ራሀፍ ሞሀመድ አል-ቁኑን ትባላለች የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያላት የአስራ ስምንት ዓመት ወጣት ነች፡፡ ወጣቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ከሳዑዲ ወደ ኩዌት ካቀናች ከጥቂት ቀናት በኋላ ከኩዌት እግሬ አውጪኝ ብላ ባንኮክ የገባችው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ አል-ቁኑን ‹‹እንዲህ አይነት እርምጃ እንድወስድ ያስገደደኝ ቤተሰቦቼ በግዞት ውስጥ እንድኖር ስላደረጉኝ›› ነው ትላለች፡፡
ከቀናት በፊት በባንኮክ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ሆና የድረሱልኝ ጥሪ በማሰማት የዓለምን ትኩረት ስባ የነበረችው ራሀፍ አል- ቁኑን አሁን ጥገኝነት አግኝታ ካናዳ ገብታለች፡፡ እርሷ እንደምትለው ከዚህ በኋላ እግሯ ሳዑዲን አይረግጥም፤ ዓይኗም በድለውኛል የምትላቸውን ቤተሰቦቿን ማየት አይፈልግም፡፡ ሰብዓዊ መብቴ ተረግጧል ብዬ ለዓለም ማህበረሰብ በመጮኼ በሳዑዲ ህግ መሰረት እስልምናን ክደሻል በሚል የሞት ፍርድ ስለሚያስፈርድብኝ ከዚህ በኋላ ወደ ቤተሰቦቼም ሆነ ወደዛች ሀገር ፊቴን ማዞር አልፈልግም ትላለች ወጣቷ፡፡
የባንኮክ ባለሥልጣናት ታዳጊዋ ቤተሰባዊ ችግር እንዳለባት በመግለጽ ከቀናት በኋላ ወደመጣችበት ኩዌት እንደምትመለስ ቢናገሩም በአየር መንገዱ ሆቴል ውስጥ ሆና ለጋዜጠኞችና ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ባሰማችው የድረሱልኝ ድምጽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥያቄዋን ተቀብሎ ጥገኝነት እንድታገኝ አድርጓል፡፡
የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቲያ ፍሪ ላንድ እንደገለጹት ታዳጊዋ መንፈሰ ጠንካራና ለሌሎችም ምሳሌ መሆን የምትችል የመብት ታጋይ ነች በማለት አወድሰዋታል፡፡ ካናዳውያን የታዳጊዋን ንግግር ለመስማት ቢፈልጉም አዲሷ ካናዳዊት ግን ባሳለፈችው እንግልትና በተጓዘችው እረጅም ጉዞ ምክንያት የድካም ስሜት ስላለባት ሀሳቧን ለህዝብ ለመግለጽ ጊዜ እንደሚያስፈልጋት የካናዳ ባለሥል ጣናት ተናግረዋል፡፡
ታዳጊዋ ከደቡብ ኮሪያ ሴዑል ፒርሰን ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ተነስታ ቅዳሜ እለት ነበር ካናዳ የገባችው፡፡ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ቀደም ሲል በትውልድ ሀገሯ እያለች የመማርም ሆነ የመሥራት መብት እንደተነፈጋት፣ በደል እንደ ተፈጸመባትና ምናልባትም አንድ ቀን ቤተሰቦቿ ሊገድሏት እንደሚችሉ ያላትን ሥጋት ተናግራለች፡፡ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገረችው ቤተሰቦቿ ለስድስት ወራት በባዶ ክፍል ውስጥ ዘግተውባት እንዳሰቃይዋትና ጸጉሯንም እንደላጯት አስረድ ታለች፡፡
የቤተሰቦቿ ቃል አቀባይ ነኝ ያለ አንድ ሰው ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ምንም አይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግና አሁን ቤተሰቦቿን የሚያሳስባቸውና ቅድሚያም የሚሰጡት ስለልጃቸው ጤንነት እንደሆነ አስረድቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲም እንዲሁ ስለሁኔታው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
ኢያሱ መሰለ