ወቅቱ መተዛዘንና መከባበርን፤ ይቅር መባባልና በእውነተኛ ልብ መጸለይን የሚፈልግና ከክፋትና ከስግብግብነት ርቆ ራስንና ወገንን መታደግን በጽኑ የሚፈልግ ነው። እንኳንስና ሌላ ጥፋትና ሃጢያት ሊሰራ ከዚህ ቀደም ለተደረጉትም በጀሶ እንጀራ የወገንን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል፣ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠርና ሸቀጦችን በመደበቅ ላልተገባ ግላዊ ብልጽግና የወገንን ደም መምጠጥ፣ ሰፈሬና ቅጥሬ ላይ ለምን ደረስክ ብሎ ክቡር የሆነውን የሰውልጅ ሕይወት መቅጠፍና ማፈናቀል ወዘተ ንስሃ የሚገባበት ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ይህ ወቅት ማን ይዳን ማን ይትረፍ የሚታወቅበት አይደለም። ይህ ወቅት እንኳንስ እንደ እኛ ዓይነቱን ምስኪን አገር ቀርቶ በቴክኖሎጂና ሥልጣኔ እንዲሁም በሀብት የሰማይ ጥግ የደረሱ የመሰሉን አገራትን እንኳን ሳይቀር አስክሬን በባቡር አጓጉዘው በጅምላ እስከ መቅበር ያደረሰ ክፉ ወቅት ነው። በምድር ላይ አለ የተባለውን ሁሉ አቅም ተጠቅመናል አሁን ብቸኛው ተስፋችን ያለው በሰማይ ነው እስኪሉ ድረስም ያደረሳቸው ነው። ይህ ሁሉ ሲታይ ዘመኑ በደግ ተግባራትና በንስሃ ልንዋጀው የሚገባን እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ ጊዜ መሆኑን ያመለክተናል።
ይህ አስቸጋሪ ወቅት እንደ አገር ሁለት በጎና እኩይ የሰው ልጅ ባህሪያትን አሳይቶናል። ካላቸው በመቁረስ አቅም ለሌላቸው ያካፈሉና ማዕድ ያጋሩ እንዲሁም ወቅታዊውን የኢኮኖሚ ጫና ተገንዝበው ኪራይ የቀነሱና የተዉ መልካምና ቅን ሰዎችን ባየንበት ዓይን አስቸጋሪውን ወቅት በመጠቀም ከእጥረት አትርፈው የወገናቸውን ደም ለመምጠጥ የተስገበገቡ የክፉ ቀን ክፉዎችንም አስመልክቶናል። በዚህም ለበጎዎቹ መልካሙን ሁሉ እየተመኘን አድናቆታችንን ስንገልጽላቸው በክፉዎቹ ደግሞ እጅጉን አዝነናል። ከላይ በመንደርደሪያው
እንደተገለጸው ይህ ወቅት ከምን ጊዜውም በላይ አንዱ ለአንዱ ሊያስብለትና ሊጠነቀቅለት የሚገባው ወቅት ነው። ምክንያቱም የአንዱ እንክብካቤና ጥንቃቄ ለሌላው መኖር እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነውና።
የኮሮና ወረርሺኝ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ የከፋ አደጋ እንዳያስከትል ታስቦ ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት ተማሪዎች በቤታቸው እንዲቀመጡና በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ነው። ይህም የተደረገው ተማሪዎች ከአካላዊ ጥግግት ታቅበው ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ታስቦ ነው። ይህንን እርምጃ ተከትሎም ትምህርት ቤቶች ዝግ ከመሆናቸውም በላይ ተማሪዎች በቴሌቪዥንና ቴሌግራምን በመሳሰሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በመደረግ ላይ ይገኛል።
ትምህርት ቤቶች ዝግ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የመምህራንና ሠራተኞች ደመወዝ እንዳይቋረጥ መንግሥት የወሰነውን ውሳኔ
ለመተግበርም በተለይም የግል ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው በሚያስከፍሉት ክፍያ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ አውጥቷል። በመመሪያውም ክፍያ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች ከወላጅ ኮሚቴ ጋር በመመካከር እስካሁን ተማሪዎች ከሚከፍሉት ከ50 እስከ 75 በመቶ ባለው ውስጥ ወስነው እንዲከፈል እንዲሁም መክፈል አቅም የሌላቸው ከክፍያ ነፃ እንዲሆኑ የሚል ነው። ይህ ውሳኔ የወላጆችን የመክፈል አቅም ያገናዘበና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ መምህራንንና ሠራተኞች ገቢን ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ በመሆኑ ወቅታዊና ተገቢ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይሁንና ለዝግጅት ክፍላችን በደረሰው ጥቆማ መሠረት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከዚህ መመሪያ ውጪ ሙሉ ክፍያ ክፈሉ በማለት ሕገ ወጥ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
እዚህ ላይ ለሲመርበት የሚገባው ጉዳይ ሕግንና መመሪያን ማክበር የሁሉም ተቋማት ግዴታ መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻር ትምህርት ቤቶችን የሚመራውና የሚከታተለው ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያን ሁሉም አካላት ያለምንም መሸራረፍ ሊገብሩት ይገባል። ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን መመሪያ ሲያወጣ በርካታ ጉዳዮችን ማለትም የመምህራንና ሠራተኞች ሕይወት አለመጎዳቱን፤ ትምህርትቤቶች እንደሌላው ጊዜ ለተማሪዎች የሚፈለገውን አገልግሎት አለመስጠታቸውና የተማሪዎቹ ወላጆች የገቢ አቅም ከኮሮና ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ መዳከሙን ከግንዛቤ በማስገባት ነው። ስለሆነም አንድም በመተሳሰብና መተዛዘን እሳቤ በሌላም በኩል የመንግሥትን ውሳኔ ከማክበር አንጻር በእንዲህ መሰሉ አላስፈላጊ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ራሳቸውን ሊያርሙ ይገባል። የሚመለከታቸው አካላትም ጉዳዩን በቅርብ በመከታተል አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012