እሁድ በጉጉት የምጠብቀው የእረፍት ቀኔ ነው። ተኝቶ ማርፈድ ፈልጌ ነበር። ንጋት ላይ የመነሳት ልማዴ ሳልፈልግ ቀስቅሶኛል። አይኔን መግለፅና ከአልጋ መውረዱ ግን ፈፅሞ አላሰኘኝም። ዛሬ ከልቤ ሰው ጋር ቀጠሮ አለኝ። ከዚህ በፊት የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ግንኙነት ቢኖረኝም የወንዶችን ታማኝነት አብዝቼ እጠረጥራለሁ።
ከአንድም ሁለት ጊዜ እምነት በማጣት የተለየኋቸው የወንድ ጓደኞቼ ወንዶች ላይ ሙሉ ዕምነት እንዳይኖረኝ አድርገውኛል። የሚገርመው ግን ሙሉ በሙሉ ከውስጤ ይሄንን ጥርጣሬዬን ማስወገድ ባልችልም ሰሎሞንን ከተዋወቅኩት ወዲህ በመጠኑም ቢሆን ቀንሶልኛል።
በጓደኛዬ ሳምራዊት አማካኝነት የተዋወቅኩት ሰሎሞን እየተላመድኩት ነው። ከተዋወቅን ቅርብ ጊዜ ቢሆንም ከሌሎች ወንዶች የተሻለ መሆኑን በብዙ ነገሩ እያሳየኝ ነው። በእረፍት ሰዓትና ከስራ ስወጣ እሱን አግኝቼ ከእርሱ ጋር ማሳለፍ መውደድ ጀምሬያለሁ። ሰሎሞን የምፈልገው አይነት ወንድ ሆኖ ስላገኘሁት ውስጤ እየተቆጣጠረው ሳይሆን አይቀርም።
በተንጋለልኩበት ስለሱ ብዙ እያሰብኩ የእጅ ስልኬ የአንሱኝ ጥሪዋን አሰማችኝ። የደዋዩ ማንነት ከማየት በፊት ሰዓቱ የማወቅ ጉጉት ስለነበረኝ ለማንሳት እየተዘጋጀሁ ሰዓቱን ተመለከትኩ። ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ይላል። እናቴ ናት የደወለችው። ስራም ጀምሬም ከእናቴ ጋር ለረጅም ጊዜ አብሪያት ቆይቻለሁ። የማስተምርበት ትምህርት ቤት ስለሚርቅና እኔም ህይወትን መልመድ አለብን ብዬ በማሰቤ ተከራይቼ ከወጣሁ አንድ ዓመት አልፎኛል።
“ሀሎ እማ እንዴት አደርሽ ሰላም ነው?” ከወዲያ የስልኩ ጫፍ ደከም ባለ ድምፅ “እንዴት ነሽልኝ ልጄ?” የሚል ድምፅ ሰማሁ። እናቴ ድምፅዋ ሲለወጥብኝ ምን እንደሆነች በመጠየቅ ወተወትኳት። “ልጄ ከትላንት ጀምሮ ትንሽ አመም አድርጎኛል። ” “እ ምንድነው እማ ምን ሆንሽብኝ ሀኪም ሄድሽ ታዲያ” ህመም ቢፀናባትም እንኳን ሀኪም መጎብኘት አትወድም እናቴ። ደግሞም ልሂደ ብትል ብቻዋን ናት ከማን ጋር ልትሄድ ትችላለች።
በፍጥነት ከቤቴ ወጥቼ እናቴ ጋር ስደርስ እጅግ በጣም ደክማ አገኘኋት። ደነገጥኩ ከታመመች ሳምንት እንዳለፋትና አንዴ በራስዋ በትግል ሲብስባት ሀኪም ቤት ሄዳ እንደነበር ነገር ግን እንደተባባሰባት በደከመ አንደበትዋ ስትነግረኝ ሳላስበው ካይኔ እንባ ተፍለቀለቀ። በራሴ ጉዳይ ሄጄ ደጋግሜ ደውዬ አለመጠየቄ ጉዳትዋን ሳይ ተፀፀትኩ። በቀበሌ ቤት ውስጥ የምትኖረው እናቴ በግቢያችን ውስጥ ያለች አንድ ክፍል ቤት አከራይታ የምግብ ወጪዋን ትሸፍናለች። የቤቱ ኪራይ ገቢ አብቃቅታ በትግል ትኖራለች።
በላዳ ታክሲ ወደ ሀኪም ይዣት ልሄድ መንገድ ጀመርን አቅራቢያ የሚገኝ አንድ የግል ሀኪም ቤት ጋር ስንደርስ ባለ ላዳው “እዚህ ነው አይደል?” ብሎ ከኔ ምላሽ ሳይጠብቅ ከመንገድ ዳር ወዳለ አንድ ግል ሆስፒታል ግቢ ይዞን ገባ። ከቤቴ ስወጣ ያላሳሰበኝ አንድ ጉዳይ ማሰብ ጀመርኩ። የወሩ መጨረሻ ላይ ስለሆንኩ እጄ ላይ ያለው አንድ ሺ ብር ብቻ ነው። እሱም የታክሲ ሲቀነስ ይጎላል።
እናቴን ደግፌ ከታክሲው ሳወርዳት በግማሽ ልቤ ፀሎት ላይ ነበርኩ። አንድ ነገር ላይ ተስፋ አድርጌያለሁ። ምርመራው ከዚህ አይበልጥም መቼም መድሀኒት ቢያዙላት ከወጣሁ በኋላ ስለሚሆን ሌላ ሰው ጋር ለመደወል ወስኜ በትንሹም ቢሆን ተረጋጋሁ። ለባለታክሲው 100 ብር ሰጥቼ ካርድ በማውጣት እናቴን በተሽከርካሪ ወንበር አድርጌ እየገፋሁ ወደ ምርምራ ክፍል አመራሁ። ሀኪሙ የሚሰማትን ስሜት በደንብ ጠይቋት እና ካየው ምልክት በመነሳት ተጨማሪ የላቦራቶሪ ምርመራ እንዲደረግላት ወረቀት ጽፎ ሰጠኝ።
ለላቦራቶሪ ምርምራ ክፍል 100 ብር ብቻ ቀረኝ፤ ይበልጥ መጨነቅ ጀመርኩ። ቀጣይ የሚሆነው ነገር ሳስብ ሀሳብ ገባኝ። ምን አልባት ካሁን በኋላ ውጤቱን አይተው መድሀኒት ቢያዝላት ነው። መድሃኒቱ ደግሞ እቤት ይዣት ከሄድኩ በኋላ ከሰው ተበድሬ ልገዛ እችላለሁ የሚል ተስፋ በውስጤ አሳደርኩ። ዶክተሩ የላቦራቶሪ ምርመራውን ከተመለከተ በኋላ እናቴን አንዳንድ ጥያቄዎች ይጠይቃት ጀመር። ምርመራው እንዳላበቃ ገባኝ።
ዶክተሩ በድጋሚ ‘ሲቲ ስካን’ መነሳት እዳለባት ነገረኝ። በዚህ ሀሳቦች ተደራርበውብኝ ጭንቀት ውስጥ ወደኩ። በአንድ በኩል የእናቴ ህመም ከባድ መስሎ ታየኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለተባለው ምርምራ የሚሆን ገንዘብ የለኝምና የማደርገው ጠፋኝ። እናቴን አንድ ጥግ በተቀመጠችበት ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ትቻት የታዘዘው ምርምራ ክፍያ ስጠይቅ 2500 እንደሆነ ተነገረኝ።
ቆሜ ብዙ አሰብኩኝ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋባሁ። ሰሎሞን ጋር ለመደወል አሰብኩ። የእርሱም ገቢ ከእጅ ወደ አፍ ነውና ላስጨንቀው አልፈለኩም። ሳምራዊት ጓደኛዬ የኮሌጅ ተማሪና ምንም ገቢ የላትም። ሌላ ሰው ሳስብ በፍፁም ብር ሊሰጠኝ የሚችል ሰው አልታሰብሽ አለኝ። በእጄ የያዝኩት ስልክ በድምፅና ንዝረት እንዳነሳው አመለከተኝ። ሰሎሞን ነው።
“ሀሎ ሰላምዬ እንዴት ነሽልኝ?” አልኝ። የመገናኛ ሰዓታችን ሲቃረብ ነበር የደወለው። ስላለሁበት ሁኔታ ሁሉ ነገርኩት። በዝምታ ትንሽ ቆየና ያለሁበት ሆስፒታል ጠይቆኝ ስልኩን ዘጋው። ሰሎሞን ብር እንደሌለው ባውቅም፤ ጭንቀቴ ተረድቶ አንዳች ነገር ይዞ ይመጣል በሚል ተስፋ አደረብኝ።
በተስፋ እየጠበኩ 30 ደቂቃ አለፈ። 40 ደቂቃ እንደ ቀልድ እዚያው ሄኜ አለፈ። የሰሎሞን መቆየት ግራ አጋባኝ። ስልኬን አንስቼ ደወልኩለት “ይቅርታ አሁን የደወሉላቸው ደንበኛ ስልክ ጥሪ አይቀበልም” ደጋግሜ ደወልኩ በድጋሚ ስልኩ መዘጋቱ የሚነግር ድምፅ ብቻ ነው የሚሰማው።
ግራ ተጋባሁ ሰሎሞን ምንድነው የሚሰራው? ለምን ስልክ ይዘጋል። ተስፋ ሰጥቶኝ አስጠብቆ ስልኩን ከሚዘጋ ለምን አልችልም አይለኝም። ብዙ ቀባጠርኩ። እናቴ አጠገብ ሄጄ በሙሉ አይኔ ላያት ፈራሁ ተመልሼ ተሸሽጌ ፈዝዤ ብዙ ቆምኩ። ለሰለሞን ከደወልኩለት 55 ደቂቃ አለፈ።
ሰለሞን የሚባል ሰው ብቻ ሳይሆን ስሙም አስጠላኝ። አጋሬ ያልኩት የተማማንኩበት ሰው በዚህ ችግር ውስጥ መሆኔን እየነገርኩት ስልክ ዘግቶ ጠፋብኝ። ወንድ የሚባል ፍጥረት ጠላሁ። በቆምኩበት ቦታ አምርሬ አልቅሼ ሲወጣልኝ እናቴን ከዚያ ይዣት ወጥቼ እቤት ወስጃት ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ወስኜ ይዣት ወደ በሩ አመራሁ።
እናቴን ይዤ ከሆስፒታሉ በር አለፍ ብዬ ስወጣ ከፊት ለፊቴ ሰሎሞንን ወደኔ ሲጠጋ አየሁት። “ይቅርታ ሰላምዬ ቆየሁ ታክመው ጨርሳችሁ ነው? ብር ፍለጋ ስኳትን ቆየሁ” አለመታከምዋን ስነግረው ብር እንዳመጣ ሲነግረኝ መልሰን ይዘናት ገብተን ሙሉ ምርምራውን ጨርሰን መድሀኒት ታዞላት ከሀኪም ቤት ስንወጣ ጠየኩት። በጥርጣሬ እየሁት “ለምን ግን ስልክህን ዘጋህ?” መመለስ አልፈለገም ወተወትኩት ደጋግሜ ጠየኩት። ሳይወድ ነገረኝ። ስልኩን ሽጦ ገንዘቡን ይዞ እንደመጣ ሲነግረኝ በራሴ አፍርኩ። አንገቴን ቀና አድርጌ ላየው ከበደኝ። ይሄን መልካም ሰው በክፉ ማሰቤ አሳፈረኝ። ተፈፀመ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ተገኝ ብሩ