎች የቤት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚስተዋልባቸውን ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ በጋራ መስራትንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ኃይለሚካኤል የሚናገረው።
የማዕከሉ ቀዳሚ ከሆኑ ልጆች አንዱ የሆነውና የማህበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ኃይለሚካኤል እንደሚገልጸው፤ እነዚህ መልካም ነገርን ተምረውና መልካምነትን ቀስመው ያደጉ ወጣቶች ታዲያ ከእርስ በእርስ መተሳሰብና መደጋገፍ ዓላማቸው ባለፈ ለሌሎች መድረስንም ዓላማ አድርገው እየሰሩ ይገኛል።በዚህም ከአንድም ሁለት ጊዜ ደም ለግሰዋል፤ በአከባቢ ጥበቃ ስራው አንድ አካል የሆነው የአረንጓዴ አሻራን ምክንያት በማድረግም ችግኝ ተክለዋል።የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ተጽዕኖን ተከትሎም ለበርካታ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ችለዋል።
በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሺኝ ጋር ተያይዞ የማዕከሉ ልጆች የነበሩ ወጣቶች በርካቶቹ ትልቅ ቦታ ላይ የደረሱ ቢሆንም፤ ጥቂት የሚባሉቱ በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሳቸው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ መኖራቸውን በመገንዘባቸው እነርሱን የመደገፍ እርምጃ ወስደዋል።በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የማዕከሉ ልጆች ገንዘብ አሰባስበው መደገፍ ቻሉ።ከዚህ ባለፈ የማዕከሉ ልጆች በተናጠል በርካታ ወገኖችን መደገፍ ችለዋል።ለማዕከሉ ልጆችም የሙያ፣ የስራ እና ሌላም ራሳቸውን የሚችሉበት እድል በመፍጠር ረገድ በብዙ መልኩ እየደገፉም ይገኛል።
ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ማዕከሉ እነዚህን ልጆች በድጋሚ እንዲደግፍ እሱን ከመጠበቅ ይልቅ እነርሱ እነዚህም ማገዝ ከቻሉ ማዕከሉ ሌሎች የተቸገሩ ህጻናትን አንስቶ መደገፍ እንዲችል ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ ዋናው ዓላማቸውም ከፕሮፌሰር ሄርማን የተማሩትን
መልካምነት በተግባር መግለጽ እንዳለባቸው በማመን ነው።ይህ ደግሞ ከሰው የሚጠበቅ ተግባር ሲሆን፤ እነርሱ ያገኙትን መልካምነት በሌሎች ለማድረግ የበለጠ አጠናክረው የመቀጠል እቅድም ምኞትም አላቸው።
አቶ እዮብ በቀለ፣ የቀድሞ የኤስ.ኦ.ኤስ ህጻናት መንደር ልጆች ማህበር ሰብሳቢ ነው።እርሱ እንደሚለው፤ ማህበሩን የመሰረቱ እነዚህ ወጣቶች ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ መቐሌ፣ ሐረር፣ ባህርዳርና ሌሎችም ማዕከሎች ውስጥ አብረው ያደጉ ሲሆኑ፤ አሁን ላይ ከድርጅቶቹ የወጡ እና የራሳቸውን ህይወት እየኖሩ ያሉ ወጣቶች ናቸው።በመሆኑም የማህበሩ መቋቋምም ከማዕከሉ የወጡ ወጣቶች እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉበትና በሚያጋጥማቸው ሁሉ የሚረዳዱበትን፣ ቤተሰባዊ ማንነትና ትስስራቸውን እንዲያዳብሩ ለማስቻል ሲሆን፤ እድል መፍጠርን ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ ነው።
አቶ እዮብ ስለ ማዕከሉ ወጣቶችና ዛሬ ላይ ይዘው ስለተነሱት ዓላማ ሲያስረዳ እንዲህ በማለት ነው።ዛሬ እህትና ወንድም ሆነን ያለነው እኛ እህትና ወንድም ሆነን ያደግነው በኤስ.ኦ.ኤስ ህጻናት መንደር ነው።ይህ የህጻናት መንደር ደግሞ በዓለማችን ላይ በብዙ አገራት የሚገኝ፤ በኢትዮጵያም ስምንት ያህል መንደሮች ያለው ነው።ይሄንን ዓላማ ይዞ የተነሳው ደግሞ ፕሮፌሰር ሄርማን ግርማይነር ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለእኛ በህይወታችን ውስጥ የደግነትን ጥግ ያሳየን ሰው ነው።ይህ ሰው ለእኛ መሰባሰብ እና ማደግ ብሎም የህይወት አቅጣጫን የማግኛ መንገዶችን ከቀረጹልን ሰዎች አንዱ ነው።
በዚህ መልኩ እኛን ረድቶ ለዚህ ያደረሰን እሱ እንደመሆኑም፤ እኛ ደግሞ በህይወታችን የተማርነውና የተካፈልነው ነገር ስላለ እንዲሁም የተደረገልን ሰዎች ስለሆንን፤ በውስጣዊ ስሜት ብቻ ሳይሆን ተደርጎልን ተለውጠን ያየን ሰዎች ስለሆንን ነው።ይህ የተደረገልን ሰዎች እንደመሆናችን ደግሞ ከእኛ በላይ የማድረግ ግዴታ ያለበት ሰው አለ ብለን አናምንም።ምክንያቱም የተካፈልነው ነገር ትልቅ ነው።የተደረገለት ሰው ደግሞ ለማድረግ ወደኋላ ስለማይል እናም እኛ የኤስ.ኦ.ኤስ ልጆች ሰውን ለመርዳት ቅርብ ነን።
እናም ይህን የማድረጋቸው ምክንያት ደግሞ በህጻናት መንደር ውስጥ ያደጉት ሁሉም ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እና በማሳደጊያው አብረዋቸው ያደጉ ልጆችን እህትና ወንድሞች በስተቀር ሌላ የእኔ የሚሉት ሰው ስለሌለ ያለው አማራጭ ሁሉም እርስ በእርሱ የመረዳዳት፣ በድካሙ ጊዜ የመቆምና የማበረታት፣ ስራዎችን ለማከናወን ነው።ከዚህ በተጨማሪም በተለያየ የህይወት አጋጣሚ እና በመልካም
የህይወት መንገድ ላይ የሚኖሩ ይኖራሉ።አንዳንዴም ህይወት ሳትፈቅድ ስትቀር ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በወጣቶቹ ላይ የህይወት አለመሳካት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
እናም ያንን ነገር እንደ ቤተሰብ፣ እንደ እህትና ወንድም በመሆን እርስ በእርስ በመነጋገር እነዛን ነገሮች በማጥናትና በማስተካከል አቅም በፈቀደ መልኩ የመደገፍና የማገዝ ነገር እናደርጋለን።አሁን ደግሞ በአገርም በዓለምም ሰዎችን ለከፋ ጉዳትና ችግር እየዳረገ ያለው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ይሄን ነገር በሰፊው እንድንሰራ ያደረገን ሲሆን፤ እኛም በዚሁ አግባብ እየረዳን እንገኛለን።ይህ ማለት ወቅቱ የእርስ በእርስ መተጋገዛችንን የሚፈልግበት ሰዓት የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ምክንያቱም ቫይረሱ ባመጣው ችግር ምክንያት ቀደም ሲል ሰርተው የሚበሉ እንኳን ሰርተው መብላት ያልቻሉበት ጊዜ ተፈጥሯል።በኮቪድ ምክንያት ከስራ መቀነስ የደረሰባቸው፤ እንዲሁም በህይወት አጋጣሚያቸው ህይወት ፈትናቸው ያሉ ይህ ሲጨመር ደግሞ ችግሩ ከብዷቸው ያሉ ወጣቶች አሉ።እነዚህን አቅም በፈቀደና በተቻለ መጠን የመደገፍ ስራ እየሰራን ነው።በቅርቡም ለእነዚህ አይነት ሰዎች ድጋፍ አድርገናል።በዚህም ለሁለት ወር የሚሆን የምግብ አቅርቦት እርዳታ አድርገናል።
በዚህ ድጋፍም በአንድ ቀን ለ43 ወጣቶች ድጋፍ ያደረግን ሲሆን፤ ከዛም በኋላም በየቤታቸው በመሄድ ጭምር ድጋፉን በማድረስና በመጎብኘት ለተለያዩ ወጣቶች ድጋፍ በማድረግ በድምሩ 83 ሰዎችን በድጋፍ ስራው ተደራሽ ማድረግ ችለናል።ይህ ነገር እንደተባለው በአገራችን እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ሌሎች ይሄንን ተግባር መቀላቀል እንዲችሉ የማስቻል ተግባርም ነው እያከናወንን ያለነው።እነዚህ ወጣቶች ግን መልካም ተደርጎላቸው ያደጉና የሰውነት ልክ ያዩ ናቸውና አሁን ላይ ባደረጉትና እያደረጉ ባሉት ተግባር የረኩ አይመስልም።እናም ሌላ እቅድና ምቾት ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው እየሰሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
የማህበሩ ሰብሳቢም ይሄንኑ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ይህ ተግባር እንደ መጀመሪያ የሰራነው ስራ ነው።ይሄን ነገር አጠናክረን የመቀጠል ሀሳብም ስላለንም አቅም በፈቀደ መልኩም እነዚህን ነገሮች አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።ብዙ ሰዎችን የመድረስ ዓላማም ስላለን እድሉን በምናገኝባቸው በተለያዩ ቦታዎችም ለመሳተፍ ፍላጎት አለን።ሲል ነው አቶ እዮብ ስለ ቀጣይ የመልካምነት ጉዞ ዓላማቸው፣ ምኞትና ፍላጎታቸው በእቅድና ተስፋቸው ውስጥ ሆኖ የሚያስረዳው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ወንድወሰን ሽመልስ