ክረምቱ ጠንከር ብርዱ ከበድ በሚልበት ወቅት ፀሀይ እንደበጋው ጉልበት አይኖራትም። አዲስ አበባ ያን ጊዜ ነው ፀሀይን የምትመኘው። ያኔ ሙቀትን በብርቱ ትናፍቃለች። ምክንያቱም አዲስ አበባ ልብስዋ ስስ ነው። ብርድን መታገል፣ ውርጭን መቋቋም የሚያስችል ጋቢ አልደረበችም። ሽንቁር በበዛባቸው ጎጆዎችዋ ብርድ እየገባ ልጆችዋን እንዳያማር፤ የአብራኳ ክፋዮች በበሽታ እንዳይጎዱ ስጋት ይገባታልና አዲስ አበባ ክረምትን ትጠላለች።
ዝናቡ አጥንትን ሰርስሮ በሚገባ ውርጭና ጣራን ለመገንጠል በሚታገል ንፋስ ታግዞ ሰማያዊ ጸጋውን ወደ ምድር ሊለቅ ተቃርቧል። ይሄ ዝናብ የስንቱን ጣራ ሰንጥቆ ስንቱን ከእንቅልፉ ይቀሰቅስ ይሆን? በተነዳደሉ ጣሪያዎች ሾልኮ ገብቶ የስንቱ ገመና እደጅ ያሰጣ ይሆን?
በሚያማምሩ እቃዎች በተሞላው ሳሎን ውስጥ ሰው ቢኖርም፤ ከአንዱ ጥግ ተከፍቶ የሰዓቱን ዜና የሚያወራው ቴሌቪዥን አንገቱን አዙሮ የሚያየው ቀርቶ ድምጹ የሚሰማው የለም። ሁሉም የራሱን ጩኸት ያዳምጣል። ባልና ሚስት፤ ሁሉቱም የራሳቸውን የውስጥ ግለት ማቀዝቀዣ መፍትሄ በማውጠንጠን ላይ ናቸው። በመፍትሄ እጦት የተጨነቀው አዕምሯቸው እንዳይነጋገሩ ምላሳቸውን ቆልፎታል። ሁሉም በራሱ ሀሳብ ተውጦ ሌላውን ረስቷል። አንድ የተለየ ድምጽ ቤት ውስጥ በሀሳብ ተራርቀው የነበሩ ባልና ሚስትን ወደ አንድ አቅጣጫ
አስመለከታቸው።
“ኳኳኳ……” የበር ድምጽ ነበር። ሳሎን ውስጥ ያሉት ባልና ሚስት ከየራሳቸው ዓለም መልሶ ወደ በሩ አስመለከታቸው። የሚሳሱላት የ4 ዓመቷ ልጃቸው ሳራ ወደ ሳሎን ገባች። “ማሚዬ… የቤት ስራና ጥናቴን ጨረስኩ….” ወደ እናትዋ እየቀረበች የተሰጣትን የቤት ስራና ማጠናቀቅዋን በደስታ ገለጸች። ወላጆቿ ከራሳቸው ዓለም ተመልሰው ሙሉ ትኩረታቸውን ልጃቸው ሳራ ላይ አድርገው በፈገግታ ተቀበልዋት። እናትዋ አቅፋ ስማ፤ ወደ አባት ተጠጋች።
አባቷን በተመሳሳይ አቅፋ ከሳመች በኋላ “ባባ መች ነው…እ.እ..ቤቢ የሚመጣው? ብቻዬ ማጥናት አስጠላኝ” ብላ አይን አይኑን እየተመለከተች ጠየቀች። ኤልያስ ይሄን ሲሰማ በረጅሙ ተነፈሰ። ይህ ጥያቄ ለህፃን ሳራ ምንዋም ነው። ወንድሟን መናፈቅዋ ብቻ የሚገልፅ፤ ‹‹ማም›› ለምትላት እናትዋ ሮዛና ‹‹ባባ›› እያለች በጣፋጭ አንደበትዋ ለምትጠራው አባትዋ ኤሊያስ ግን ጭንቅ የሚፈጥር ዱብእዳ ነው። የሳራ የሁለት አመት ታላቅ የመጀመሪያ ልጃቸው ሃሪ ታሞ ሆስፒታል ከገባ ወራት ተቆጥሯል።
አባት ጥያቄውን የሚሸሽ በሚመስል አንደበት “እ..እ..ሳርዬ ይመጣል አሁን እየዳነ ነው ይመጣል” ሲል አይኖቹን ከአይኗ ሸሸት እያደረገ መለሰላት። እሷግን በቀላሉ የምትለቀው አትመስልም ቀጠለች “መች ነው የእውነት ሚመጣው ሁሌ.. ይመጣል… ይመጣል…” እናት በተመሳሳይ የውስጥ መብሰልሰል
“ሳሪዬ እንዲ አይባልም አላልኩሽም። አባት ይዋሻል? ….ይመጣል አለሽ አይደል…” የአባቷን ጭንቀት ለመጋራት ሞከረች።
ሮዛ ለባለቤትዋ ያላት ጥልቅ ፍቅር ለቤተሰብዋ ያላት ክብር ለንጹህ ልቦች ብቻ የሚታደል ነው። የሮዛ ደም ግባት ያስደምማል። የሴት ልጅ ውበትና አካላዊ ቁመና ከወሊድ በኋላ ይቀየራል የሚለው ልማድ በሮዛ ድል ተነስቷል። ይበልጥ እያማረች ይበልጥ እየፈካች የምትሄድ ልቅም ያለች ቆንጆ ናት።
ባለትዳሮቹ ሳይነጋገሩ የሚግባቡ፣ ሳይከራከሩ የሚስማሙ፣ የተለያየ ቦታ ሆነው አንድ ሀሳብ፤ እንደ አንድ ሰው የሚያስቡና የሚያስቀና ፍቅር የታደሉ ባልና ሚስቶች ናቸው። ጥምረታቸው ሌላውን ያስቀናል። ፍቅራቸውን ለመግለፅ ብዙ ቃላት ማማጥ ይጠይቃል።
ኤሊያስ ፀባየ ሰናይ፣ በስራው ትጉህና ታማኝ ሰው ነው። የራሱ የሚለው አንድም ነገር ባይኖረውም ‹‹የገመናዬ ደባቂ ውድ ጓደኛዬ›› ከሚለው በላይ ጋር ይሰራል። በላይ የስኬቱ ቁልፍ ኤሊያስ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል። የኤልያስ በእርሱ ድርጅት መገኘት የድርጅቴ ህልውና ነው ብሎ ያምናል። በዚህ እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ለገጠመው ተድላ ሚስጥር ኤሊያስ የመሆኑን አሳምሮ ያውቀዋል። አብረው የጀመሩት ስራ ሁለቱንም በስኬት ማስጓዝ ሲጀምር በሸረበው ሴራ ጓደኛውን ከመስመር አስወጥቶ የራሱ ብቻ ማድረግ ችሏል። በዚህ ምክንያት ኤሊያስ የእርሱ ተገዢና አንዳችም ጥሪት ያልቋጠረ ዕድለ ቢስ ሆኗል።
በላይ እርሱን ማቆየት ረዳቱ አድረጎ ስኬቱ ይበልጥ ማረጋግጥ ይፈልጋል። በስራ ብቃቱ ይተማመንበታል። ፈጽሞ ከሱ እንዳይነጠል የድርጅቱ ህልውናው እናዳያከትም፤ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ለማዋል መላ ዘይዶለታል። ስለሱ ስራ ኤሊያስ ሲያስብ፤ እሱ ስራውን ኤሊያስን ማጥመድ ሁሌም በቁጥጥሩ ስር ማዋል ነው።
በላይ ኤሊያስን በተለያየ መልኩ የሱ ግዞተኛ ማድረግ ችሎበታል። ለኤልያስ ቤት ወጪ እና ዳባወራ ይመድብለታል። ነገር ግን ሁሉ ነገር በስሌት ይከወናል። ኤልያስ ገንዘብ በእጁ እንዳይገኝ አድረጎ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ እንዲገፋ በበላይ ተፈርዶበታል።
በላይ ጥሩ ጭንቅላት አለው ግን ለሴራ እንጅ ለስራ አልተፈጠረም። ገና ከጅምሩ አብረው የጀመሩት ስራ የራሱ ብቻ ለማድረግ ኤሊያስን ቀለበት ውስጥ ለማስገባት ብዙ ነገር አድርጎ ተሳክቶለታል። የተቀነባበረ ወንጀል ማሰራት፣ ያንን ወንጀል ለመሸፈን ሌላ ተጨማሪ ወንጀል እንዲሰራ ሆን ብሎ አጥምዶታል። በወንጀሎች ተብትቦታል።
ኤልያስ ስለ ራሱ ብቻ አይደለም ሀሳቡ፤ ጭንቀቱ ስለ ግሉ ብቻ አይደለም። እሱማ እጁን ለህግ ሰጥቶ ከሰራው ወንጀል መንጻትን ይሻል። ቅጣቱን ተቀብሎ ጭለማ ውስጥ ዘላለሙን ቢኖር ይመርጣል። የሚያፈቅራት ሚስቱ፣ የሚወዳቸው ልጆቹ ካለሱ ሲያስባቸው ህይወታቸው፤ መበተናቸው ያሰጋዋል። ቤተሰቡን ላለመበተን ፈሪ ሆኗል። የነሱን ሀዘን ላለማየት ህሊናውን እያቆሰለ ለመኖር ወስኗል።
የልጃቸው ጤና ሁኔታ ለውጥ ከማሳየት ይልቅ እያደር ተባብሷል። ይባስ ብሎ የያዘው ህመም በሀገር ውስጥ መዳን የማይችልና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ህክምና ማግኘት አለበት የሚል መርዶ ተነግሯቸዋል። የእስካሁኑ ህክምናው ወጪ የሚሸፈነው በበላይ ቢሆንም የውጭ ህክምናውን ለመሸፈን ግን ሌላ ትልቅ ፈተና በሮዛ በኩል እቤታቸው ገብቷል።
በላይ ኤሊያስ የሌለበት ወቅት እና አጋጣሚ እየጠበቀ ሮዛን አላነቃንቅ ማለት ከጀመረ ውሎ አድሯል። ትዳር ቢኖረውም ልቡ ውስጥ መታመን አልታተመም። ከሌሎች ጋር በመማገጥ ጊዜያዊ ደስታ ያገኛል፤ ህሊናውን አሳውሮ ስጋውን ያስደስታል። ባዶ ጭንቅላቱ ከበጎነት ርቆ የቆሸሸ ሀሳብና ተግባር ዋንኛ ማዘዣ ማዕከል ሆኗል። ሮዛ እርካሽ ፍላጎቱ ስታውቅ አራክሳ ብታባርረውም ዛሬ የባሰ ችግር ሲደርስ በሌላ መንገድ መሞከሩን ተያይዞታል።
በላይ የባልንጀራው ሚስት፤ የሮዛ ውበት ጭንቅላቱ ደፍኖት ንፁህ ገላዋን ሊያሳድፍ በአዲስ መልክ ሙከራ ማድረግ ከጀመረ ከራርሟል። የኤልያስና ሮዛ ልጅ መታመም ደግሞ የተሻለ እድል ፈጥሮለታል። ለሮዛ ሁለት ምርጫ በበላይ ቀርቦላታል። ለልጅዋ መታከሚያ ገንዘብ እንዲሰጣት አንሶላ በመጋፈፍ ክብርና ፍቅሯን ማርከስ። አልያም ደግሞ በገንዘብ እጦት የልጅዋ ሞት ቁጭ ብሎ መጠባበቅ። አንዱን መምረጥ ግድ ይላታል። … ይቀጥላል
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
ተገኝ ብሩ