አንዳንድ ሰዎች ስም ማውጣት ያውቁበታል። ለአንዱ ልጃቸው የአያቱን ወይ የቅድመ አያቱን ስም ማስታወሻ ብለው ይሰጡታል። ለአንዳንዱ ደግሞ ከሚመኙት ተነስተው ስም ያወጡለታል። ሀብትን የናፈቁ በልጃችን እንኳ ያሉ በድህነት የሚኖሩ ቤተሰቦች ልጃቸውን ‹‹ሀብታሙ›› ብለው ይጠራሉ። የተመኙት ይደርሳል… ይባል የለ። ይሄ እንዲሆንላቸው በመመኘት ነው። ሁልጊዜም በጭቆና ተረግጦ መግዛትን እንደ ጥሩ ነገር ይለመድና የሚወለደው ልጃቸው እነሱ የደረሰባቸው ፣ እነሱ እንዳዩት የአፍሪካ መሪ እንዲሆንላቸው በማሰብ ‹‹ዘላለም ግዛው›› ብለው ስም ያወጡለታል። ‹‹ንጉስ ሁናቸው፣ጌታቸው፣ደምመላሽ … ›› ሌላም ሌላም ስሞች የሚያወጡት እንግዲህ እንደየሰው ምኞት፣ ፍላጎት፣ በቀል እና ውስጥ ነው። ልጅ አላድግ ያላት እናት ያገኘችውን ፍሬዋን ‹‹ማስረሻ ፣ ብዙነህ ›› ብትለው ውስጧን ነው።
መውለድ ሲዘገይ ‹‹ጽናት›› ሲሉ ያወጡት፣ ሴት እየተመኙ ወንዱ ሲደረደር የተገኘችን ‹‹የትነበርሽ›› ፣ ከእርግዝና እስከ መወለዱ ቢያስቸግር ‹‹አስጨናቂ›› ብለው የጠሩ ፤ ለምታጠባው እናት እንኳን ሀይለኛነቱ አልመለስ ቢል ‹‹ በሀይሉ›› ብለው ስም ሰጡ። እንዳው ለወጌ መነሻ ብዬ እንጂ ስም ከነገጠመኙ ከነምኞቱ ብዘረዝር ምናልባትም የቦታ ጥያቄ ጥያቄ ሆኖ ያስቆመኝ ይሆናል። ግን እዛም ሳልደርስ ቆም ላድርገው፤ ግን ግን አንድ ሳላነሳ የማላልፈውን ስም ‹‹ሰርተሽኩሪ›› ይህን ስም ስሰማ ምን አይነት ቤተሰቦች ይሆኑ ? ጠይቄ ልደርስበት ባልችልም እኔ ግን የስራ ሰዎች፣ ሙስናን የሚጠየፉ፣ የወንድ እጅ አትይ ብለው ለልጃቸው ስም የሰጡ ይመስለኛል። ይሄ ግምቴ ነው።
ግን እኮ ስምን መላክ ያወጣዋል የሚል አባባል አለ። ይሄንን አንርሳ ። አሁን አሁን ግን ስምን ሰይጣን ያወጣዋል ብዬ ማሰብ ጀምሬያለሁ።ያለምክንያት ግን አይደለም። ቅን ልቡና፣ ብሩህ አእምሮና ፍቅር የራቀው ሰው ስም የሚያወጣው በሚያየው፣ እንዲሆንለት በሚፈልገው መልካም ነገር ብቻ አልመስል አለኝ። እንዳው ስም አጥፊ ለመሆን በማሰብ ብቻ የሚወጡ ስሞች አሉ።
የአንዳንዱ አስተዳደግ ሁሌም ከጎረቤት ጋር በድንበር፣ እግዜር በሰጠ ዝናብ ጎርፍ ፣ በልጅ፣ በውሻ፣ … መጋጨትን ደሙ ያደረገ ነው። መልካም ማሰብን ትቶ ክፋትን ሲያነግስ፣ ጥበብን ሳይሆን ሰይጣንን ሲያማክር ያድራል ፤ ይከርማል። እና በየደረሰበት ያየውን መልካም ነገር አፈር ከድሜ ያስገባል። ማንም ይስራው ማን ለሀገር የተሰራ ነገር የሀገር መሆኑን ይዘነጋል። አንቶኔም እንቶኒትም አልፈው ቀሪው የሀገር መሆኑን ይረሳል። ወይ አሻራ ብሎ ይብከነከናል፣ ይትከነከናል።
ዛሬ ስንቱ እየተጠቀመበት ነገም ልንጠቀምበት እንደምንችል ሳያስብ ለመቃወም ብቻ ይቃወማል። ሆዱ እያወቀ ዓይኔን ግንባር ያድርገው፣ ይሄ ‹‹ቀለምና አበባ›› ነው ብሎ ይከራከራል። መከራከሩ ደግ ቢሆንም ያልሆነን ነገር ሆኗል ብሎ ለማሳመን መመከሩ አመዛዛኝ ራስ ያለው አለና ኧረ ያስተዛዝባል።
አንድ ጊዜ አንድ ሰው በጣም በሰዎች ተወደደ አሉ። እሱ ሲደርስ ጎንበስ ቀና የሚሉ እጅ አንስተው የሚያጨበጭቡ በዙ። እሱም ስመ ጥሩ ስራ ብዙ ሆነ። በዚህ የተበሳጩ አለቃው ‹‹ ዘጠኝ ድስት ጥዳ አንዱንም የማታማስል›› ብለው ወረፉት አሉ። አሁን ግን የምናየው ከግምትም በላይ የሚገርም፣ የሚደንቅ ደግሞ የሚያስመሰግን ነው። ግን ስም ወጣለት ‹‹ ቀለምና አበባ››። ይሄኔ ነው ማለት ተግባርና ስም ለየቅል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
አልማዝ አያሌው