የኮሮና ቫይረስ በዓለም ዙሪያ ከፈጠረው ሥጋትና ጭንቀት አኳያ ከበሽታው መዛመት ባሻገር በቤተሰብና በአጠቃላይም በሕብረተሰቡ ላይ ያስከትላል ተብሎ የሚጠበቁ ስጋቶች አሉ። በበርካታ ያደጉ አገራት ወረርሽኙን ለመከላከልና የዜጎችን ህይወት ለመታደግ የሚደረጉ ከፍተኛ ጥረቶች ቢኖሩም ዛሬም የዓለም ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ቀጥሏል። ችግሩ አብዛኛውን የዓለም አገራትን ያዳረሰ ቢሆንም ከሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አንፃር በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሀገር ኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን በበለጠ የእያንዳንዱን ቤተሰብ የሚመለከት ስጋትም ነው። ከዚህ ስጋት ለመዳን ዜጎች በግላቸውና በቤተሰብ ደረጃ የሚያደርጉት ራስን የመጠበቅና የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ርብርብ እንደ ሀገር የሚያመጣው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን የሥነ ህዝብ ጉዳይ ባለሙያው ዶክተር ንጉሴ ተፈራ ይናገራሉ።
ዶክተር ንጉሴ ተፈራ ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ ሥነ ህዝብ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ፤ የውጭ ጉዳይ የፍትህና የማስታቂያ ቢሮ ሃላፊ፤ የፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ለረጅም ዓመታትም በሚዲያው ዘርፍ የሰሩ ባለሙያ ናቸው። ዶክተር ንጉሴ የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ከቤተሰብ እስከ መንግሥት መደረግ ያለበትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
ዶክተር ንጉሴ እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ሳይታሰብና ማንም ዝግጅት ሳያደርግ የተከሰተና በከፍተኛ ደረጃ መዛመት ዓለምን ለጭንቀት የዳረገ፤ የዓለምን እንቅስቃሴ የገታ ብሎም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገና ዛሬም መጨረሻው ያልለየለት አደገኛ ወረርሽኝ ነው። ወረርሽኙ ምንም እንኳ ዓለም አቀፍ ክስተት ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሀ አገራት ላይ የሚጥለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ጠንካራ ከመሆኑ ባሻገር ቀውሱ ከሀገር ኢኮኖሚ በላይ በግለሰቦችና በቤተሰብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የባሰ ነው። ህዝቡ በቤቱ እንዲቀመጥ በመደረጉና በሀገሪቱ አገልግሎት ሰጪና አንዳንድ የልማት ተቋማት ብቻ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው በቫይረሱ ከሚታመመው ሰው በላይ ለሌሎች ችግሮች እየተጋለጠ ያለው ዜጋ ቁጥር እንዲጨምር እያደረገው ይገኛል።
በመንግሥትም በኩል እንደ ሀገር ዕርዳታ የሚያስፈልገው አስራ አምሰት ሚሊየን ህዝብ ወደ ሰላሳ ሊጨምር እንደሚችል መገለፁ ይታወሳል። ይህ ማለት ደግሞ መንግሥት ይህንን ህዝብ ከሦስት እስከ አራት ወራት በራሱ ወጪ ለመሸፈን ቢሞክር ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስፈልገዋል ማለት ነው። በአሁኑ ወቅትም በከተሞች በዝቅተኛና በዕለት ሥራ ተሰማርቶ ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው ከሦስት ሚሊየን ህዝብ በላይ ችግሩ እየነካካው ይገኛል። ከዚህ በተጓዳኝ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንደ ሀገር በመቀዛቀዙ የሥራ አጡን ቁጥርም እያሻቀበው ይገኛል። በመሆኑም ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ የመንግሥት እንቅስቀሴ ብቻ በቂ ባለመሆኑ እንደ ህብረተሰብ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቃል። እንደ ህብረተሰብ እንቅስቃሴ ለማድረግ ደግሞ በቤተሰብ ደረጃ በመንግሥትና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ትእዛዞችን እየተከታትሉ በአግባቡ መተግበር ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ይሆናል።
በዚህ ረገድ የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት የሴቶች ትልቅ ሚና መጫወት የሚችሉ በመሆኑ ሁኔታዎችና ዕድሉ ሊመቻቹላቸው ይገባል። እንዳጠቃለይ የሀገር ሁለንተናዊ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው በሴቶች ቢሆንም እስካሁን ያለው ልምድ እንደሚያሳየን በሴቶች ላይ ያለው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ጫና ማበርከት የሚችሉትን አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱና ማግኘት ያለባቸውንም ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ችግሩ ሥር የሰደደና ለመፍታትም ረጅም ጊዜ የሚፈልግ ቢሆንም ዛሬም በሁለት አይነት አካሄድ የእነሱን ተሳታፊነት ለማጠናከር መሥራት ይቻላል። የመጀመሪያው አንገብጋቢ ጉዳይ ከሆነው የኮረና ስርጭት ጋር በተያያዘ ሴቶች ቤተሰብ በማስተዳደርና በቁጠባ ረገድ ያላቸውን ብቃት እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያሉባቸውን ችግሮች ከመሰረቱ አጥንቶ መፍትሄ ማስቀመጥ ይጠበቃል። ሁሉም ሴቶች አንድ ያለባቸው ችግር አንደ አይነት አይደለም። ለምሳሌ በገጠር ያለች አንዲት እናት ገበያ ውላ ስትመጣ ባሏ ቢኖርም ባይኖርም ልጅ አዝላ እንኳን ዕቃ ተሸክማ የምትመጣው እሷው ስትሆን እቤት ከገባችም በኋላ ውሃ መቅዳት እንጨት መፍለጥ ምግብ ማብሰልም ይጠብቃታል፡፡ ይህም ሆኖ ገበታ እንኳን የምትቀርበው ሙሉ ቤተሰቡ ከተመገበ በኋላ ነው። እንዲህ አይነቱ ባህል ቤተሰቡን ለጊዜው የሚጠቅም ቢመስልም ሴቶችን ለጉዳት የሚዳርግና
አምራች እንዳይሆኑ አምራች ሃይል እንዳያፈሩም የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር ጫናው ሲበረታ ወደ ከተማ ለመግባትና በከተማም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ እንዲኖሩ ያስገድዳቸዋል። አይነቱና መጠኑ ቢለይም በከተማም በሴቶች ላይ ያለው ተጽዕኖ ተሳትፏቸውን የሚገድብ ነው። ለዚህ ደግሞ ከባህሉ ባልተናነሰ በሃይማኖት በኩል ያለው የአስተምህሮ መዛነፍ እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲስፋፉ መንገድ ከፋች ነው።
በዚህ ረገድ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ለውጥ እየታየ ቢሆንም ከሚጠበቀው አንፃር ዛሬም የሚቀሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። ይህም ሆኖ በመንግሥት በኩል የሚዘጋጁ የሥነ ህዝብ ጉዳይ ፖሊሲዎች፤ ሴቶችን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች በተለይም በገጠር ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ከወረቀት ወርደው ተተግባሪ መሆን አለባቸው። ነገር ግን ችግሩ መንግሥት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ህጎች ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑና ማንኛውንም ስው ከኋላቀርነት ነፃ የሚያወጣው ትምህርት እንደመሆኑ ሴቶችን በማስተማር ማብቃት ይጠበቃል።
በተጨማሪ በቤተሰብ ውስጥ ከሴቶች ባለፈ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲገጥሙ የልጆችን በተለይ የወጣቶችን ተሳትፎ ማጠናከር ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ለሀገር ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ የሚጠበቀውና ለሚደረገው ሽግግር ትልቁን ሚና የሚወስደው ወጣት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ራሱንና አገርን ሊጠቅም በሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም። ዛሬ ከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው በሀገሪቱ ያለው የኢንቨስትመንት ሀብት ውስን በመሆኑና ፈጣን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ያለሥራ የተቀመጡት በርካቶች ናቸው። በዚህ ላይ እንደ ኮሮና አይነት የእንቅስቃሴ ማዕቀብ የሚጥልና ኢኮኖሚን የሚጎዳ ክስተት ሲፈጠር ችግሩን በማወሳሰብ ወጣቶችን የቤተሰብ ተጧሪ ከማድረግ ባለፈ ለሀገር ቀውሰ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአግባቡ መከታተል ከተቻለ እንደ ቤተሰብ ሰርቶ ቤተሰብንም ራስንም በመደጎም ችግሮችንም ማለፍ ይቻላል። በአነስተኛ ገንዘብ በመበደር ችግሮችን ለማለፍ ይቻላል፡፡ በአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ አገራት ያለው ከመደበኛ ሥራ ባሻገር ቤተሰብ አንድ የራሱን የገቢ ማስገኛ የመፍጠር ልምድ እዚህ በማምጣት መተግበር ይቻላል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥትም በየአካባቢው ለገቢ ማስገኛነት ሊውሉ የሚችሉ ነገሮችን መለየት ማልማትና ማቅረብን ይጠበቅበታል። ልማትን በማፋጠን የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እውቀቱ፤ ልምዱና ክህሎቱ ያላቸውን ኢትዮጵየውያን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ መጠቀም፤ በክልሎችም የሚካሄዱ ልማቶችም ተመጣጣኝ መሆን ስለሚኖርባቸው የክልል መንግሥታትም ልማት ላይ
ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው።
በሌላ በኩል አሁን በመንግሥትና በህዝብ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየታየ ያለው ቁርጠኝነት አደጋውን ካለ ብዙ ጉዳት ለመሻገር የሚያስችል እንደሆነ ተስፋ የሚጣልበት ቢሆንም። በተወሰነ ደረጃ የችግሩ ሰለባ በሆኑ ቤተሰቦች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊከሰት ስለሚችል እንደ ቤተሰብ በመነጋገር ለሌላውም መትረፍ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል። ለብቻ የሚደረግ ጥንቃቄም ሆነ ጥበቃ ብቻውን የሚጠበቀውን ውጤት ሊያስገኝ አይችልም። ስርጭትን ለመግታት ለውጡ እንደ ማህበረሰብ መምጣት አለበት ሲባል የሚጀምረው የማህበረሰቡ ዋና አካል ከሆነው ከቤተሰብ ነው። ይህም ሆኖ ጥንቃቄ የማያደርጉት ለሚጠነቀቁትም የሚተርፉበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ በተወሰነ ቤተሰብ ወይንም ግለሰቦች የሚደረግ ለውጥና ልፋት ራስንም ቤተሰብንም ለመታደግ በቂ ላይሆን ይችላል። እንደ ኤች አይቪ ኤድስና ሌሎች ወረርሽኞች ሲከሰቱ በግለሰብ ደረጃ በሚደረግ ጥንቃቄ ራስን የመታደግ ዕድሉ ሰፊ ነበር፡፡ ኮሮና ግን የግለሰብ ጥንቃቄ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም ለጥንቃቄው ውጤታማነት ግን በአካባቢው ያሉ ሰዎች እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው። በዚህ ረገድ አሁን አሁን በገበያና አንዳንድ ቦታዎች ያለው መዘናጋት መወገድ ስላለበት ሕግ አስከባሪዎችም መጠበቅ ሰውም ራሱን መጠበቅ አለበት።
ከወረርሽኙ ለመዳን ከቤት መዋል በቤተሰብ ላይ ከሚፈጥረው ተጽዕኖ አንዱ የገቢ መቀነስ ነው። ሳይነቀሳቀሱ መሥራት ገቢ ማግኘት የሚችሉ እንደ ቤት አከራይ ያሉት ጥቂቶች ናቸው። በኢትዮጵያ አብዛኛው የህብረተሰቡ ክፍል አኗኗር ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ሥራ ሳይሰራ ውሎ ባለው ጥሪት የዕለት ጉርሱን በመሸፈን ለተወሰነ ጊዜ መቆየት የሚችለው በጣም ውሱን ነው። በዝናብ መጥፋት ብቻ በርካቶች ለረሃብ ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ ከአስራ አምስት ሚሊየን ህዝብ በላይ ከመንግሥት ዕርዳታ ሲጠብቅ ቆይቷል። ከሰላሳ በመቶ በታች ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፡፡ ምርትና ምርታማነት በሌለበት ድህነት በበዛበት አገር ወረርሽኝ የነበረውንም ችግር የሚያወሳስብ ይሆናል። አንዳንዴም ችግሩ ሲጠነክር የሚያስከትለው ጦስ በግለሰብ ደረጃ ገንዘብ በመኖሩና ባለመኖሩ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለውን የምርትም አቅርቦት መሠረት የሚያደርግ ይሆናል።
በቅርቡ በአሜሪካ ተከስቶ የነበረው የውሃና የሶፍት እጥረት ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። በኢትዮጵያ ያለው የህዝብ ብዛትና የምርት አለመመጣን በዚህ ረገድ ያለውን ችግር አሳሳቢ ያደርገዋል። ምንም እንኳ በኢትዮጵያ የመሬት እጥረት ባይኖረም የሚመረተው ሀብት ያለውን ህዝብ አጥግቦ የሚያሳድር አይደለም። በሀብት መጠንና በህዝብ ቁጥር መካከል ያለው ክፍተት ሰፊ በመሆኑ የምግብ አቅርቦት የጤና የትምህርት አቅርቦት ጋር የተመጣጠነ አይደለም። በዛ ላይ
ሲከሰቱ የነበሩ ሰው ሰራሽ ችግሮችም ዜጎች ሀብት እንዳያፈሩ ተረጋግተው እንዳይኖሩና ጥሪት እንዳይዙ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡
ከዓመታት በፊት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት በሀገሪቱ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ህዝብ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ የነበሩ ሲሆን በቋሚነት እንደ ሀገር አስር ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነበሩ። በመሆኑም የኮሮናን ወረርሽኝ በቤተሰብ ደረጃ ብሎም በማህበረሰብና በሀገር መከላከል ካልቻልን በዚህ ሁኔታ የተዳከመውን የመንግሥትም፣ የግለሰብም አቅም የበለጠ የሚያሽመደምድ ይሆናል ማለት ነው። ይህም ሆኖ በየቤተሰቡ ገቢ ባያስገኝ እንኳ ወጪ በመቀነስ በኩል መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ ብክነትን መቀነስ አንዱ አማራጭ ሊደረግ ይችላል፡፡ በቅርቡ በክርስትና እምነት የሚከበሩትን በዓላት ተከትሎ ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት ሲያደርግ የነበራቸውን ነገሮች ለመከወን መንቀሳቀሱ ከዋጋ ባለፈ ጥሪቱንም የሚያሳጣው መሆኑን መገንዘብ ነበረበት። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ የኮሮና ቫይረስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፤ እያንዳንዱ ሰው ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያደርስና በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ምን ሊያስፈልገው እንደሚችል የሚታወቅ ነገር ባለመኖሩ ባለ አቅም ተዘጋጅቶ መቀመጡ ተገቢ ይሆናል።
በአጠቃላይም አንድ ቤተሰብ የተለያዩ አገራዊም ሆነ ግላዊ ችግሮች ሲገጥሙት በራሱ አቅም እንዲያልፍ የተጠናከረ እንዲሆንና በርካታ ጠንካራ ራሳቸውን የቻሉ ቤተሰቦች በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲፈጠሩ ራስን ለመቻል ቁጠባ ሁሌም የሚያስፈልግ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከምግብም ቀንሶ መቆጠብ ይጠበቃል።
ህብረተሰብ የተሳሰረ በመሆኑ በአንዱ ላይ የሚደርሰው በሌላውም ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም። ራስን መቻል በግለሰብ የሚከናወን ቢሆንም ለማደግ ተያይዞ ተረዳድቶ መሆን አለበት። በዚህ አይነት ኢኮኖሚው በሚዳከምበትና ሥራ አጥነት በሚስፋፋበት አጋጣሚ የህብረተሰቡ የመረዳዳት እንቅስቃሴ በርካታ ችግሮችን የሚቀርፍ ነው። ስለዚህ የበጎ ፈቃድ ማጠናከር ለፋሲካ በዓል ሰሞን የነበረው ትብብር በቤተክርስቲያን በኩልና በወጣቶች የተጀመሩ ሥራዎችን መቀጠልና ባህል ማድረግ ይገባል። የሃይማኖት አባቶችም ህዝብ ራሱን እንዲጠብቅ ከማስተማር ባለፈ በመረዳዳቱ ረገድ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት መአድን የመጋራት በጎ ተግባር እንዲስፋፋ ለተከታዮቻቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
በመጨረሻም የሚሰሩት ሥራዎች እንዳይሰናከሉ በሚዲያውም ረገድ እየተከታተሉ መዘናጋት እንዳይፈጠር ህዝብን ማስተማር ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ዜጎች ስለኮሮና ቫይረስ ምን እንደሆነ ስለሚያስከትለው አደጋ መከላከያ መንገዶቹንና ስለሚደረገው ጥንቃቄ መረጃና ምክር የማግኘት መብት አላቸው። እስካሁን ሚዲያውን ለማንቀሳቀሰ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምሮ የችግሩን አሳሳቢነት አስመልክቶ በተደጋጋሚ የተሰጡት መግለጫዎችና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች፤ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ሃይል፤ አርቲስቶች፤ የሃይማኖት አባቶች፤ በተለይ ደግሞ የጤና ሚኒስቴር በሚኒስትሯ ደረጃ በየቀኑ የሚሰጠው መረጃ የተሳሳቱና ችግር የሚያስከትሉ መረጃዎችን ለመቀነስ አስቸሏል። ይህም ሆኖ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ሚዲያውን እንዴት እንጠቀም፤ ምን እናድርግ በምን መልኩ መረጃዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ይሁኑ የሚለው ቢቻል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ መቀመጥ አለበት። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የኤች አይቪ ኤድስ ጉዳይ አሳሳቢ በነበረበት ወቅት ብሔራዊ የኮሚዩኒኬሽን ፍሬም ወርክ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ በመዋሉ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል። በተመሳሳይ የሥነ ተዋልዶ ጉዳይን በተመለከተ የሚዲያ የኮሚኒኬሽንና የአድቮኬሲ ስትራቴጂ የሚል ተቀርጾም ሲሰራ ነበር፡፡ በኮሌራም እንደዚሁ ተደርጓል። እነዚህን እንደ መነሻ በመውሰድ ሚዲያውን መቆጣጠር ይገባል።
በአቀራረብም ረገድ የሚሰጠው መረጃም የጉዞ ታሪክን ያካተተ መሆኑና ተክክለኛ መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ በወቅቱ እንዲደርስ የማድረጉ ሥራ መቀጠል አለበት። እስካሁን ይህ ባይደረግ ኖሮ ምን አልባትም በርካታ መጥፎ ዜናዎች ለህዝቡ ይሰራጩና ያልታሰበ ችግር የሚፈጥሩበት ዕድል ሰፊ ይሆን ነበር። አሁንም አንዳንድ መዘናጋቶችና የተሳሳቱ መረጃዎችን የማሰራጨት እንቅስቃሴ ስላለ መዘናጋት አለ፡፡ ለቀጣይም ሚዲያው ከበሽታውና ከሞት አደጋው ባሻገር የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ታሳቢ በማድረግ የተፈጠሩትን ነገሮች መዘገብ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትሉትንም ውጤቶች በማስተንተን ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲወስድ የማድረግ ሃላፊነት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ