በከተራ ዕለት ከአራት ሰዓት ጀምሮ ከተለያዩ ደብሮች ታቦታት ይወጣሉ፡፡ ታቦታቱ ደማቅ በሆነ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንት ታጅበው አዘዞ ፣ ባህታ እና አጼ ፋሲለ ደስ መዋኛ ገንዳ ወደሚገኙት ሦስት ጥምቀተ ባህሮች ያመራሉ፡፡ የፋሲለ ደስ መዋኛ ገንዳ በሚገኝበት ጥምቀተ ባህር ስምንት ታቦታት ስለሚያድሩ በዓሉ ይበልጥ ይደምቃል፡፡ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችም ይህን ሥፍራ ይመርጣሉ፡፡ ሀገሬው በጥምቀት ታቦት ለማጀብ ያልወጡ ሰዎችን
ዳቢሎስ ሞተ አሉ ከነሚስቱ
ተስካር ያውጡለት ከዚህ ያልመጡ፤
እያለ ሸንቆጥ ያደርጋሉ፡፡
ጥምቀት በጎንደር ልዩ በዓል ነው፡፡ ይህን በዓል ለመታደም በ2010 ዓ.ም አርባ አምስት ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ጎንደር ተገኝተው ነበር፡፡ ዘንድሮ እስከ አሥራ አምስት ሺህ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ይገባሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥርም እንደሚጨምር እየተጠበቀ ነው፡፡
በ2011 ጥምቀትን በጎንደር በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ለበዓሉ የሚደረገውን ዝግጅት የሚያስተባብር አብይ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ በስሩም ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ከተማ አስተዳደሩ በጀት መድቦ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማከናወን ላይ ነው፡፡ ከተቋቋሙት ንዑስ ኮሚቴዎች የፀጥታና ሰላም አስከባሪ አንዱ ነው፡፡ ከወጣቱ ጋር በመተባበር ፀጥታ ለማስከበር በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ቦታዎችን ተከፋፍሎ እያንዳንዱ ታቦት በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባና በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ለማድረግ ሥራውን አጠናቋል፡፡
በዚህ ምክንያት ከፀጥታ አንጻር ችግሮች ይገጥማሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በርካታ ታቦታት የሚያድሩበትን አንድ ጥምቀተ ባህር ጠግኗል፡፡ እስከ ዘጠኝ ሺ ሊትር ውሃ የሚይዘውን የአጼ ፋሲለ ደስ መዋኛ ገንዳ ውሃ የመሙላት ሥራም እየሰራ ነው፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ አስቻለው ወርቁ ጥምቀት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ለማስመዝገብ የመጨረሻ ሂደት ላይ መገኘቱንና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለጎንደር ባለሀብቶች አቅርበን ኢንቨስት እንዲያደርጉ የምንጋብዝበት ወቅት በመሆኑ የዘንድሮው በዓል ለየት ያለ ነው ይላሉ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘም የተሻለ ገቢ ለማግኘት ለቱሪስት መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን የማስፋትና የማልማት ሥራ እየሰራ ነው፡፡ አንድ ተጨማሪ የባህልና የታሪክ ሙዚየም ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ ሙዚየሙ በዋነኝነት ከጥንት ጀምሮ እስካሁን በጎንደር የተከናወኑ ታሪካዊ ክስተቶችንና የቀድሞ ነገስታትን አመጣጥ ታሪክ የያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ የጦር መሳሪያዎችን ፣ ጥንታዊ መጠቀሚያ ቁሶችን፣ ቀደም ሲል በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የዱር አራዊት ቅሪትን አካቶ ባህልንም ታሪክንም የሚዘክር ነው፡፡ በተጨማሪም ለቱሪስት አገልግሎት ከሚሰጡ ባለሀብቶች ጋር የሚሠጡት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ቱሪስቶቹን የሚያረካ እንዲሆንና አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳከሰት ውይይት አድርጓል፡፡
ቱሪስቶች በብዛት የሚሸምቷቸውን የዕደጥበብ ውጤቶችና የባህል ልብሶች በማምረት ሂደት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወጣቶች ሰልጥነው ወደ አሥራ ሁለት ማህበራት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በፋሲል ግንብ አካባቢ ምርቶቻቸውን መሸጥ እንዲችሉ ሼዶች እየተገነቡላቸው ነው፡፡ ለጥምቀት በዓልም በጥምቀተ ባህር የሚሸጡበት ቦታ ስለተዘጋጀላቸው ምርቶቻቸውን ለበዓሉ ታዳሚ ያቀርባሉ፡፡
ለጥምቀት የሚመጣ ቱሪስት ሌላ ቦታ ቆይቶ ጥር አስር የጥምቀት በዓልን ብቻ ለማየት በጎንደር ከሚገኝ የተለያዩ ትእይንቶችን እየተመለከተ ስድስትና ሰባት ቀናትን ጎንደር ላይ እንዲቆይ የበዓል ሳምንት በሚል በከተማ አስተዳደሩና አጋር አካላት የተለያዩ ዝግጅቶች ተሰናድተዋል፡፡
ከጥር ስድስት ጀምሮ እስከ ጠር ዘጠኝ ድረስ የሚካሄደው የበዓል ሳምንት በርከት ያሉ ዝግጅቶችን ያቀፈና በርካታ አካላትን የሚያሳትፍ ነው፡፡ ጥር ስድስት ጠዋት በማርሽ ባንድ የታጀበ የባህሉን መጀመር ማብሰሪያ ዝግጅት ከቀረበ በኋላ የአጼ ቴዎድሮስ ሁለት መቶኛ ዓመት የልደት በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡ በመስቀል አደባባይም የአጼ ቴዎድሮስ የስዕል ኤግዚቢሽን የተካሄደ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ በርካታ የጎንደር ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ጥር ሰባት አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች ፣ የከተማዋ ወይዛዝርት ፣ አማተር ከያኒያንና ሌሎችም የሚመለከታቸው የኪነጥበብ ማህበራት ተሳታፊ የሚሆኑበት በጎዳና ላይ የሚካሄድ የፌስቲቫል ፕሮግራም ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ዝግጅት የተለያዩ የኪነጥበብ ማህበራት የራሳቸውን ትርኢት በጎዳና ላይ ያሳያሉ፡፡ ሀገሬ መልቲ ሚዲያ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ያሰናዳው በአጼ ቴዎድሮስ የልደት በዓል ላይ የሚያተኩር የስነጽሑፍ ምሽት መርሐግብር ይካሄዳል፡፡ በጎንደር ሲኒማ አዳራሽ የሚካሄድ የቴአትር ፌስቲቫልም ይኖራል፡፡ በፌስቲቫሉ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ማህበራዊ ችግሮችንና ጥንታዊ ባህሎችን የሚዳስሱ በርካታ ተውኔቶች ይቀርባሉ፡፡
ጥር ስምንትም በዚሁ የጎንደር ሲኒማ አዳራሽ በሚደረግ የስነጽሑፍ ምሽት በሙዚቃ የታጀቡ ሀገራዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ወጎችና ግጥሞች ይቀርባሉ፡፡ ጥር ዘጠኝ የበዓል ሳምንቱ በዓላዊ ትዕይንት ማጠቃለያ ነው፡፡ ከመስቀል አደባባይና ቴዎድሮስ አደባባይ የተለያዩ ባህላዊ አለባበሶች፣ አጨፋፈሮች አዘፋፈኖች ፣ የፀጉር ስሪቶች እና የጎንደርን ባህል የሚያሳዩ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚታዩበት ትእይንት ይደረጋል፡፡
በዚህ ዕለት ዝግጅት ካሰናዱ አካላት መካከል አንዷ ድምጻዊት ቻቺ ታደሰ ናት፡፡ ቻቺ ስለምታቀርበው ሥራ ስትናገር ‹‹ዓላማችን በተለይ ከውጭ ሀገር ለሚመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ቤተ እስራኤላውያን የኢትዮጵያን ባህል፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ አለባበስ ለማሳየት ነው፡፡ የባህል አልባሳት ፋሽን ሾው አዘጋጅቻለሁ፡፡ ኮንሰርትም አለኝ፡፡ በፍቃዱ ያደቴ እና ፍሬህይወት ኃይለ ሚካኤል የተባሉ ተወዳጅ የጎንደር ሙዚቀኞች ይዘፍናሉ፡፡ በተጨማሪም ከእስራኤል አገር ጊል የሚባል ከኢትዮጵያ በ4 ዓመቱ የወጣ ቤተ እስራኤላዊ ሙዚቀኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ መጥቶ ኮንሰርቱ ላይ ያቀነቅናል፡፡
እስራኤል ውስጥ 140 ሺ ቤተ እስራኤላውያን አሉ፡፡ ከዛ ሁለት አውሮፕላን ዳያስፖራዎች እንደሚመጡ መረጃ አለኝ፡፡ ከአሜሪካን ብቻ አሥራ ሁለት አውሮፕላን ሙሉ ዲያስፖራ ወደጎንደር ይመጣል፡፡ ቴል አቪቭ ውስጥ የኢትዮጵያ ቀን በሚል የምሰራው ሥራ አለ፡፡ እዛ አገር ቤተ እስራኤላውያን የሚከታተሉት ቴሌቪዥን ላይ እንግዳ አድርገው አቅርበውኝ ነበር፡፡ አብዛኞቹ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንደሆኑ ነው የተረዳሁት፡፡ እነሱ ወገን እንዳላቸው እንዲገነዘቡ፤ ባህላቸውን እንዲያውቁ ማድረግ እፈልጋለሁ ለዛ ነው በዚህ መልኩ ግንኙነት እንዲጀመር ጥረት እያደረኩ ያለሁት፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ አርባ ሰባት ሺ ተማሪዎችንም ታሳቢ አድርገናል፡ ይህ ሥራ ለአምስት ዓመታት የሚቀጥል ነው፡፡ ከጎንደር ከተማ አስተዳደርና ዳሽን ቢራ ጀምሮ አብረውኝ የሚሰሩ በርካታ አካላት አሉ›› ብላለች፡፡
ጥር አሥራ ሁለት የጥምቀት በዓል እንደተጠናቀቀ ለዳያስፖራዎችና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች በዳያስፖራ ማህበር አዘጋጅነት የእራት ግብዣ ይኖራል፡፡ ሰኞ ጥር አሥራ ሦስት የዳያስፖራዎች መድረክ ይኖራል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ የጎንደር ተወላጆች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከተለያዩ ከተሞች ከጋበዝናቸው ባለሀብቶች ጋር በጎንደር ልማት ላይ የኢንቨስትመንት ውይይት ይደረጋል፡፡ በዚህም በጎንደር ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተለይም በሆቴል፣ ቱሪዝምና በሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች ይቀርባሉ፡፡ ፍቃደኛ ለሆኑ በተናጠልም ሆነ በቡድን ቦታ ተረክበው ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ቦታ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ መሰረት በዓሉ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል ውይይት ከጎንደር ተወላጆችና ባለሀብቶች ጋር የሚደረግበትና የልማት ዕቅዶች የሚወጠኑበት ይሆናል – ጥምቀትም በመንፈሳዊ በዓልነቱ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር ለኢኮኖሚያዊ ትሩፋት በር በመክፈት በአንድ ሁነት ሁለት ስኬት ያበረክታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
የትናየት ፈሩ