አሁን ባለንበት ወቅት አለምን ያዳረሰው ወረርሽኝ ባህርን አቋርጦ በሀገራችን ከገባ ሳምንታት አስቆጥሯል። ታዲያ ይህን ወረርሽኝ እንዴት ተቀበልነው? በምንስ መልኩ ለማክሰም አስበናል? እንዲሁም ማህበረሰባችን ዘንድ ያለው የአመለካከትና የግንዛቤ ልዩነቶች ምን ይመስላሉ? እስኪ ተከታዩን የባልና ሚስት ወግ እንከታተል።
ወ/ሮ ሀሊማ፡- አንቱዬ ጨነቀኝ እኮ… ኧረ አንድ ነገር ይበሉኝ!
ጋሽ አምበርብር፡- ምነው ምን ሆነሻል?.. በግድ ቤቴ ሀዘን ካልገባ ነው የምትይው!
ወ/ሮ ሀሊማ፡- በሽታው ነግሶ፤ ሀዘን ወርሶ አለምን ሲያጥመለምል አይታዮትም እንዴ?
ጋሽ አምበርብር፡- አንቺ ሴት በሽታ፡ በሽታ እያልሽ የጀግኖችን ሀገር፤ የጥቁርን አልበገር ባይነት ምነው ካልካድኩ ገደል ካልሰደድኩ አልሽ?
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ድንቄም ጥቁር! እንደውም ይኸውሎት… ይህ ወረርሽኝ ማንንም አይምርም። ጥቁር ነጭ፣ ሀብታም ድሀ፣ ወንድ ሴት፣ ትልቅ ትንሽ ሳይለይ ሁሉንም የሚያጠቃ ነው።
ጋሽ አምበርብር፡- አሁን ወግሽን ተይና ጭሱን አጫጭሰሽ ቤቱን ፏ አርገሽ ቆይኝ፤ በይ እኔ ባልንጀሮቼ ዘንድ ሄጄ ተጨዋውቼ እመጣለው።በሽታ የሚባል እኛ ጋር የለም አልኩሽ፤ ይህ የፈሪዎች ቧልት ነው።
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ኧረ ተለመኑኝ አንቱ ሰውዬ! እንደው ይሄን በሽታ የዋዛ አድርገው አይመልከቱት፣ ጠንቀቅ ቢሉ ይበጃል
ሁሉም የየራሱን ሀሳብ ሰንዝሮ ሲያበቃ… ጋሽ አምበርብር አሻፈረኝ ብለው የወረርሽኙን አስከፊነት ቦታ ሳይሰጡት፤ ሬድዮም ቴሌቭዥኑም ሲያሳስብና ሲያስታውስ የከረመውን ዘንግተው ከባለቤታቸው ጋር ብዙ ተባብለው ወደ ባልንጀሮቻቸው ዘንድ በድፍረት አቀኑ።
ወይዘሮ ሀሊማ የወረርሽኙ ጭንቀት እንደ ኩፍኝ ሰውነቷን ወሯት እህል በቅጡ ከተመገበች፤ እንቅልፍ በአግባቡ ከተኛች ሳምንታት አስቆጥራለች።ስራዬ ብላ
ስለኮሮና ቫይረስ መረጃ ለመስማት ጆሮዋን ሬዲዮ ላይ ጥዳ ስትሸበር ትውላለች፤ ታድራለችም።በበሽታው እንደተጠቃች ማሰብ ከጀመረች ሰንብታለች።ነገረ ስራዋ ሁሉ ምልክቶቹን እያጤኑ ያለባትንም የሌለባትንም እያመሳሰሉ “ኮሮና..” አለብኝ በማለት ድምዳሜ ላይ የደረሰች ትመስላለች።ጋሽ አምበርብር ከሄዱበት ተመለሱ።
ጋሽ አምበርብር፡- እንዴት ዋልሽ..
ወ/ሮ ሀሊማ፡- አይይይ… እህ …ተወኝማ!
ጋሽ አምበርብር፡- ደግሞ ምን ሆንኩ ነው የምትይው… አያልቅብሽ!
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ይኸውልህ… ሰውነቴም አተኩሷል፣ እራሴንም ይዞኛል፣ ያለማቋረጥ እያሳለኝ ነው።አዬ! እንደው ምንም አልቀረኝም ብቻ ኮሮና ይዞኛል…
ጋሽ አምበርብር፡- ጀመረሽ ደግሞ
ወ/ሮ ሀሊማም የበሽታው ሰለባ እንደሆኑ በማሰብ የቀን ተቀን እንቅስቃሴያቸውን በድብርትና በጭንቀት እንዲሁም ከዛሬ ነገ እሞታለሁ በማለት ሲቆዝሙ ይውላሉ።እንዲሁም ጋሽ አምበርብር ለበሽታው ሊሰጠው የሚገባውን ጥንቃቄና አስተዋይነት ዘንግተው አካላዊ እርቀታቸውን ሳይጠብቁ ኑሯቸውን ቀጥለዋል።በዚህ መሀል የቅርብ ወዳጃቸውና ጎረቤታቸው አቶ ዓለሙ ይመጣሉ።
አቶ አለሙ፡- ደህና ዋላችሁ
ጋሽ አምበርብር፡- ፈጣሪ ይመስገን…እንዴት ነህ.. ግባ እንጂ
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ምን እግር ጣለህ… እንደው አሁን ሰው ቤት የሚመጣበት ዘመን ሁኖ ነው… ምን አለ እንደው አርፋችሁ ብትቀመጡ፤
ጋሽ አምበርብር፡- እንግዳ አይምጣ እያልሽ ነው እንዴ… በሌለ በሽታ ጭራሽ ወዳጅ ከዘመድ አቆራርጠሽ ልታርፊው ነው?
አቶ አለሙ፡- ያስጨነቀኝ የማማክራችሁ ነገር ነበር።ምን መሰላችሁ፡- ትናንት ሀገር ሰላም ነው ብዬ ወደ መስሪያ ቤቴ አቀናሁ:: የስራ ባልደረባዬ እንዲሁም የቅርብ ወዳጄ የሆነው ፋሲል በኮሮና ቫይረሰ ከተያዘ ግለሰብ ጋር ንክኪ አለህ ብለውት የጤና ባለሙያዎች ለይቶ ማቆያ ቦታ ወሰዱት፤ ከምርመራው በኋላ በኮሮና እንደተጠቃም አረጋግጠዋል።
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ወይ ጉድ! ከዛስ ምን ደረሰ ጉዳዩ?
አቶ አለሙ፡- ዋናው ጉድ ምን መሰላችሁ ከፋሲል ጋር ቅርርብና ንክኪ ያለውን ሰው እያጣሩ እየወሰዱ ነው።እኔም አንዱ ተጠርጣሪ ስለሆንኩኝ የሚያደርስብኝን መገለል፤ ከቤተሰብ መነጠል፤ የሰው መጠቋቆሚያ መሆንን ፈርቼ አምልጫለሁ።አንዳያገኙኝም በቻልኩት መጠን እራሴን ደብቂያለሁ።
ጋሽ አምበርብር፡- ደግ አረግክ.. ዝም ብለው እኮ ነው የሚያዋክቡን፤ እኛን አይዘንም የፈጣሪን ሀገር አይደለም ሊነካ…
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ይሄን ቅዠቶን ያቁሙ… አሁንስ በዛ…
አቶ አለሙ፡- በሉ ደህና ሁኑ እኔ ልሂድ
ብሎ እንደወጣ ወ/ሮ ሀሊማም በአይነቁራኛ ትከታተለው ጀመር።አቶ አምበርብርም ‘አልቀረብሽም’ በሚል አስተያየት እየተመለከቷት ወዲያውኑ አቶ አለሙ የግቢው ደጃፍ እንደደረሰ ከአንዴም ሶስቴ አከታትሎ አስነጠሰ።ይህን ጊዜ ነበር የወ/ሮ ሀሊማ ጆሮ እንደ አንቴና የቆመው፤ ሁለመናዋም የተሸበረው።
ወ/ሮ ሀሊማ፡- ይህን ነበር የፈራሁት… ተያይዘን አለቅናታ!
አቶ አምበርብር፡- ይማርህ ወዳጄ ይማርህ..
በማለት በባለቤታቸው ፍርሀት አሾፉ።ወ/ሮ ሀሊማም ምላሽ ሳይሰጡ አፋቸውን በሻሻቸው ከልለው፣ እጃቸውን በላስቲክ ሸፍነው አቶ አለሙ የተቀመጠበትን፣ ያረፈበትን፣ የተነፈሰበትን ሳይቀር እያደኑ ያፀዱ ጀመር።
ከሶስት ቀናት በኋላ አቶ አለሙ የህመሙን ምልክት እራሱ ላይ እያስተዋለ ቢሆንም ብርድ ይዞኝ ነው፣ ጉንፋንም ይሆናል እያለ እራሱን ለማሳመን ይሞክራል።የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ያለምንም ጥንቃቄ ቀጥሏል።ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ይሄዳል፣ በተደጋጋሚ ጓደኞቹን ያገኛል፣ ታክሲም ይሳፈራል።
ወ/ሮ ሀሊማ የአቶ አለሙ ነገር በጣም አስጨንቋታል።ከማስጨነቁም ባሻገር ከባለቤታቸው ጋር የቀን ተቀን ጭቅጭቃቸው ሆኗል።ይህ ነገር ስር ሳይሰድ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ በማለት ወደ ጓዳ ገብተው ወ/ሮ ሀሊማ ስልካቸውን አንስተው 8335 በመደወል ስለ አቶ አለሙ ሁኔታ እንዲሁም ስለሚኖሩበት አካባቢ ተናገሩ።አሁን
በከፊልም ቢሆን ልባቸው አርፏል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግርግርና ጫጫታ ሲሰሙ ሁለቱም ተያይዘው ከቤታቸው የወጡት።ነገሩንም ትኩር ብለው ሲመለከቱ ነበር።
አቶ አለሙ፡- እባካችሁ ተውኝ እኔ ደህና ነኝ።የምትሉት ነገር በፍፁም ልክ አይደለም።ከማንም ጋር ንክኪ የለኝም .. ከቤት እንኳ ወጥቼ የማላውቅ ሰው ነኝ።
የጤና ባለሙያዎቹም ለማምለጥ እየታገለ መሆኑን ሲረዱ እንዲረጋጋ በማሳሰብ ይዘውት ይሄዳሉ።ይህንን ሁሉ ነገር የተመለከቱት ጋሽ አምበርብርና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሀሊማ በድንጋጤ በቆሙበት ደርቀው ቀሩ።አቶ አለሙ ተይዞ ወደ ለይቶ ማቆያ ተወስዶ ያለበትን ምልክቶች አጢነው እንዲሁም በላብራቶሪ ምርመራ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆኑ ተረጋግጧል።
ጋሽ አምበርብር ወደ ራሳቸው መለስ ያሉ ይመስላሉ።ወ/ሮ ሀሊማም ጭንቀትና ፍርሀቱ እያደረ አገርሽቶባታል።ከመጠን ያለፈው ጥንቃቄዋና ያለ ዕረፍት የምታገኘው መረጃ እንደቀጠለ ቢሆንም የአቶ አለሙ በበሽታው መያዝ፣ አካላዊ ርቀቱን ሳይጠብቅ የነበረ ቅርርባቸውን እንዲሁም የባለቤታቸውን ግድየለሽነትና ስለ ጥንቃቄ ጉድለቱ ስታስብ ይባስ ትጨነቃለች።
ጋሽ አምበርብር፡- ይህ ነገር እውነት ሁኖ መቅረቱ ነው.. ግን እንዴት ይሆናል የፈጣሪን ሀገር፣ የጀግኖችን መንደር ከቶ እንዴት ይሆናል…
ወ/ሮ ሀሊማ፡- እስኪ አሁን እንኳ ይሸነፉ.. አፍጥጦ የመጣውን ችግር ጆሮ ዳባ ብለው እውነታውን አሻፈረኝ ብለው እዚህ ደርሰዋል… የአቶ አለሙን ነገር አይተው እንኳ አይማሩም?
ጋሽ አምበርብር ከራሳቸው ጋር ሙግት ይዘዋል።የአቶ አለሙም ጉዳይ እውነት ስለመሆኑ ያመኑ ይመስላሉ።በዚህ ወቅት ነበር የእነ ጋሽ አምበርብር ቤት የተንኳኳው።ባለቤታቸውም በሩን እንደከፈተችው ቫይረሱ ከያዘው ሰው ጋር ንክኪ እንዳላቸውና ወደ ለይቶ ማቆያ መሄድ እንዳለባቸው ተነግሯአቸው እሷንም ባለቤቷንም ይዘዋቸው ሄዱ።
እስቲ እራሳችንን እንመልከት… የቱ ጋ ነው ያለነው?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2012
ሀናን ሁሴን፣ ሣራ መሐመድ፣ መልከብርሃን ብርሃኑ
(ሳይክ-ኢን-አክሽን ክለብ፤ ሳይኮሎጂ ት/ቤት፣አ.አ.ዩ)