እኤአ በመጋቢት ወር 1996 በማሌዥያ ኳላላንፑር የሚገኘው ፔትሮናስ ታውር በሴራስ ታወር ተይዞ የነበረውን የዓለም ረጅም ህንፃ ክብረወሰን ተረከበ:: ህንፃው ሙሉ በሙሉ በብረት የተሰራ ሲሆን፣ ርዝመታቸው 73 ነጥብ አምስት ሜትር የሆኑ ብረቶች በምሰሶነት ተተክለውለታል:: ታወሩ 88 የህንፃ ወለሎች ያሉት ሲሆን፣ 451 ነጥብ ዘጠኝ ሜትር ርዝማኔ አለው:: በእኤአ 2003 የታይዋኑ የታፒ የፋይናንስ ማዕከል የፔትሮናስ ታወርን ሪከርድ በማሻሻል በ508 ሜትር ርዝማኔ የዓለም ቁጥር አንድ ረጅሙ ህንፃ ለመበል በቃ:: የታይዋኑ የታፒ የፋይናንስ ማዕከል ክብረወሰኑን ከጨበጠ ከአንድ ዓመት በኋላ የቡርጃ ካሊፋ ህንፃ ግንባታ ተጀመረ::
በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የዱባይ ከተማ በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ጎብኚዎችን በመሳብ በዓለማችን ላይ እጅግ በጣም ዘመናዊ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ በማቅረብና የጥንት የዓረብ ባሕልን በማስተማር ላይ ይገኛል:: ዱባይ ከአንዲት የዓሣ አጥማጅ መንደር አንስቶ እስከ ዓለማችን ቱሪዝም እና የቅንጦት ማእድናት መገበያያ በመሆን በአሥርተ ዓመታት ውስጥ ያደገች ከተማ ስትሆን፣ በእንግዳ ማረፊያዎች፣ ግዙፍ የገበያ ማዕከሎች እና ልዩ ልዩ መስህቦች አካታ ይዛለች:: ከእነዚህ መካከል የዓለማችን ረጅሙ ሕንፃ የሆነው የቡርጃ ካሊፋ ይገኝበታል::
ባለቤትነቱ የሼክ መሀመድ ባን ራሽድ ብላይድ የሆነው ቡርጃ ከሊፋ ህንፃ በጣም ረጅም በመሆኑ ጫፍ ላይ የወጣ ሰው የትኛውንም የከተማ ክልል ሙሉ በሙሉ ማየት ይችላል:: በመላው ዓለም ዛሬ የሚታወቀው ይህ ህንፃ፣ የተጀመረው በአዲሱ ፕሬዝዳንት ካሊልያ ኢብኑ ዚይድ አልዳህ በፕሬዚዳንቱ ክብረ በዓል ላይ ነው::
ይህ በዱባይ የተገነባው ቡርጃ ከሊፋ በዓለም ላይ ትልቁን የህንፃ ሆኖ ከፍታው አንድ ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ስምንት ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል:: ሕንፃው ሙሉ በሙሉ የከተማው መኖሪያ፣ መናፈሻ፣ የገበያ ማዕከሎች፣ ሱቆች፣ ሬስቶራንት፣ ሆቴና የግል አፓርታማ ይዟል:: ይህን ግዙፍ ህንፃ ለመገንባት ከስድስት ዓመት ያነሰ ጊዜ ወስዶበታል:: ቡርጃ ካሊፋን ለመገንባት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል::
የዚህ ሕንፃ ፕሮጀክት የአሜሪካው ኩባንያ ስኪድሞውኦ ኦወንግስ እና ሜሪል እንዲሁም በአጠቃላይ ሂደቱን የተከታተለው ዋናው መሐንዲሱ እንደዚህ የመሰለ ዘመናዊ ሕንፃዎችን ለመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው የአድሪያን ስሚዝ ነው:: ፕሮጀክቱ የተጠናቀቀውና የተመረቀው እኤአ ጥር 4 ቀን 2010 ነው::
ቡርጃ ካሊፋ ቱሪስቶች በዋናነት ከሚጎበኙት ዘመናዊ መስህቦች አንዱ ሲሆን፣ በማማው ንድፍ ውስጥ 27 መስመሮች ይገኛሉ፤ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በከፍተኛው ማማ ላይ ያለው የንፋስ መከላለያ አንድ ነጥብ አምስት ሜትር ይሆናል:: እነዚህ መስመሮች ወደ ሰማይ ሲቃረብ የሕንፃውን ክፍል ክፍተት ይቀንሳሉ::
በዚህም ምቹ የሆኑ ገመዶች ተዘጋጅተዋል::
በአጠቃላይ ህንፃው የተሰራበት ቦታ ከ174 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ይሸፍናል:: እናም የህንፃው የውጭው ጫፍ የመጨረሻው በዓለም ከሚገኙ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ቁመት 232 ሜትር ይረዝማል:: ውስጣዊ ንድፉ ሙሉ በሙሉ ከእስላማዊው ሕንፃ ምሰሶዎች ጋር ተመሳሳይ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ ነው:: በቡርጃ ካሊፋ ውስጥ ፎቶግራፍና እጅግ በጣም ብዙ የተለያዩ የስነጥበብ ቁሳቁስ ይገኛሉ:: ቡርጃ ካሊፋ የቱሪስት መስህብ ብቻ ሳይሆን የዱባይ ድምቀትም ጭምር ነው:: በሺዎች የሚቆጠሩ አርክቴክቶችና መሐንዲሶች በዱባይ በሚገኙ ፕሮጀክት ላይ በጥንቃቄ በመስራታቸው ከተማዋ ውብ እንድትሆን
አድርጓታል::
በህንፃው ላይ የሚገኘው ሆቴል አርማኒ ዓለም አቀፋዊው ፋሽን ዲዛይነር የሆነው ጆርጅ አርማኒ ባለቤትነት የተያዘ ነው:: ሆቴሉ 304 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በሆቴሉ ለአንድ አዳር ከ370 ዶላር እስከ 1 ሺህ 600 የአሜሪካ ዶላር የሚያስከፍሉ የቅንጦት መኝታዎች ናቸው:: ምንም እንኳን ከፍተኛ ዋጋ ቢኖረውም እንኳን በቡርጃ ካሊፋ የሚገኘው ምግብ ቤት ለእንግዶች በጣም ተወዳጅ ቦታዎች አንዱ ነው:: ምግብ ቤቱ የሚገኘው በህንፃው ከፍታ በ442 ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን፣ በመስኮቱ በኩል የዱባይ ከተማ አጠቃላይ ሁኔታ ማየት ያስችላል:: ይሁን እንጂ በዚህ ሬስቶራንት ውስጥ ዝቅተኛ የምግብ ክፍያ መጠን መቶ ዶላር ነው::
በህንፃው ላይ የሚገኘው ፏፏቴ የቱሪስቶች ሌላኛው መስብ ነው:: ከህንፃው ፊት ለፊት በሚገኝ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ውስጥ የሚገኘው የሙዚቃ ፏፏቴ በዓለም ላይ ሁለተኛውን ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ በየቀኑ ብዙ የውጭ አገር ቱሪስቶች
ይጎበኙታል:: በቡርጃ ካሊፋ ህንፃ ላይ ከተማውን ለማየት እንዲቻል ክፍት የመመልከቻ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል:: የመመልከቻ ቦታዎቹ ከመሬት 555 ሜትር ከፍ ያለ ቦታ ላይ የሚገኝ ነው:: ከተማውን ለመመልከት የኤሌክትሮኒክስ ቴሌስኮፖች ተዘጋጅተዋል::
የቡርጃ ካሊፋ ህንፃ ሲገነባ ከተለያዩ አገራት የመጡ ከአስራ ሁለት ሺህ በላይ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከ26 ሺህ በላይ ቁርጥራጭ መስታወቶች ለህንጻው ውጫዊ ክፍል ማሳመሪያነት ውለዋል:: በህንጻው ላይ የሚገኙት መኖሪያዎችና ሆቴሎች በመስታወቶቹ የተሸፈኑ ናቸው:: አጠቃለይ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለማፅዳት የሶስት ወራት ጊዜ ፈጅቷል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27/2012
መርድ ክፍሉ