ከ12 አመታት በፊት የተሰናበትነው የሚሊኒየሙ የመጨረሻ ወረርሽኝ ማለትም የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃው ስፓኒሽ ፍሉ/ የሕዳር በሽታ/በሰው ልጅ ላይ የመውጫ በትሩን ያሳረፈበት 100ኛ አመት በሚያስደንቅ አጋጣሚ ከኖቨል ኮሮናቫይረስ ሰሞናት ጋር ተገጣጥሞ ሕመሙን ሕማማት አድርጎታል። ይህ ወረርሽኝ በመላው አለም ከ50 ሚሊዮን በላይ በሀገራችን የ40ሺህ የሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በዚህ አደገኛ ወረርሽኝ የሞተው የሰው ቁጥር በ1ኛውና 2ኛው የአለም ጦርነቶች ከሞቱት ይበልጣል። በሁለት አመታት የወረርሽኙ ቆይታ ግማሽ ቢሊዮን ሰዎችን አጥቅቷል። ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሎ እንደነበርም በታሪክ ድርሳናት ተከትቦ ይገኛል። የሚያሳዝነው ይሄን ሁሉ ቀውስ ያስከተለው ወረርሽኝ በጊዜው በነበሩ ጋዜጦችና መፅሔቶች ተገቢውን ሽፋን ካለማግኘቱ ባሻገር በቂ መፅሐፍትም አልተጻፉም ማለት ይቻላል። ወረርሽኙ ከ1ኛው የአለም ጦርነት ጋር መገጣጠሙ በቂ ትኩረት ላለማግኘቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ዛሬስ ስለ ኮቪድ – 19 የሀገራችን ጋዜጦች፣ መፅሔቶች፣ ሬዲዮዎችና ቴሌቪዥኖች ከአኃዝ ለዛውም በቅጡ ካልተተረጎመና ካልተተነተነ አኃዝ ባለፈ ተገቢውን ሽፋን እየሰጡ ነው !? መልሱን ለእነሱ እተወዋለሁ። በተቃራኒው የተሻለ መረጃ፣ ግንዛቤ፣ የሚዲያ አማራጭና ተደራሽነት ባለበት የምዕራብ ሀገራት የሚገኝ የፐብሊክም ሆነ የግል ሚዲያ ለ24 ሰዓት ከተለያየ ማዕዝን እየቀጠቀጠው ይገኛል። ሌላ ወሬ የለም። ወሬው ሁሉ የሚተነተነው፣ የሚተረጎመው፣ የሚበየነውና የሚነጸረው ከኮቪድ 19 አንጻር ነው። የእኛ ሚዲያዎች በዚህ ሚዛን ራሳቸውን አስቀምጠው ሊመዝኑና ውስንነቶቻቸውን ቢቀርፉ ይበጃል።
በነገራችን ላይ ይህ ወረርሽኝ ሶስተኛው አደገኛ ወረርሽኝ ነው። ከዚህ በፊት በ14ኛው እና በ16ኛው ክ/ዘ/ እንደ ቅደም ተከተላቸው ጥቁር ሞት / ብላክ ዴዝ /ና የፈንጣጣ / ስሞልፓክስ / የሚባሉ አደገኛ ወረርሽኞች አሳር አብልተው አልፈዋል። ወደ ስፓኒሽ ፍሉ ስንመለስ ለመጀመሪያ ጊዜ የት እንደተከሰተ ዛሬ
ድረስ በሊቃውንት መግባባት ላይ አልተደረሰም። አንዳንዶች መጀመሪያ የታየው ከተጨናነቀውና ፈረንሳይ ከሚገኘው የእንግሊዝ የጦር ካምፕ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ የለም አሜሪካ ካንሳስ ከሚገኝ እርሻ ነው የተከሰተው ሲሉ የራሳቸውን መከራከሪያ ያቀርባሉ፤ ወቅትን ጠብቀው ከቻይና በተሰደዱ አእዋፍ አማካኝነት ነው የመጣው የሚሉም አሉ። የዛሬው ኮቪድ – 19 መነሻም ሳይንቲስቶችን ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን እያወዛገበ ይገኛል። አንዳንዶቹ ውሃን ከተማ ከሚገኝ የየብስና የውሃ አራዊት መሸጫ ገበያ ውስጥ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው ሲሉ፤ (መቼም ይሄን ገበያ በቴሌቪዥን ለተመለከተ እንኳን ለመብላት ለአይን ይዘገንናል ያስፈራል፤) ሌሎች ደግሞ ከቻይና ላብራቶሪ አምልጦ የወጣ ቫይረስ ነው ይላሉ። ዶናልድ ትራምፕና ተከታዮቹም የዚህ መላምት አቀንቃኝ ናቸው። ሆኖም ተጨባጭ ሳይንሳዊ ማስረጃ የላቸውም። ይሁንና የወታደሩን ሞራል ለመጠበቅና ለ1ኛው የአለም ጦርነቱ ስንቅና ትጥቅ ያቀርቡ የነበሩ ፋብሪካዎች ምርት ወረርሽኙን በመፍራት እንዳይስተጓጎል ስለ ወረርሽኙ እንዳይዘገበ ቅድመ ምርመራ / ሴንሰርሽፕ /ተጥሎ እንደ ነበር ይወሳል። ሆኖም ስፔን የጦርነቱ ተሳታፊ ስላልነበረች ጋዜጦቿ ስለ አደገኛው ወረርሽኝ በነጻነት ይፅፉና ይዘግቡ ነበር። የተቀረው አለም አንዳንድ ጋዜጦችም ከወደ ስፔን የሚወጡ ዘገባዎችን እየተቀባበሉ ያትሙ ስለነበር ሀገሪቱ በተዛባ መንገድ በወረርሽኙ የተነሳ እውቅና አገኘች። ወረርሽኙም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስፓኒሽ ፍሉ ተባለ። ይሄው እስከ ዛሬ ድረስ ስፔን ያለስሟ ስም ተሰጥቷት አለች።
ወደ ሀገራችን ስንመጣ ወረርሽኙ ህዳር ወር ላይ ስለገባ “ የህዳር በሽታ “ ተባለ ፤ ወደ ወለጋ ሲዛመት ደግሞ የንፋስ በሽታ ‘ ዱኩባ ቂሌንሳ ‘ ተሰኘ።
“… ይህ መቅሰፍት በሀገራችን በ1911 ዓ.ም ወርዶ ብዙ ሰው ጨርሷል። ወረርሽኙ በጉንፋን በሳል ይጀምርና ትኩሳት፣ ማስለቀስ፣ ነስር፣ ተቅማጥና ተውከት ከማስከተሉ ባሻገር አእምሮም ያስት ነበር። ከዚያም በሦስት በአራት ቀን ይገድላል። የቤተሰቡ አባላት በሙሉ አልጋ ላይ ይውሉ ስለነበር አስታማሚ ስለሚጠፋ በርሀብና በውሃ ጥም ብዙ ሰው ይጎዳ ነበር። ከአራት ቀን ያለፈ ሕመምተኛ ግን ይድናል። አፍላው
በሽታ የቆየው ከኀዳር 7 እስከ 20፣ 1911 ዓ.ም ነበር። በየቀኑም ሁለት ሦስት መቶ ከዚህ በላይም ይሞት ነበር። በአንድ መቃብር ሁለት ሦስት አስክሬን እስከ መቅበር ተደረሰ። በዚህ ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና አስክሬን ተሸክሞ ወደቀብር የሚወስድ ሰው ማግኘት ችግር ነበር። ባል የሚስቱን፤ አባት የልጁን አስክሬን እየተሸከመ ቀበረ። መቃብር ይቆፍርና ቤቱ ሄዶ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል።
ቤተሰብ በሙሉ የታመመባቸው በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው። በበሽታው ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪና ልዕልት ወ/ሮ መነን በጠና ታመው ነበር፤ ንግስት ዘውዲቱም አልጠናባቸውም እንጂ ታመው ነበር። ከመኳንንት ከንቲባ ወሰኔ ዘማኒኤል፤ ከካህናትም የሐዲስ አስተማሪው አለቃ ተገኘ ሞቱ። አለቃ የመምህር ወ/ጊዮርጊስ ደቀ መዝሙር ነበሩ። የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሃ ሲያድሉ ሰነበቱ። የዚህን አይነት ትሩፋት የሰሩ መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሙሴ ሴደርኩይስት የተባሉ ስዊድናዊ ሚስዮናዊ አስተማሪ በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሃ መድሀኒት በመስጠት ትሩፋት መስራታቸውን ሰምቻለሁ። እኒህ ሽማግሌ ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ታመውና ሞተው ጉለሌ ተቀብረዋል።
የኀዳር በሽታ (ግሪፕ) በአዲስ አበባ ብቻ አልተወሰነም። ወደ ባላገር ተላልፎ ብዙ ሰው ፈጅቷል። ሆኖም በባላገር የአዲስ አበባን ያህል አልጠነከረም ይባላል። በዚህ በሽታ በመላ ኢትዮጵያ የሞተው የሕዝብ ቁጥር እስከ 40 ሺህ ድረስ መገመቱንም አስታውሳለሁ። በተለይ ኀዳር 12፣ የሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ። ሰለሆነም ወረርሽኙ እስከዛሬ በየዓመቱ የህዳር ሚካኤል ዕለት በየሰፈሩ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል ‘ ኀዳር ሲታጠን ‘ በሚል ይዘከራል። …” በማለት ‘ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ‘ ደራሲ መርስኤ ኀዘን ወ/ቂርቆስ ይነግሩናል። …” በአጠቃላይ ዛሬ አሽሞንሙነን አጋጊጠንና ኳኩለን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የምንለው ቀን እንዳይመጣ በአጭር ታጥቀን የዜግነት ድርሻችን መወጣት አለብን።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከዚህ ወረርሽኝ ይጠብቅ ! አሜን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com