ህይወት ሁለት መንገድ አላት።አንዱ የፍቃድ ሁለተኛው የግዳጅ። የመጀመሪያው ነፃነት የምታጎናፅፍበት መንገድዋ ነው። ይሄን መንገድ ለፈቀደችለት ፍቃዱን ሞልታ የወጠነው ህልሙ እንዲያሳካ ምቹ መደላደልን ታበጃለች። ሁለተኛው እርስዋ ባሻት መልኩ ያለ ሰው እቅድና ምኞት ከፈለገቸው የምታስጉዝ።የመጀመሪያዎቹ እድለኞች ናቸው።ምክንያም ለምኞት የቀረበ መንበር ላይ የተቀመጡት ጥቂት ዕድለኞች ብቻ ናቸው።እነርሱ ፍቃዳቸው ሙሉ ሆኖ መሻታቸው ተሟልቶ ይቀርብላቸዋል።
የዛሬዋ የዝነኞች አምድ እንግዳችን ህይወት ፈቅዳ ምኞትዋን ያሰመረችላት፤ የልጅነት ህልሟን ያሳካች፣ መሆን የምትፈልገውን ሆና የተገኘች ናት። ለህዝብ ባቀረበቻቸው በርካታ ዜማዎች አድናቆትና ዝናን አግኝታለች። በሳል የሙዚቃ ባለሙያዎች አሳትፋ የምትሰራቸው ሙዚቃዎችዋ ለወራት በከፍተኛ ደረጃ በብቸኝነት በመደመጥ ተወዳጅ ሆነው ዘልቀውላታል። በተለይ “የናፍቆት ዜማ” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበምዋ በብዙ አድናቂዎችዋ ልብ ውስጥ ጠልቀው የተሰሙ ስራዎችዋ የተካተቱበት ነበር።
“ ካለህበት ፍቅሬ ካለህበት ውዴ ካለህበት
ልፈልግህ ልልፋ ልንከራተት ውዴ ካለህበት…”
አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ ተወልዳ የልጅነት ውብ ጊዜዋን ያሳለፈችበት ሰፈር ነው። ያደገቸው ዝነኛና ተወዳጅዋ ድምፃዊት ሀሊማ አብዱረህማን።ልጅ ሆና ትመኘው የነበረ ዘፋኝ ሆኖ ውስጣዊ ስሜት በሙዚቃ የመግለፅ ህልሟን የምትሰማቸው ዘፈኖች መለሳ ደጋግማ በመዝፈን ወደ ሙዚቃው ቀረበች። እጅግ የምትወዳት ጓደኛዋ ከታዋቂው የሙዚቃ ሰው ሞገስ ተካ ጋር ለመገናኘት ምክንያት ሆነቻት።ለብዙ ድምፃዊያን የግጥምና የዜማ ምንጭ የሆነው ሞገስ ተካ ለሀሊማ የሚዚቃ ጅማሮ ብርታትና ረዳት ሆናት።
በስራቸው እጅግ የምትወዳቸው ድምፃዊያን ሙዚቃዎችን የነፃነት መለሰ፣ የሀመልማል አባተና የፍቅርአዲስ ነቅዓጥበብን ሙዚቃዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተጫወተች ቆይታ የራስዋን ስራ ለህዝብ አቅርባ ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘች።
የድምፃዊዋ የእረፍት ውሎ
“እስቃለሁ እስቃለሁ… እስቃለሁ እኔ ስካለሁ…
ከእንግዲህ አታልቅስ አይኔ… ሰቀቀን ጭንቁ ለምኔ ” ሳቅ እራሴን የማዝናናበት ልዩ ስጦታዬ ነው ትላለች ሰዎችን ስትቀርብ በፈገግታ ተሞልታ መልካም ድባብን መፍጠር የሚቀላት ሀሊማ ፈገግታ መለያዋ ነው።የዕረፍት ሰዓትዋን ከቤተሰብዋ ጋር ቤት ውስጥ ማሰለፍን ታዘወትራለች። ቤተሰባዊ ፍቅርን የሚያሳድጉ ጥምረትን ይበልጥ የሚገነቡ ተግባራት በቤት ውስጥ ቆይታዋ ትከውናለች።መልካም ነገሮችን እያነሱ መወያየት ቤተሰባዊ ጨዋታ የእረፍት ሰዓትዋ ዋነኛ መቆያዎቿ ናቸው።
ከከተማ ወጣ ብላ ተፈጥሮን እያዩ መደሰት፤ ታሪካዊ ቦታዎች መጎብኘት የእረፍ ሰዓትዋን አስደሳች የሚያደርጉላት ተጨማሪ ተግባራቶቿ ናቸው። ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የምትችለው ሀሊማ ከቤተሰቦችዋ የተረፋትን ጊዜ ከምትወዳቸው ጓደኞችዋ ጋር በመልካም ሁኔታ ማሳለፍንም ትመርጣለች።
በማህበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊም ናት።የታመመን መጠየቅ ከጓደኞችዋ ጋር በመሆን የተለያዩ የበጎ አድራጎትና መልካም ተግባራት ስራዎች ላይ ትሳተፋለች። በዝና ምክንያት የሚያጡት ነፃነት ሀሊማ ጋር ተትረፍርፏል። ከሰዎች ጋር በቀላል የመላመድ ባህሪዋና ጉዳዮችን አቅልላ ማየትና አለማካበድዋ በነፃነት ለመንቀሳቀስ ጠቃሚ ስንቅ ሆኗታል።
ሳይበዛ የምትዘነጥባቸው ከማህበረሰቡ ዘንድ በአብዛኛው ቅቡልነት ያለው አለባበስን ታዘወትራለች። ከገበታዋ አዘውትራ ባታጣው ደስ የሚላትና ከምግቦች ልዩ ፍቅር ያላት ገንፎ ነው።ለዚህ ምግብ ካላት ፍቅር የተነሳ ቁርስ ምሳና እራት ደጋግማ የበላችብትን ጊዜ አትረሳውም።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚፈለገው እድገት ላይ መድረስ ይችል ዘንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል። ለዚህም አብሮ በመስራ የነጠሩና ተሰሚነታቸው የጎላ ስራዎች ማበርከት ይቻላል በማለት በሙዚቃው ኢንዱስትሪው ላይ አስተያየትዋን ትሰጣላች። በግልዋ ወደፊት የተሻለ ስራዎችን ለህዝብ አቅርባ በዘርፉ የራስዋን ሚና ለመወጣት በመትጋት ላይ ትገኛለች።
መልዕክት
“አሁን ያለንበት ወቅት ለሁላችንም ከባድ ጊዜ በመሆኑ አብረን መቆምና የመጣብንን አደጋ በጋራ መመከት ይኖርብናል። ሁሌም ያለመዘናጋት ኃላፊነታችን እንወጣ። ስለምንወዳቸው ቤተሰቦቻችንና ሰዎች ብለን እራሳችንን እንጠብቅ። እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው የታመሙ ወገኖቻችን በማከም ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን ትልቅ ክብር ልንሰጥ ይገባል። እኛም በመጠንቀቅ የእርነሱን ስራ እናቅልል። ተስፋ ሳንቆርጥ የጠንካራ የመከላከያ ስራ ከሰራን ነገ መልካም የሆነች ሀገር እናያለን።” በማለት በዚህ ወቅት የገጠመንን ፈተና የምንሻገርበት የጥንቃቄ መልክት ለኢትዮጵያዊያን ወገኖችዋ አስተላልፋለች። እኛም ስለ አገር መዳን ብለን እራሳችንና ወገኖቻችንን ከአደጋው እንጠብቅ ማሳረጊያ አደራችን ነው። ቸር ያቆየን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ተገኝ ብሩ