በከተማዋ ከሚደረጉ የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች አንዱ የከተማ ግብርና ነው፡፡ዘርፉ ለከተማ ነዋሪዎች በምግብ አቅርቦት ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ፣ገቢ ማስገኛ በመሆን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓትን በማስተካከልና መሰል ችግሮችን ለማቃለል የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው፡፡ በተለይ በዘርፉ በቀላሉ እና በማንኛውም ሁኔታና ደረጃ ለማሰማራት አመቺ ነው፡፡
በተለያዩ የከተማ ግብርና ዘርፎች ተሰማርተው ለሚገኙና በቀጣይ መስራት ለሚፈልጉ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት፣የግብዓት አቅርቦት በማመቻቸት ፣የተለያዩ አገልግሎቶችን በተለይም እንስሳትን በሰው ሰራሽ ዘዴ የማዳቀል ፣የእንስሳት ጤናና ላብራቶሪ ምርመራ መሰል ማዕከላት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሥራዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም የነዋሪውን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ በስጋ ምርመራ ፣ በህገ ወጥ እርድ ቁጥጥር እንዲሁም በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የብቃት ማረጋገጥ ድጋፍ ይሰጣል፡፡እኛም ለዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ዳይሬክቶሬት እየሰራቸው ባሉ ሥራዎች ውስንነቶች እና ቀጣይ መፍትሄዎች ላይ ከዳይሬክቶሬቱ ተወካይ አቶ ተፈራ አብርሃ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በአቀረቡበት ወቅት አናግረናቸው ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
የዘርፉ አሳታፊነት
የከተማ ግብርና ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማስቻል ነባር ተጠቃሚዎችና አዲሶቹን ማጠናከር ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ተጠቃሚዎችን ብዛት 88 ሺህ በላይ ከፍ ለማድረግ ተችሏል፡፡ከዚህ ጎን ለጎን ሶስት ሺህ ሶስት መቶ በላይ ተጠቃሚዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ይህም በአሁኑ ወቅት በመዲናይቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ተብሎ ከተለየውና ችግሩን ለማቃለል ክፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ከሚገኝበት የሥራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በዘርፉ ያሉትን አካላት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ክትትልና ድጋፍ ወሳኝነት ስላለው ለ61 ሺህ ሶስት መቶ 99 ነባር ተጠቃሚዎች በልማቱ ለማስቀጠል ተችሏል። በዚህም ከመሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የቧንቧ ውሃ መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ሥራውን ያቋረጡ ተጠቃሚዎች ዳግም እንዲመለሱ ለማድረግ ያጋጠማቸውን ችግር ለይቶ መፍትሄ መስጠት ተገቢ ነው።
ዘርፉን ለማሳደግ
ዳይሬክቶሬቱ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራት ከፍ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። በከተማ ግብርና የሚመረቱ ምርቶች ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ለተጠቃሚዎች እንዲቀርቡ ያደርጋል። በዚህም ተደራጅተው እየሰሩ ላሉና ቀጣይ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የማዳበሪያ ፣ የሰብል ምርጥ ዘር ድጋፎችን እንዲያገኙ ያደርጋል። በሥራው ተጨማሪ መሬትንና እንስሳትን ወደ ተግባር በማስገባት ምርታማነቱ እንዲያድግም ሥራዎች ይሰራሉ። ከዚህ ጎን ለጎንም ከእነዚህ የምርት ግብዓቶች ሊገኝ የሚችለውን ምርት ከፍ እንዲል ለማስቻል በመስኩ ለተሰማሩ አካላት ድጋፎች ይሰጣሉ።
የግብዓት ውስንነቶችም ስለሚስተዋሉ ችግሮቹን ለማቃለልና ምርትን ለማሳደግ የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዲችሉ መንግሥት የተለያዩ አሰራሮችን ቀይሶ ይሰራል። የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ በማሳ ላይ የሚገኘውንና ከእንስሳትም በተመሳሳይ የሚገኘውን ምርት ከፍ ማድረግ ተችሏል።
የተገኙ ለውጦች
በመዲናዪቱ በተያዘው በመኸር እርሻ ምርት ዘመን አራት ሺህ አምስት መቶ ስምንት ሄክታር ማሳ በላይ በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተችሏል። ይህም በከተማ የሚገኘው ነዋሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከገጠሩ የአገሪቱ ክፍሎች ብቻ ይጠበቅ የነበረውን የምግብ አቅርቦት በማገዝ በምግብ ራሱን እንዲችል ያደርገዋል።
የአትክልት ልማት ሥራ በኩል ያለው እንቅስቃሴም እያደገ መጥቷል። ሶስት መቶ 73 ሄክታር ማሳ በአትክልት መስኖ የማልማት ሥራ ተሰርቷል። በማልማቱ ተግባር ላይም ሶስት ሺህ አንድ መቶ 59 ተጠቃሚዎች ለማሳተፍና ለማጠናከር ተችሏል። ከእነዚህ ተሳታፊዎችም መካከል አንድ ሺህ አንድ መቶ 23 የሚሆኑት ወጣቶች ሲሆኑ ይህም መንግሥት የወጣቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በዘርፉ የከተማዋን ነዋሪ በስፋት ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው በመኖሪያ ግቢና በተቋማት ክልል ውስጥ በሚገኙ ክፍት ቦታዎች እንደሆነ ይታወቃል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በግቢና በጓሮ አትክልት 33 ሺህ ሰባት መቶ 27 ተጠቃሚዎች በልማቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪን በማስገኘትና በአገር ውስጥም በተለያዩ ተቋማት ተፈላጊ የሆነውን የእንጉዳይ ምርትም ለማሳደግ ተጠቃሚዎችንም ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል።በመሆኑም ዳይሬክቶሬቱ 88 ተጠቃሚዎችን እያጠናከረና እየደገፈ ሲሆን ከእነዚህ በሥራው ላይ ከተሰማሩ አካላት ውስጥም 19 ወጣቶች ይገኙበታል።
በከተማ ግብርና ሌላው ዋነኛው ዘርፍ የእንስሳት እርባታ ነው። በዚህም 21 ሺህ ስድስት መቶ 67 ነባር ተጠቃሚዎች ተሳታፊዎች ናቸው። በተያዘው በጀት ዓመትም እንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ሥራ 12 ሺህ አንድ መቶ አምስት፣ በጫጩት ማሳደግ አንድ ሺህ አራት መቶ 83 ፣ በወተት ከብት እርባታ አራት ሺህ ሰባት መቶ 43፣ በዳልጋ ከብት ማድለብ ስምንት መቶ 55፣ በበግ ማድለብ አንድ ሺህ ሰባት መቶ 58፣ በማር ምርት ማሻሻያ ሥራ አምስት መቶ 59፣ በዓሳ እርባታ 27፣ በቆዳና ሌጦ ማሰባሰብ 78 እንዲሁም በእንስሳት መኖ ማቀነባበር 59 ማከናወን ሲቻል በእነዚህም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችና ተግባር ላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ለማሳተፍና ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል።
ለሥራዎቹ ስኬትም የአፈር ውሃ ልማት ጥበቃና የመስኖ ሥራ ወሳኝ እንደሆነ ዕሙን ነው። ዳይሬክቶሬቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በመተግበር ረገድ ሰባት ነጥብ 632 ኪሎ ሜትር ላይ ተሰርቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የእርከን ሥራ፣ ከማሳ ላይ የውሃ ማጠፍጠፍ 6 ነጥብ 4 ሄክታር ተግባራዊ ተደርጓል። ለመስኖ ልማት ሥራም አጋዥ የሆኑ ተግባራት መካከል ስድስት ኩሬ ቁፋሮ፣ 28 ሄክታር አነስተኛ መኖ ልማት ማስፋፊያ እንዲሁም 17 የመስኖ ጥገናዎችን በማድረግ የከተማውን ግብርና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተችሏል።
ዘርፉ በዋናነት በቀላሉ ሊሰራ የሚችልና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ባለው ግብዓት ሊሰማራበት የሚችል በመሆኑ በአጠቃላይ በቤተሰብ ደረጃ 23 ሺህ ሁለት መቶ 81 ተሳታፊዎች ሆነዋል። ለዚህም በተመረጡ በግቢና በጓሮ ልማት፣ በእንጉዳይ፣ በዶሮና በንብ እርባታ ተጠቃሚዎችን ለማሳተፍ ጥረት ተደርጓል። የቤተሰብ ፍጆታን በመሸፈንም በኩል በአትክልትና እንጉዳይ 15 ሺህ አንድ መቶ 84፣ የእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ 88፣ የስጋ ዶሮ አንድ ሺህ ሰባት መቶ 41፣ በንብ ማነብ 71 ለመሸፈን ተችሏል።
የስራ ዕድል ፈጠራ
የከተማ ግብርና ሥራ በቀላሉ በአካባቢና በቤት ውስጥ ሊጀመር የሚችል በመሆኑ በሰፊው የሥራ ዕድል ለመፍጠርም አመቺነቱ በዛው ደረጃ ከፍ ያለ ነው። በዚህም በዕፅዋት ዘርፍ በአትክልት ልማት ስምንት መቶ 47 ፣ በእንጉዳይ 27 በተለያዩ ንዑስ ዘርፎችም 25 በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በአጠቃላይ በንብ ማነብ፣ በበግ ማድለብ፣ በዳልጋ ከብት ማድለብ፣ በዓሳ እርባታ፣ በቆዳና ሌጦ ማሰባሰብ፣ እንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ፣ በወተት ከብት እርባታ፣ በጫ ጩት ማሳደግ፣ በእንስሳት መኖ ማቀነባበር እንዲሁም በአሳማ እርባታ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ጨምሮ ሶስት ሺህ ሰባት መቶ 39 የሥራ ዕድሎችን በዘርፉ መፍጠር ተችሏል።
የምርት ዕድገትና አቅርቦት
በከተማ ግብርና የምርት ዕድገቱንና አቅርቦቱን ለመጨመር በተከናወኑ ተግባራት 82 ሺህ ዘጠኝ መቶ 20 ቶን ምርት ጥቅም ላይ ውሏል። በዕፅዋት ዘርፍ የተሰማሩ ተጠቃሚዎች በተሰማሩበት የሰብል ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ መስክ 27 ሺህ አንድ መቶ 80 ቶን ለከተማዋ ነዋሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ በእንስሳት ተዋጽዖም 55 ሺህ አራት መቶ 40 የእንቁላል፣ የዶሮ ስጋ፣ ወተት እንዲሁም ማርና መሰል ምርቶች ቀርበዋል። ይህም ከገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ብቻ ይጠበቅ የነበረውን ምግብ በከተማዋና በዙሪያዋ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማቅረብ ከመቻል ባለፈ በሥራ ዕድል ፈጥራና በምግብ ራስን መቻል ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በውጭ ምንዛሪ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የቆዳና ሌጦ ማሰባሰብ ሥራ አንዱ ነው። በመሆኑም ከቄራ ውስጥና ውጭ አምስት መቶ 93 ሺህ ሶስት መቶ 68 የቆዳና ሌጦ ምርት ለማቅረብ ተችሏል። በዚህም በቄራ ውስጥ ከሚካሄድ እርድ ሶስት መቶ 34 ሺህ ሰባት መቶ 81 እንዲሁም ከቄራ ውጪ ሰባት መቶ 73 ሺህ ሶስት መቶ 63 በማሰባሰብ ለፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃው እንዲቀርብ ተደርጓል። ይህም በከተማዋ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከሚኖረው ሚና ባሻገር በሀገሪቱም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሊኖረው የሚችለው አስተዋፅኦ የላቀ እንደሆነ ይታመናል።
በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች
የመሬት ሀብት ውስን መሆን፣ የመስሪያ ቦታ አቅርቦት እጥረት ይህም የከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ የሚያስገድድ ነው። በተጠቃሚዎች ፍላጎት ደረጃ ምርቶችን በጥራትና በመጠን ያለማቅረብ ውስንነት ሌላው በዘርፉ የሚታይ ችግር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለእንስሳት ዋነኛ ግብዓት የሆነው መኖ ቢሆንም የመኖ አቅርቦት ውስንነት እና ጥራት ችግርም ይታያል። ይህም የዘርፉ ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።
በአጠቃላይ በከተማ ግብርና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ይህም በቀላሉ በጥቂት ቦታ ብዙም የሰው ኃይል ሳያስፈልግ የከተማው ነዋሪ የአርሶ አደሩን እጅ ሳይጠብቅ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ይረዳዋል፡፡በተጨማሪም የከተማ ግብርና ራስን በምግብ ከመቻል ባለፈ ሥራ አጥ ለሆነው የህብረተሰብ ክፍልም ከፍተኛ የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ ዘርፎች አንዱ እና ዋነኛ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2012
አብርሃም ተወልደ