ልጆች! እንዴት ሰነበታችሁ? የኮሮና ወረርሽኝ እየጨመረ ስለሆነ መጠንቀቃችሁን እንዳትረሱ፤እንዳትዘናጉ። በቤት ውስጥ ስትውሉ ወረርሽኙን ከመከላከል፣ ቤተሰብን በስራ ከማገዝ፣ ከመዝናናት፣እንዲሁም ከማንበብ በተጨማሪ ጊዜያችሁን በግቢያችሁ ውስጥ ችግኝ በመትከል ማሳለፍ አለባችሁ።
ልጆች ባሳለፍነው አመት እንደምታስታውሱትና ብዙዎቻችሁም እንደተሳተፋችሁ በሀገር ደረጃ በርካታ ችግኞች ተተክለዋል። በአንድ ጀምበር ከሁለት መቶ ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል በህንድ በአንድ ቀን በርካታ ችግኝ በመትከል ተይዞ የነበረውን ሪኮርድ የግላችን ማድረግ ችለናል። ባሳለፍነው አመት ከተተከሉ ችግኞች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት ጸድቀዋል። ማለትም ከተተከሉ መቶ ችግኞች ውስጥ 84ቶቹ ፀድቀዋል እንደማለት ነው። በዚህ አመትም በርካታ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀዋል። ሁለተኛው ብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ግንቦት 28 በይፋ ተጀምሯል። እናንተም በክረምቱ የእረፍት ወቅት በደጃችሁ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራችሁን አሳርፉ።
ዘንድሮ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል አብዛኞቹ ለምግብነት የሚውሉ ናቸው። ይህ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲኖረው ያደርጋል። በኢንዱስትሪዎች ብዛት እና በንፁህ አየር እጥረት የተነሳ ዓለም ከባድ ፈተና ተጋርጦባታል። ችግኞችን መትከል ደግሞ የሳሳውን ደን ለመመለስ ይጠቅማል። ችግኞች በተተከሉ ቁጥር የአፈር መንሸራተትና ጎርፍ ይቀንሳል። ለም አፈርም በጎርፍ እንዳይወሰድ ያደርጋል። ችግኝ ለሰውም ለእንሰሳውም ህይወት ወሳኝ ነው። ስለዚህ ሁላችሁም ችግኝ መትከል አለባችሁ።
ችግኝ በመትከል የተራቆተውን የሀገራችንን የደን ሽፋን ማሳደግ ይጠበቅባችኋል። አሻራችሁን በማሳረፍ የወቅቱ ‹‹የአረንጓዴ ልማት›› አካል ሁኑ። በቀላሉ የወዳደቁ እቃዎችን በመጠቀም በዋናነት ከረጢት፣ ፕላስቲክና ቆርቆሮዎችን አፈር በመሙላት እንደ ቃሪያ፣ ቆስጣ፣ ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ካሮት የመሳሰሉ ተክሎችን ማሳደግ ትችላላችሁ። ችግኞችን በግቢ ውስጥ ተክሎ መንከባከብና ማሳደግ ከቻላችሁ ደስ የሚል የመንፈስ እርካታ ታገኛላችሁ። በብዛት እቤት በመዋል በሚመጣ ድብርት አትጠቁም። እንዲሁም ንጹህ አየር ትተነፍሳላችሁ። የመኖሪያ አካባቢያችሁ ይበልጥ ያማረ ይሆናል።
በጠባብ ቦታ ላይ ችግኞች ተክላችሁ ማሳደግና መጠቀም ከቻላችሁ ሽልማት ትሸለማላችሁ። እናንተም ተሸላሚ ለመሆን ከዛሬ ጀምራችሁ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ጀምሩ። እቃዎችን በስፋት አዘጋጁ ከዚያ የምትፈልጉትን የችግኝ አይነት ቤተሰቦቻችሁ እንዲያመጡላችሁ ጠይቋቸው። ከዛም በመትከል ጠዋትና ማታ ውሃ እያጠጣችሁ ተንከባከቧቸው።
ልጆች !እንዴት መትከልና መንከባከብ እንዳለባችሁ በትክክል ካላወቃችሁ ደግሞ ቤተሰቦቻችሁን ጠይቁ። የምትተክሏቸው ችግኞችም ቅጠላቸው፣ ስራቸውና ፍሬያቸው ለምግብነት የሚውል መሆኑን እንዳትረሱ። ችግኝ መትከል አካባቢን ከማስዋብ በተጨማሪ ንጹህ አየር እንድንተነፍስ ያደርጋል። መልካም ቀን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ሞገስ ፀጋዬ