በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ትምህርት መስጠት ከጀመረ ከሺህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ዘመናዊ ወይንም ሳይንሳዊ ትምህርት መሰጠት የጀመረው ግን በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። የመደበኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ለመስፋፋቱም እንደ አንድ ዐብይ ክስተት የሚቆጠረው ድርጊት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተከናወነውና በንጉሠ ነገሥቱ ስም ተሰይሞ እስካሁንም ያለው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም መከፈቱ ነው።
ለዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትና ማደግ ፍላጎት መምጣት የጀመረው ደግሞ ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ በመምጣቱ ነበር። በወቅቱም ንጉሠ ነገሥቱ በአንድ ወገን ትምህርት ለአገር እድገትና ብልጽግና ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን በመገንዘብ፤ በሌላ በኩል እንደ አድዋ አይነት ዳግም ወራራ ቢከሰት ለመመከት የተማረ ኃይል እንደሚያስፈልግ ተረድተው ነበር።
በዚህም ልጁን የማያስተምር ወላጅ ሀብቱ እንደሚወረስ እስከ ማወጅ ደርሰው በትምህርት ላይ ጠንካራ ውሳኔዎችን ያስተላልፉ የነበረ ቢሆንም፤ በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር የነበረው ፍላጎት ውስን በመሆኑ መኳንንቱ አሽከሮቻቸውን እንዲያስተምሩ እስከማዘዝ መድረሳቸውንም የታሪክ ሰነዶች ይናገራሉ። ልጃቸው ግርማዊት ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክም የአባታቸውን ፈለግ ተከትለው ትምህርት የማያስተምሩ ወላጆችን የሚቀጣ አዋጅ አውጀው ነበር።
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከመቶ ዓመት በፊት ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ የተጀመረ ቢሆንም፤ እስከ ቅርብ ጊዜ የተደራሽነቱ ነገር እዚህ ግባ የሚባል ሳይሆን ቆይቷል። ነገር ግን በእነዚህ ዘመናት በርካታ ወላጆች ሳይማሩ ብሎም መጻፍና ማንበብ ሳይችሉ እንኳን እድሉን ሲያገኙ ብዙዎችን ለወግ ለማረግ አብቅተዋል። ዛሬ ዛሬ በትምህርት ተደራሽነት ረገድ መንግሥት በሚያስመሰግን ሁኔታ ተጨባጭ ሥራዎችን የሰራና እየሰራም ያለ ቢሆንም ጥራትን በተመለከተ ግን በየደረጃው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። ለትምህርት ጥራት መጓደል በየወገኑ እንደየሰው እይታ የተለያዩ ምክንያቶች የሚሰነዘሩ ሲሆን ወላጆች ለልጆች ትምህርት የሚሰጡት ትኩረትና ክትትል ዝቅተኛ መሆንም ከእነዚሁ መላምቶች መካከል አንዱ ነው።
በቅርቡ ደግሞ ዓለምን አዳርሶ ኢትዮጵያንም እየጎበኛት ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአዋጅ ትምህርት እንዲቆም አስገድዷል። ይህም ሆኖ ልጆቹ ከትምህርት መራቅ ስላልነበረባቸው የተለያዩ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ትምህርቱን ተደራሽ ለማድረግ መንግስት እየሰራ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ከአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር ትምህርት በቤቴ ፕሮግራም እየሰጠ ይገኛል። በዚህ ፕሮግራም በቤተሰብ ድጋፍ ትምህርታቸውን ተከታትለው የተሰጠውን ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡትም ሽልማቶችን ሰጥቷል። እኛም በዚህ ዘመን በትምህርት ብዙም ሳይገፉ ልጃቸውን ለዚህ ያበቁትን እናትና አባት ይዘን ቀርበናል።
አቶ ሽኩር መሀመድ በሽር ይባላሉ፤ ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል ቅልጦ ወረዳ ሲሆን፤ አሥራ አምስት ዓመት እስኪሞላቸውም የቆዩት በተወለዱባት ትንሽ መንደር እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብት እየጠበቁና በሌሎች የጉልበት ሥራዎች ቤተሰቦቻቸውን እያገዙ ነበር። በአካባቢያቸው ዘመናዊ ትምህርት ባይኖርም በእስልምና ሃይማኖት የሚሰጠውንም የቁርአን ትምህርት ለመከታተል ቦታው እሩቅ ስለነበርና ለእናታቸው የነበሩት ሁለት ልጆች ብቻ በመሆናቸው ምግቡም መንገዱም ስለሚያስቸግር ትጎሳቆልብኛለህ በማለት እናት እንዲማሩ አልፈቀዱላቸውም ነበር። አሥራ አምስት ዓመት ሞልቷቸው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም ከወንድሞቻቸው ጋር ሱቅ በመስራት ላይ ሳሉ በወቅቱ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል ለመቁጠር እድሉን ያገኙ ቢሆንም ከዛ የዘለለ ለመማር ግን ሁኔታዎች አልፈቀዱላቸውም ነበር።
አቶ ሽኩር «የተማረ ሰው ቢነግድም ምንም ቢሆን የተሻለ ውጤታማ ይሆናል ትምህርት ለልብም ለእግርም መንገድ ነው» በሚል ለትምህርት ለየት ያለ እይታ ነበራቸው። ስለዚህ ለትምህርት ተብለው የሚሰስቱት ነገር አልነበራቸውም ልጆቻቸውንም ጠንክረው እንዲማሩ ይጎተጉቱ ነበር። ይህም ሆኖ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ልጆቻቸው የተማሩ ቢሆንም እሳቸው በሚፈልጉትና
በሚጠብቁት ደረጃ አልሄዱላቸውም ነበር። ሶስተኛ ልጃቸው ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት በቤቴ ፕሮግራም ተወዳድሮ ለሽልማት በቅቶላቸዋል።
«ልጄ ጃፋር ህልሜን እውን አድርጎልኛል» የሚሉት አቶ ሽኩር፤ «ለሽልማት ተጠራሁ ሲለኝ አላመንኩም ነበር፤ ከእናትህ ጋር ሂድ አልኩት። ሽልማቱን ይዞ ሲመጣ ሳየው ግን ወዲያውኑ አላህን አመሰገንኩት እሱንም መረቅኩት። ደስ ያለኝ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ስላመጣ ብቻ አልነበረም። ትምህርት ጥሩ ነው ነገር ግን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ልጆች ጥሩ ባህሪ ይዘው ማደግ እንዳለባቸው አምናለሁ ጃፋር ደግሞ ይህን ያሟላ ነው» ሲሉም የልጃቸው በትምህርት መመረጥ ለእሳቸውና ለቤተሰቡ የፈጠረውን ደስታ ገልጸውታል።
እኔ ብዙ ልጆች ደብተራቸውን ሱቅ እስቀምጠው ፑል ቤትና ሌሎች አልባሌ ቦታዎች ሲገቡ አያለሁ፤ የሚሉት አቶ ሽኩር፤ ተማሪ ልጆች ላላቸው ወላጆችም የሚከተለውን ምክር ያስተላልፋሉ። የቤተሰብ ክትትል ለልጆች ባህሪ ወሳኝ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ከሚማሩበት ትምህርት ቤትና ከመምህራኖችም ጋር መነጋገር መወያየት ይጠበቅባቸዋል። ወላጅ የማይከታተል ከሆነ መምህርና ትምህርት ቤት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም ክትትል ካልተደረገ ደግሞ ልጆች የሚገጥማቸው ከትምህርት መስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ለሌላ ችግሮችም መጋለጥ ይሆናል።
የተማሪ ጃፋር እናት ወይዘሮ ዙቤዳ ናሰር መሀመድ፣ እንደ አቶ ሽኩር ሁሉ ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል አዘርነት የሚባል ቦታ ነው። በአካባቢው በቅርበት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የሶስት ሰዓት መንገድ እየተጓዙ ደራውትና ሰመርቲ በሚባል ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። በወቅቱ ፈረቃ ስላልነበር ትምህርቱ የሚሰጠው እስከ ዘጠኝ ሰዓት ቢሆንም ወደ ቤት ሲመለሱ የእግር ጉዞው ስለሚያደክማቸው ለማጥናት ጊዜ አልነበራቸውም ነበር።
ይሄንንም ሲያስረዱ፣ እቤት የምንደርሰው ጀንበሯ ማዘቅዘቅ ስትጀምር ነው፤ ስለሚደክመን ትንሽ አርፈን እንዳናጠና ደግሞ መብራት እንደልብ የለም፤ እቤት ውስጥ የሚበራውም ኩራዝ ሌላ ለመላው ቤተሰቡ የሚሰራበት ሥራ ስለሚኖር ጥናት የሚታሰበው ቅዳሜና እሁድ ለዚያውም ከሥራ በተረፈ ጊዜ ብቻ ነበር። ይህም ሆኖ ትምህርት ቤት መሄድም ሆነ መማር በዘመኑ ብርቅ ስለነበር ክፍል ውስጥ ስንሆን መምህራኖቻችንን በሥርዓት ነበር የምንከታተላቸው። መጽሐፍ የሚሰጠን አንዳንድ
ጊዜ ለሶስት እጥረት ሲኖር ደግሞ ለአምስት ነበር። በዚህም የተነሳ የቤት ሥራ ሲኖር ተቀባብለን እንሰራ ይሆናል እንጂ እቤት አውሎ አሳድሮ መጽሐፉን ደጋግሞ አንብቦ ለመረዳት እድሉ አልነበረንም። ደብተርና ወረቀት፤ እስክሪብቶና እርሳስም ውድ ስለነበር እንደልብ ገልብጠንም ስለማናስቀምጥ የኛ ማስታወሻ አእምሯችን ብቻ ነበር። በዚህም የተነሳ ትምህርት ለሚለው ነገር ሁላችንም አንጓጓ ነበር።
በ1983 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ይህውም ተቋረጠ ቆይቼም ወደ ትዳር ስለገባሁ የእኔ የትምህርት ነገር አበቃለት። እኔ ግን ልጆቼን ሁል ጊዜ ጥሩ ተማሪ እንዲሆኑ ከመወትወት ተቆጥቤ አላውቅም። በእርግጥ እኔ በትምህርት ስላልገፋህ ይሄ ይሄ ነው እንዲህ ይሆናል ብዪ ማስጠናት አልችልም ነገር ግን ቁጭ ብለው እንዲያጠኑ አዛለሁ የትምህርት ቤት ውሏቸውም እንዴት እንደነበር እጠይቃለሁ አንዳንድ ጊዜም ትምህርት ቤት ሄጄ ያለውን ነገር የምጠይቅበት አጋጣሚ አለ። ሌሎቹ ልጆች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ቢሆንም እንደ ጃፋር ጠንካራና ውጤታማ አይደሉም መጀመሪያ ደረጃ ጃፋር እኛ አጥና እስክንለው የሚጠብቅ ልጅ አይደለም እቤት ውስጥም ሣርዓት በማክበር የሚታወቅ ነው። የቤተሰብ ሽልማት አለ ስባል አላመንኩም ነበር፤ መጀመሪያ ቢሸለምስ እሱ እንጂ እንዴት የቤተሰብ ይሆናል አልኩ። ካረጋገጥኩና አብሬው ሽልማቱን ከተቀበልኩ በኋላ ግን እስካሁን ደስ እንዳለኝ አለሁ።
በአሁኑ ጊዜ ለመማር ብዙ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፤ ነገር ግን መሰናክሉም የዛን ያህል ነው፤ የገጠር ልጅ በተስተካከለ ሁኔታ ለመማር ሁኔታዎች ተመቻችተውለት እድሉን ባያገኝም፤ በአንጻሩ ብዙ ከትምህርት ሊያዘናጉት የሚችሉ ነገሮችም በአካባቢው ባለመኖራቸው እቤት ውስጥ ሥራ ካልሰራ ለትምህርቱ የግድ ትኩረት ይሰጥ ነበር። የከተማ ልጅ ግን ከሚያየው፣ ከሚሰማውና በየወቅቱ ከሚመጡት መጫወቻና መዝናኛዎች አንጻር ከትምህርቱ የሚያዘናጉት በርካታ ወጥመዶች በአካባቢው አሉ።
ይህም ሆኖ ከትምህርት መሰናከል እዳው ብዙ መሆኑን ልጆችም ወላጆችም መረዳት አለባቸው በተለይ ወላጆች ልጆች ቅድሚያ ለስሜታቸው እንደሚሰጡ በመገንዘብ በሥራ ተወጥረው ጊዜ ባይኖራቸው እንኳ በከፍተኛ ትኩረት መከታተል ይጠበቅባቸዋል። እኔ ልጆቼን የግልም የመንግሥትም ትምህርት ቤት አስተምሬያለሁ ህጻናት ሳሉ
በመንግሥት ትምህርት ቤት ብዙ ስለሚሆኑ የግል ትምህርት ቤት ተመራጭ ነው። ከፍ ካሉ በኋላ ግን የመንግሥት የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ መንግሥትም እያደረገ ያለው ድጋፍና ማበረታቻ በጣም ጥሩ ነው፤ ልጆች ትምህርት ቤታቸውን እንዳይጠሉ ወደው እንዲሄዱ የሚያደርግ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ይላሉ።
ጃፋር ሽኩር መሀመድ በሽር የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ሲሆን፤ በለቡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነው። ለሽልማት የበቃበትን መንገድ እንዲህ ይናገራል። አባቴም እናቴም ጠንክሬ መማር እንዳለብኝ ስለሚያሳስቡኝ ሁል ጊዜ የማጠናው እነሱን እያሰብኩ ነበር፤ አሁን አሁን ደግሞ የእነሱ ምክርም ሆነ የእኔ ጠንክሮ መማር ጥቅሙ ለራሴ መሆኑን ስለተረዳሁ የእነሱን ምክር አልጠብቅም። በኮሮና ትምህርት ቤት ስለተቋረጠ የምውለው እቤት ሳጠና ነው አንድ ቀን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትምህርት በቤቴ ፕሮግራም እንደሚተላለፍ ሰማሁና የተሰጠውን አድራሻ ሞልቼ በአፍሮ ሄልዝ ቴሌቪዥን በዲሽ መከታተል ጀመርኩ።
በቀን አንድ አንድ ጥያቄ ይጠየቃል፤ በሳምንት አራት የትምህርት ዓይነቶች ይተላለፋሉ፤ውድድሩ እነዚህን ጥያቄዎች ቀድሞ በትክክል መመለስ የሚል ነበር። ትምህርቱ የሚሰጠው አንዳንድ ጊዜ በኮምፒዩተር ብቻ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አስተማሪ ነው መምህር ቆሞ ሲያስተምር እኔ የተሻለ እረዳለሁ፤ ከትምህርቱ በኋላ ያሉኝን የትምህርት መርጃ መጽሐፍትና ደብተሮቼን ከተማርኩት ጋር እያመሳከርኩ አጠናለሁ። ከዚያ ቀድሞ ሞኦ የሚል ሌላ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እከታተል ነበር ያኛው ግን እንደዚህኛው ግልጽና የተብራራ አልነበረም።
በመደበኛው ትምህርቴ እስካሁን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ለቀቄ አላውቅም ዘንድሮም በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ሁለተኛ ነው የወጣሁት። ከአንድ ወር በላይ ከተከታተልኩና በየቀኑ መልስ ስሰጥ ከቆየሁ በኋላ ስልክ ተደውሎ የእናንተ ቤተሰብ አሸንፏል እናም ተሸላሚዎች ስለሆናችሁ እንድትመጡ ብለው ሽልማቱ ከሚሰጥበት ከሁለት ቀን በፊት አስታወቁኝ። በትክክል ስከታተልና ስመልስ የቆየሁ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ነገር ከዚህ በፊት ስላላየሁ እውነት አልመሰለኝም ነበር። በነጋታውም ደውለው ሽልማቱ መስቀል አደባባይ ሀያትሪጀንሲ ሆቴል ስለሚሰጥ መጥታችሁ እንድትወስዱ የሚል መልእክት ተነገረኝ። በእለቱ ሰባት ሰዓት እንድንደርስ የተነገረን ቢሆንም እኔና እናቴ እቦታው የደረሰነው ቀደም ብለን ስለነበር ሌሎችንም ሰዎች ስናይ እውነት መሆኑን አረጋገጥኩ።
ቤተሰቦቼ ባላቸው አቅም ትምህርትን በተመለከተ የምጠይቀውን ሁሉ ያደርጉልኛል፤ ሳጠና እንዳልረበሽ በጣም ይጠነቀቃሉ። እስካሁን ጠይቄ ያላገኘሁት ነገር የለም። ባገኘሁት ውጤት በጣም ተደስተዋል፤ እኔም የልፋታቸውን ውጤት ገና በጅምሩ ለማሳየት በመብቃቴ በእነሱ ደስታ ረክቻለሁ። አርባ ሶስት ኢንች ቴሌቪዥንና ሌሎች ሽልማቶችንም ተቀብያለሁ ሽልማቱ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተሰብ ለጓደኞቼም ኩራትና መነቃቃት የፈጠረ ነው። አሁንም ትምህርቱን እየተከታተልኩ እገኛለሁ መጀመሪያም ስከታተልም ሆነ ሳጠና የነበረው ይህንን ሽልማት አገኛለሁ ብዬ ሳይሆን ለራሴ በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ ቃል ስለገባሁ ነው በመሆኑም አሁንም በጀመርኩት መሰረት የምቀጥል ይሆናል።
እኔ ከስድስተኛ እስከ ሰምንተኛ ክፍል የተማርኩት የግል ትምህርት ቤት ነበር፤ ነገርግን ከመንግሥት ምንም ያህል ለወጥ አላየሁም፤ ዋናው ነገር ትኩረት ሰጥቶ መማርና ደጋግሞ ማጥናት መሆኑን ተረድቻለሁ። ባጋጣሚ እኔ የምማርበት የመንግሥት ትምህርት ቤት በግል ከተማርኩበትም የተሻለ ቤተ መጽሐፍት መምህራንና ምቹ ሁኔታ ያለበት ነው። የግል ስማር ተማሪውም ቁጥሩ ትንሽ ስለነበር ያን ያክል ውጤትህን በከተማ ደረጃ ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ ፉክክር አልነበረም። አሁን ያለሁበት ግን ተማሪው ብዙ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክርም ያለበት ነው።
አሁን በከተማ ደረጃ ተወዳድሬ ይሄን ውጤት በማግኘቴ የተረዳሁት ነገር አንደኛ መውጣት በራሱ የጉብዝና ማሳያ ሊሆን አለመቻሉን ነው። ጥሩ ተፎካካሪ ከሌለ ዝቅተኛ ውጤት ይዞ አንደኛ መውጣት ይቻላል፤ ያ ግን የኋላ ኋላ በዩኒቨርሲቲም ሆነ በሌላ ደረጃ ከሌሎች ጠንካራ ተማሪዎች ጋር መወዳደር ሲያስፈልግ ከጨዋታ ውጪ ያደርጋል ስለዚህ ያለነን አቅምና ሁኔታዎች ተጠቅመን ሁሌም ጠንክረን መስራት አለብን ለዚህ ደግሞ የቤተሰብ ድጋፍ ወሳኝ ነው መሆኑንም ነው ተማሪ ጃፋር የሚናገረው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ