ቢቢሲና ዘጋርድያን ሰሞኑን ይዘው የወጡት ዘገባ እንዳመለከተው ፤ በዓለም የቡና ዝርያዎች ላይ የተካሄደው የመጀመሪያው ሰፊ ጥናት በእንግሊዙ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ሳይንቲስቶች ለህትመት በቅቷል፡፡ ጥናቱ ከ124 የቡና ዝርያዎች 60 በመቶው በመጥፋት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
ሳይንቲስቶቹ በጥናታቸው እንዳስታወቁት፤ በዓለም በስፋት የሚጠጡትን ሁለት የቡና ዝርያዎች ጨምሮ 100 የቡና ዝርያዎች የሚለሙት በጫካ ውስጥ ሲሆን፣ እነዚህ የጫካ ቡና ዝርያዎች ከአየር ንብረት ለውጥና ከደን መመናመን ጋር በተያያዘ በመጥፋት አፋፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ የጫካ ቡና ዝርያዎች በመጥፋት አፋፍ ላይ መገኘት አስደንጋጭ እንደሆነ የሚናገሩት ሳይንቲስቶቹ ፣የጫካ ቡና የዓለም የቡና ሰብል መሰረት መሆኑ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት ከፍተኛ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ጥናቱ በ124 ታዋቂ የቡና ዝርያዎች ላይ ተመስርቶ የተካሄደ ሲሆን፣ ጥናቱ የተካሄደውም አደጋ የተጋረጠባቸውን ዝርያዎች እየለየ በቀይ መዝገብ ውስጥ ለሚያሰፍረው ለዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ህብረት ሥራ ነው፡፡ በዚህ ግኝት መሰረትም የኮፊ አረቢካ የጫካ ዝርያ በአሁኑ ወቅት ሊጠፉ የተቃረቡ ከሚባሉት ዝርያዎች ዝርዝር መካከል ተመድቧል፡፡
ጥናቱ እንዳመለከተው፤በአሁኑ ወቅት 75 የጫካ ቡና ዝርያዎች ለመጥፋት ተቃርበዋል፡፡ 35ቱ ለእዚህ አደጋ ያልተጋለጡ ሲሆን፣ስለተቀሩት 14 የጫካ ቡና ዝርያዎች በዚህ ደረጃ ላይ ናቸው ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ መረጃ የለም፡፡ ከጫካ ቡና ዝርያዎች 28 በመቶው ብቻ ጥበቃ በማይደረግባቸው አካባቢዎች የሚለሙ ሲሆን፣ ከቡና ዝርያዎቹ ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው ዘራቸው በዘር ባንክ የተቀመጠው፡፡
የሮያል ቦታኒክ ጋርደኑ ሳይንቲስት ዶክተር አሮን ዴቪስ ‹‹ የጫካ ቡና ባይኖር ኖር ፣ዓለም በዚህ ወቅት ሊጠጣ የሚችለው በቂ ቡና ባልነበረ ነበር ›› ሲሉ አስገንዝበው፣ የዓለምን የቡና ልማት ታሪክ መለስ ብላችሁ ብትቃኙ ፣ቡናን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማልማት ወሳኞቹ የጫካ ቡና ዝርያዎች ናቸው›› ሲሉ የጫካ ቡና ዝርያን ሚና አመልክተዋል፡፡ ሊጠፉ ከተቃረቡት የቡና ዝርያዎች መካከል የወደፊቱ ቡናን ለማልማት፣ በሽታ የሚቋቋሙት እንዲሁም አስቸጋሪ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉት ይገኙበታል ይላሉ፡፡
ሌላው ሁለተኛው ጥናት በዓለም በስነ ህይወት ላይ IUCN እየተከሰተ ካለው ለውጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ዘገባዎቹ ያመለክታሉ፡፡ ጥናቱ ከጫካ ቡናዎች መካከል አንዱ የሆነው የአረቢካ የጫካ ቡና ክፉኛ ለአደጋ መጋለጡን ጠቁሟል፡፡ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለው ችግር ሲታሰብ አረቢካ ቡና ዝርያቸው የጠፋ እጽዋት ቀይ መዝገብ በመባል የሚታወቀው ሉሲን/ IUCN / መዝገብ ውስጥ ሊሰፍሩ ከተቃረቡ ዝርያዎች አንዱ ሊባል እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡
ሳይንቲስቶቹ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚለማው ይህ የአረቢካ ቡና /የጫካ ቡና/ እአአ በ2080 በ85 በመቶ ቅናሽ ያሳያል እንዲሁም አሁን ቡና የሚለማበት መሬትም እስከ 60 በመቶው በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ለቡና ተስማሚ ወደማይሆንበት ሁኔታ ይሸጋገራል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡
የዘጋርዲያን ዘገባ እንደጠቆመው፤ የአረቢካ ቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቡና ወጪ ንግድ ታላቅ ሀገር ስትሆን፣ በየዓመቱም አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡና ለውጭ ገበያ ታቀርባለች፡፡ 25 ሚሊዮን የሀገሪቱ ዜጎች ህይወትም ከቡናና ቡና ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ይህ የቡና ዓይነት ለገበያ ለሚመረተው ቡናም ሆነ ለሌላው የቡና እርሻ ወሳኝ መሆኑን ዘገባው ጠቅሶ፣ በዚህ የቡና ዝርያ ላይ የተደቀነው ስጋት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ጫና ያሳድራል ይላል፡፡
ጥናቱ መፍትሔዎችንም አመላክቷል፡፡ የቡናውን ዘርፍ ዘላቂነት ለማረጋገጥ የጫካ ቡና ልማትና አጠቃቀም ላይ መሥራት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በተወሰኑ ትሮፒካል ሀገሮች በተለይ በአፍሪካ ላይ ወሳኝ ሥራዎች በአስቸኳይ መከናወን እንዳለባቸው አስገንዝቦ፣ይህም የነገውን ቡና ለመጠበቅ እንደሚያስችል ያመለክታል፡፡
የጥናት ቡድኑ አባል ዳቪስ የቡናን ዝርያዎች ለመጠበቅ የሚረዱ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም የጫካ ቡናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ አሠራሮች እንዳሉም ይናገራሉ፡፡
ዳቪስ በቀጣይም የተጠናከረ ተግባር መከናወን እንዳለበት ጠቅሰው፣የዘር ባንኮችን መጠቀም ከረጅም ጊዜ አኳያ ጠቃሚ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የቡና ደረጃዎችን ማውጣት እንዲሁም የምስክር ወረቀት አሰጣጡንም ከደን ጥበቃ ጋር ማቆራኘት እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የአካባቢ የአየር ንብረት፣ የቡና እና ደን መድረክ ከፍተኛ ተመራማሪውና አማካሪው ዶክተር ታደሰ ወልደማርያም የደን መመንጠሩ ላለፉት ሠላሳ እና አርባ ዓመታት መታየቱን፣የአየር ንብረት ለውጡም እንደሚታወቅ ይናገራሉ፡፡ አየሩ በደረቀ ቁጥር ለቡና ያለው ምቹነት እየቀነሰ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ይህን ችግር እያየን ከተቀመጥን ጥናቱ ያመለከተው ስጋት በእርግጥም ስጋት ይሆናል ይላሉ፡፡ ዕርምጃዎች ከተወሰዱ ግን ስጋቱ እንደማይኖር ይጠቁማሉ፡፡
ስጋቱ ስጋት የሚሆነው የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል ምንም ዓይነት ጥረት ካልተደረገ ነው የሚሉት ዶክተር ታደሰ፣ ከዚህ አንጻር እየተደረገ ያለው ጥረት ከቀጠለ ስጋቱ መልካም አጋጣሚ ይዞ እንደሚመጣም ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ታደሰ ገለጻ፤ የአየር ንብረት ለውጡ ቡና አሁን ከሚለማበት ከፍታ ወደ ላይ ወደ ሰሜንም እንዲሰደድ ሊያደርግ ይችላል፡፡ቡናው የሚበቅልበትን ቦታ ወደ ከፍታ ቦታ ማዘወር ከተቻለ ፣ቡናው አሁን ባለበት ቦታ ላይም የተለያዩ የማኔጅመነት ስራዎች ከተከናወኑ እንዲሁም ደን እንዳይመናመን ከተደረገ ፣ለቡና የሚያስፈልገው የጥላ ዛፍ መጠን እንዳይቀነስ የሚያደርጉ ሥራዎችን ከተሠሩ ስጋቱ በቁጥጥር ይውላል፡፡
ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ስጋት የተባለው ለእኛ ስጋት ሳይሆን መልካም ዕድል ነው ያሉት ዶክተር ታደሰ፣ ቡና በሚመረትበት ስፍራ ላይ አስፈላጊው የልማትና እንክብካቤ ሥራ ከተከናወነ የቡና ምርትን በአራት አጥፍ ማሳደግ የሚቻልበት ዕድል እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ በኩል መንግሥት ብዙ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ሃሳቡ እንዳለው ዶክተር ታደሰ ጠቅሰው፣ የተለያዩ ተቋማት በቅንጅት መሥራት አስፈላጊነትንም ያመለክታሉ፡፡ በቡና ልማት ላይ የሚሠራው መስሪያ ቤትና በደን ላይ የሚሠራው በቅንጅት ቢሠሩ፤ደኑ ሲስፋፋ ቡናም ከስሩ ቢተከል ቡና ወደ ደጋና የሚፈለገው አካባቢ ሊሄድ እንደሚችል ይናገራሉ፡
እስከ አሁን ሁሉም በየዘርፉ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ግብርናም የራሱን የደንና አየር ንብረት ዘርፉም ደኑን ብቻ እንደሚመለከት ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ የደን ባለሙያዎች ቡናን የደን ጠላት አድርገው ይመለከታሉ ያሉት ዶክተር ታደሰ፣ ‹‹በኛ ሀገር ሁኔታ ሲታይ ቡና ያለበት አካባቢ ደን አለ፡፡ ይህም ቡና ለደን መቆየት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ያመለክታል፡፡ የደን መመናመን ሊኖር ይችላል እንጂ ለደን መመንጠር ቡና አስተዋጽኦ አያደርግም›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ግብርናዎች ቡናን ለማልማት ጥረት ሲያደርጉ ደንን ለመንከባከብ ያለው የልህቀት ማዕከሉ ያለው በኮሚሽኑና በተዋረድ መስሪያ ቤቶች ነውና በተናጠል ቢሠሩ የተሟላ ሥራ መሥራት አይቻልም ይላሉ፡፡ ቡና የሚተክሉት የጥላ ዛፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ይህ ግን የተሟላ እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ጥላ ዛፉ ምን ዓይነት ነው፤ የአካባቢው ስነምህዳርን ነባሮቹን ዝርያዎች የያዘ ነው ወይ የሚለውን ይይዛል›› የሚሉት ዶክተር ታደሰ፣ልማቱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚመለስ መሆን እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ፡፡ይህ ደግሞ በአንድ መስሪያ ቤት ለብቻ መሠራት የለበትም ብለዋል፡፡
አንዳንድ የቡና ዛፍ ጥላ ዛፎች ራሳቸወም የጥላ ዛፍ እንደሚፈልጉ፣ በተፈጥሮ ደኖች አካባቢ ብዙ ንጣፍ (ሌየር) ያላቸው ዛፎች እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ በጣም ረጃጅም እንዲሁም ከሥራቸው አነስ ያሉ ዛፎች እንደሚገኙ ይገልጻሉ፡፡ ይህን ዓይነቱ ሥራ በተቀናጀ መልኩ ቢከናወን ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው የጠቆሙት፡፡
እንደ ዶክተር ታደሰ ገለጻ፤ በሀገሪቱ በሥራ ላይ በሚገኘው አሳታፊ የደን አስተዳደር ላይም በተጠናከረ መልኩ መሥራት ይገባል፡፡ አስተዳደሩ የሚገለውን እየሞሉ መሠራት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የደን ጥበቃው ምን ይጎለዋል የሚለውን መመልከት ይጠቅማል፡፡ ጥበቃውም ቢሆን አሳታፊ ቢሆን ይመረጣል፡፡ አንዱ የሚጎለውን በሌላው አሟልቶ ቢሠራ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡
‹‹ይህን ዝርያ ለእኛም ለዓለም ቡና ኢንዱስትሪም ትልቅ ሀብት ነው›› ያሉት ዶክተር ታደሰ ፣ የኢትዮጵያ የቡና ዋጋ ሲተመን ቡናው ለአካባቢ ጥበቃ እና ለቡና ጀነቲክ ሀብት ያለው ፋይዳ መታየት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የገበያው መነሻ ይህ ነው ብለን ከፍ አርገን ዋጋ መጠየቅ ይኖርብናል፤ ገዥ አናገኝም ብሎ ዋጋ ዝቅ ማድረግ አይገባም፡፡ ከፍ አርገን ብንጠይቅም ለጣእሙ ስለሚፈልጉትና ምንም ምርጫ ስለሌላቸው ተመልሰው ይመጣሉ›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በአየር ንብረትና ደን ኮሚሽኑ በደን መጨፍጨፍ እና መመንጠር የሚወጣው ሙቀት አማቂ ጋዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ ፣ እንደሚሉት ኮፊ አረቢካ ቡና በጥላ ስር የሚያደግ ዝርያ ነው፡፡ የአጥኚዎቹ ስጋት ይመስለኛል የደቡብ ምዕራብ አካባቢ ደን ለመጥፋቱ ተጋልጧል ፡፡ ደኑ በብዝሃ ሕይወት የሚታወቅ ደን ነው፡፡ በአካባቢው የህዝብ ብዛትም አለ፡፡
የሕዝብ ብዛቱ አንደኛ የደኑን ስር እጽዋት ቀስ በቀስ በማጥፋት ቡና ይተክላል ፤ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀስ በቀስ በህገ ወጥ መንገድ ጣውላ ማምረት ውስጥ ይገባል፡፡ ስጋቱ ለዛሬ ሳይሆን የዛሬ ሃያ ዓመት በሙሉ ጥላዎች ከጠፉ ያለ ጥላ ሊለማ የማይችለው የአረቢካ ቡና አደጋ ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው፡፡ አረቢካ ቡና የትሮፒካል ፀሐይን ግማሽ ያህሉን / 50 በመቶውን/ ብቻ ነው ሊቋቋም የሚችለው፡፡ ስለዚህ ይህ የደን ውድመት ከቀጠለ ቡናው ጥላ ስር የሚያደግ እንደ መሆኑ ዛፎች ከጠፉ ማሳደጊያ ቦታም አይኖርም፡፡ ስለዚህ የደን ውድመቱ ለቡናችንም አደጋ ነው፡፡
‹‹በደኑ ስር ያለውን ብዝሃ ህይወት እየመነጠሩ ቡና ከስር መትከሉ ለእኔ እንደ ነቀርሳ ነው›› ይላሉ ዶክተር ይተብቱ፡፡ ይህም በሂደት ዛፉን ሊተካ የሚችለው እየታረመ የሚወገድ ከሆነ ትላልቆቹን ዛፎች የሚተካ አይኖርም፡፡ ይህም ለደኑም ስጋት ነው፤ ትላልቆቹ ዛፎች አርጅተው ሲወድቁ ደን አይኖረንም ማለት ነው፡፡ ይህም ሂደት ለደናችን ለብዝሃ ህይወታችን ስጋት ነው›› ይላሉ፡፡
የሚሠራው ሁሉ ስርዓት ካልያዘ ቡናውም ደኑም ብዝሃ ህይወቱም አደጋ ላይ ይወድቃል ያሉት ዶክተር ይተብቱ፡፡ ያንን አስበን በሬድ ፕላስ ፕሮግራም ደቡብ ምዕራብን መሰረት አድርገን በአሁኑ ወቅት አሳታፊ የደን አስተዳደርን ለመተግበር ሥራ ጀምረናል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ በተቻለ መጠን ማህበረሰቡን ማስተማር አለብን። ቦታውን እንዲከለሉ እና እንዲጠበቁ የማድረግ ሥራ እየሠራን ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ዶክተር ይተብቱ፣ የደን ጥበቃው በአሳታፊ የደን አስተዳደር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣እሱም ቢሆን ክፍተት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ለእኔ ህዝብን አሳትፈን እንጠብቀዋለን የሚለው ከድህነቱ ጋር በተያያዘ በጣም ደካማ መንገድ ነው፡፡ በማንም ላይ መፍረድ አትችልም››የሚሉት ዶክተር ይተብቱ፣ ደኑን መንግሥት ከልሎ የሚያስተዳድረው ከሆነ ሊተርፍ እንደሚችል ነው ያመለከቱት፡፡ መንግሥት በኃላፊነት ስሜት በደን አስተዳደር ላይ ኢንቨስት በማድረግ የተወሰኑ ደኖችን ለማዳን መሥራት እንደሚኖርበት ይጠቁማሉ፡፡
‹‹የእነዚህ ቡና ዝርያ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ነው ›› የሚሉት ዶክተር ይተብቱ፣እዚህ ላይ የዓለም ህዝብም ቡና ጠጪ ነውና በጥበቃው ላይ መሳተፍ እንዳለበት በመጥቀስ የዶክተር ታደሰን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ብዝሃ ህይወቱ በተቋማት መጠበቅ እንዳለበት ለዚህ የሚሆን ሀብት ሊገኝ እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል