የተመሰረተው ከዛሬ አስራ አራት አመት በፊት የጂኦ ቴክኒካል፣ የአፈርና የማቴሪያል ላብራቶሪ ፍተሻ እንዲሁም የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና የመአድን ፍለጋ አገልግሎቶችን የማቅረብ ቢዝነስ ዓላማን በማንገብ ነው። በአዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ መቀሌና ባህርዳር ከተሞች ለተገነቡ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ አነስተኛና ከፍተኛ ህንፃዎች ፣ የቢራ ፋብሪካዎች፣ የሲሚንቶ ፋበሪካ ፕሮጀክቶች፣ የመንገድና የድልድይ ስራዎች ፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የንፋስ፣ ግድብ፣ መስኖ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የጂኦ ቴክኒካልና የአፈር ምርመራ ስራዎችን በብቃት አከናውኗል- አዲስ ጂኦ ሲሰተም ኩባንያ።
ዶክተር አዲስ አለም ዘለቀ የኩባንያው መስራችና ባለቤት ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጂኦሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በጂኦቴክኒክ ትምህርት ዘርፍ ደግሞ ቤልጂየም ሃገር ከሚገኘው ብራሰልስ ዩኒቨርሲቲ የፒ ኤችዲ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። በተማሩበት ሙያም በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ ከሃያ አመታት በላይ የተግባርና የማስተማር ልምድ አካብተዋል።
አብዛኛው ኑሮውን በባህር ማዶ ያደረገ ሰው ወደ ሀገሩ ገንዘብ ይዞ በመምጣት መዋዕለ ንዋዩን ሲያፈስ ቢታይም እርሳቸው በእንግሊዝ ሃገር በነበራቸው ቆይታ ያላቸውን እውቅትና የስራ ልምድ እንዲሁም በዚያው ሀገር የነበራቸውን የስራ ባህልና ክህሎት በመያዝ ወደሃገራቸው ተመልሰዋል። በሙያቸው የመስራት ፍላጎት ገፋፍቷቸውም በእጃቸው ላይ ያለውን እውቀት ወደ ስራ ፈጠራ በመለወጥ ከዛሬ አስራ አራት አመታት በፊት የጂኦ ቴክኒካልና የአፈር ምርመራ ስራ ጀመሩ።
በወቅቱ ስራውን ሲጀምሩ መነሻ ካፒታላቸው ከ50 ሺ ብር አይበልጥም፤ ልምድ ለማግኘት ትናንሽ ስራዎችን ከውጪ ኩባንያዎች ጋር ሰርተዋል። ለቤቶችና አነስተኛ ህንፃዎችም የአፈር ምርመራ ስራዎችን አከናውነዋል። በመቀጠልም የጎጀብ የኤሌክሪክ ሃይል ማመንጫን ለመሳሰሉ የግድብ ፕሮጀክቶች የጂኦቴክኒክና የአፈር ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ልምዳቸውን እያሳደጉ መጡ።
ለትንንሽ ህንፃ ግንባታዎች የአፈር ምርመራ በማድረግ ስራውን የጀመረው ኩባንያቸው በአሁኑ ወቅት የያዛቸውን ልዩ ልዩ ማሽኖች ጨምሮ የካፒታል መጠኑ 30 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ከሃምሳ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም ቋሚ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አስር ያህሉ ከባችለር ሳይንስ ዲግሪ እስከ ፒ ኤች ዲ የትምህርት ደረጃ የያዙ የጂኦ ቴክኒካል ኢንጂነሮች፣ ጂኦሎጂስቶችና የጂ አይ ኤስ ባለሙያዎች ናቸው።
በመካከለኛ ደረጃ የኩባንያው የቴክኒካል ሰራተኞች ደግሞ የመቆፈሪያ ማሽን ኦፕሬተሮችን፣ የመኪና ሜካኒኮችንና የላብራቶሪ ቴክኒሺያኖችን አካቷል። ኩባንያው በሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ልክ ከሰላሳ እስከ አርባ ለሚሆኑ ዜጎችም በተለያየ መልኩ ጊዜያዊ የስራ እድል ይፈጥራል። በመሳሪያዎችና በፋሲሊቲ ደረጃም አምስት የመቆፈሪያ ማሽኖችና መኪናዎች ከአፈርና የማቴሪያል ፍተሻ ላብራቶሪ ጋር አቅፏል።
ኩባንያው እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ መቀሌና ባህር ዳር ከተሞች ከትንንሽ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላላቸው ከአንድ ሺ አንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ የህንፃ ፕሮጀክቶች፣ ለልዩ ልዩ የቢራ ፋብሪካዎች፣ የሲሚንቶ ፕሮጅቶች የጂኦ ቴክኒካል ስራዎችንና የአፈር ምርመራዎችን አካሂዷል። ለአዲስ አዳማና ለሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቶች፣ በጅንካ ለኔሪ ድልድይ እንዲሁም በወንዶ ገነት ለሸንኮራ ድልድይ ፕሮጀክት ተመሳሳይ የጂኦ ቴክኒካልና የአፈር ምርመራ ስራዎችን አከናውኗል።
ኢንዱስትሪዎችን በሚመለከትም ባህር ዳር ለሚገኘው የጣና ፐልፕና ወረቀት ፕሮጀክት፣ ለሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት፣ ባህርዳር ለሚገኘው የኮካኮላ ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ ለጎንደር የፔፕሲ ፕሮጀክትና ለዱከም ኢስት ኢንዱስትሪ ዞን ተመሳሳይ የጂኦ ቴክኒካልና የአፈር ምርመራ ስራዎችን ሰርቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ለአይሻ ሁለት፣ አዳማ ሁለት እና ለድብረብረሃን ጫጫ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ይህንኑ ስራ ሰርቷል።
ለሃርጌሳና ለአስራ አምስት ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች፣ ለመቀሌ የንፁህ ውሃ መጠጥ ፕሮጀክት እንዲሁም በአባይ ተፋሰስ ስር ለሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተለይም የመገጭ፣ የርብ፣ የበለስና የዲንጀር በርሃ የግድብ ፕሮጀክቶች ተመሳሳይ የጂኦቴክኒካልና የአፈር ምርመራ አገልግሎቶችን ሰጥቷል። የጨው ባህር፣ የሃሮማያ ሃይቅና የጣና ሃይቅ ጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ የጥናት ፕሮጀክቶችንም ሰርቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሱማሌ ክልል የአይሻ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን፣ ለአዲስ አበባ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሮቢቸዳ ግድብ ፕሮጀክትን፣ ሌሎች ኢንዱስሪዎችንና የቢራ ፋብሪካዎችን ይዞ እየሰራ ይገኛል።
ኩባንያው ከሚሰጠው የጂኦ ቴክኒካልና የአፈር ምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ ሁለት ተጨማሪ እህት ኩባንያዎችንም አቋቁሟል፤ ከነዚህ ውስጥ አንዱ አዲስ ኢንቫሮሜንታል ሰርቪስ ሲሆን፣ በዋናነት ከውሃ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህ ኩባንያም በዋናነት የውሃ አቅርቦት ማማከር፣ ውሃን የማጣራት፣ የውሃ ጥራት ፍተሻ፣ የሞያ ጤናና ደህንነት፣ የውሃ ማሸጊያ መስመሮች አቅርቦትና ጥገና እንዲሁም የቆሸሸ ውሃ የማከም አገልግሎቶችን ይሰጣል። ለብቻውም አስራ ሁለት ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ አግሮ ሊንክ ኢኪዩፕመንት ኤንድ ማሽነሪ የተሰኘው ሌላው እህት ኩባንያ እፀዋትን ለማቀነባበርና አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ ጭማቂዎችንና ለስላሳ መጠጦችን ለማሸግ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ የማሸጊያ መስመሮችን ይሰራል፤ የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ፓስቸራይዜሽን ስራዎችንም በተጨማሪነት ይሰራል።
ኩባንያቸው ከሚያከናውናቸው ስራዎች ጎን ለጎን ታዲያ ዶክተር አዲስ አለም በተማሩበት ሙያ በአዳማ፣ ሃዋሳ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች ኮርሶችን ይሰጣሉ። ኩባንያው የሰራቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ያቀፉ ዳታ ቤዞች ያሉት በመሆኑም እነዚህን ዳታ ቤዞች ለዩኒቨርሲቲዎች ክፍት በማድረግ ተማሪዎች ለጥናት ስራዎቻቸው እንዲጠቀሙባቸው ይደረጋል። በዚህም በርካታ ተማሪዎች የኩባንያውን ፕሮጀክቶች መነሻ በማድረግ ጥናታቸውን ሰርተዋል። ይህም ኩባንያው ከሚያከናውናቸው መደበኛ ስራዎቹ በተጨማሪ ተማሪዎች በዘርፉ እውቀት እንዲኖራቸውና እንዲሰሩ በትም ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ይጠቁ ማል።
‹‹የጂኦቴክኒካልና የአፈር ምርመራ ስራ ማንኛውም የግንባታ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት መታሰብ ያለበትና
ዲዛይን ሲደረግም መካተት ያለበት ጉዳይ ነው›› የሚሉት ዶክተር አዲስ አለም፣ በዚህ ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንት በተለይ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ትልቅ ድጋፍ የሚሰጥና አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ። ሆኖም የአስፈላጊነቱን ያህል በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ ሰዎች ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ይገልፃሉ።
በሌሎች ሀገራት ለአንድ ፕሮጀክት ዲዛይን የሚደረገው ወጪ ይታወቃል። ለእያንዳንዱ ወጪም የራሱ መመሪያም አለው። ይሁንና በኢትዮጵያ የዚህ አይነት አሰራር ባለመዘጋጀቱና አማካሪዎችን በደምብ የሚመዘን ስርዓት ባለመኖሩ ስራው በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑንም ዶክተር አዲስ አለም ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በሚመለከተው አካል በቂ የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ የኩባንያቸውን አቅም በማሳደግ ስራቸውን ወደ ተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ማስፋት እንዳልቻሉም ያመለክታሉ። ኩባንያቸው ይህንኑ የፋይናንስ ድጋፍ ቢያገኝ ኖሮ ከዚህም በላይ መስራት እንደሚችልና ከሀገር አልፎ ለጎረቤት ሀገራትም ሊተርፍ ይችል እንደነበረም ያስረዳሉ።
ኩባንያው እስከ ሶማሌ ላንድ ድረስ በመሄድ መስራቱንም ዶክተር አዲስ አለም ይጠቅሳሉ። ከጂቡቲም በርካታ ጥያቄዎች የሚቀርቡ ቢሆንም እዛ ድረስ በመሄድ ለመስራት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሌለ ይጠቁማሉ። ይህ ሲባል ግን እንደው ዝም ብሎ ማማረርና ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን በመንግስት በኩል ያሉ ፖሊስዎች ታች ድረስ ወርደው ቢሰራባቸውና ተግባራዊ ቢሆኑ፣ የፋይናንስ ስርዓቱ ቢስተካከልና ሴክተሩን በሚመራው ሚኒስቴር በኩል ጠንካራ ቁጥጥሮች ቢኖሩ ብዙ መስራት እንደሚቻልም ያመለክታሉ።
ለሙያው ፍቅር ላለው ሰው ካልሆነ በስተቀር የጂኦቴክኒካልና የአፈር ምርመራ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አስቸጋሪና ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር አዲስ አለም፣ በተለይ የሚመለከተው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ታች ድረስ በመውረድ ከፍቃድ አሰጣጥና ከማማከር ጀምሮ ያሉ ስራዎችን ሊቆጣጠር እንደሚገባ ያሳስባሉ። ይህም ሁሉም በዘርፉ ያለ ሞያተኛ በአቅሙ ስራዎችን ወስዶ ለመስራት እንደሚያስችለውና በሌላ በኩል ደግሞ ሙያውና እውቀቱ ያለው ብቻ ፕሮጀክቶችን ወስዶ የመስራት እድል እንደሚፈጥርለትም ይጠቁማሉ። በፋይናስ በኩል ያለው ችግርም በተመሳሳይ መፈታት እንደሚኖርበት ተናግረው፤ በተለይ በባንኮች በኩል ያለው የፋይናንስ አቅርቦትና የብድር ስርዓት ሊስተካከል የሚችለው የፋይናንስ ስርዓቱ ባጠቃላይ ሲስተካከል
መሆኑንም ያመለክታሉ።
‹‹እውቀቴንም ገንዘቤንም በዚህ የሞያ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ተሳክቶልኛል›› የሚሉት ዶክተር አዲስ አለም፣ በታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፈው መስራታቸውና አሻራቸውን ማስቀመጣቸው፣ በስራቸው ቀጥረው የሚያስሯቸውን ሰራተኞች በሞያቸው እንዲበቁ በማድረጋቸውና በተለያዩ ዩኒቨርቲዎች ያሉ ተማሪዎች የርሳቸውን ኩባንያ ፕሮጀክት ዳታ ቤዞች በመጠቀምና ጥናታቸውን ሰርተው ወደሙያው እንዲቀላቀሉ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው የስኬታቸው ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የስኬታቸው ዋነኛ ሚስጥርም ለሙያቸው ያላቸው ፍቅርና ለዚሁ የከፈሉት መስዋትነትና የሃገር ፍቅር ስሜት መሆኑን ይጠቁማሉ።
በተመሳሳይ በዚህ የሞያ ዘርፍ ተሰማርተው ስኬታማ መሆን ለሚፈልጉ ሰዎችም በቅድሚያ ለሞያው ፍቅርና ክብር ሊኖራቸው እንደሚገባና ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ሙያው የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ሊከፍሉ እንደሚገባ ይመክራሉ። ሀገራቸውንም መውደድ እንደሚገባቸውምና በሀገር ውስጥ ምንም አይነት ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ቢያጋጥሙም ታግለው መስራት እንደሚኖርባቸውም ያበረታታሉ።
ይህ ሴክተር ካልተደገፈ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እንደማያድግ ሁሉ በዚህ ሙያ ውስጥ ያሉ ሁሉ ዘርፉን ለማሳደግ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ በሙያው ላይ አተኩረው የሚሰሩና ሙያተኞችን ሊያበቁ የሚችሉ ጠካራ ኩባንያዎችን መፍጠር እንደሚገባም ያሳስባሉ። በዚህ ረገድም ዘርፉን የሚመራው የመንግስት አካል ታች ድረስ በመወረድ ሊሰራና ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
ዶክተር አዲስ አለም ገንዘብን ሳያስቀድሙ በተማሩበት የጂኦቴክኒካል ትምህርት ዘርፍ እውቀታቸውን በመጠቀም በርካታ ዜጎችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ አስተምረዋል። ይህንኑ አውቀታቸውን ወደ ስራ ፈጠራ በመቀየርና ታላላቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍም ሀገራቸውንና ህዝባቸውን አገልግለዋል። በቀጣይም በሌሎች ሀገራት ላይም የጂኦ ቴክኒክና የአፈር ምርመራ ስራዎችን የመስራት ዓላማ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ይህንኑ ግባቸውን እንዲያሳኩ ታዲያ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸውና ሊበረታቱም ይገባል። እኛም ዶክተር አዲስ በሞያቸው ለሀገርና ለህዝባቸው እያደረጉ ያሉትን አስተዋፅኦ እያደነቅን ቀሪ የስራ ዘመናቸው የስኬት እንዲሆን እንመኛለን። ሰላም !
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
አስናቀ ፀጋዬ