የኮረና ቫይረስ በዓለም ሥጋት ሆኖ ሁሉም በድንበሩ፤ በአገሩ ከትሟል፡፡ ነገሮች በየቀኑ እየተቀያየሩ ለማመን የሚከብዱ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ኃያላንም፣ ልዑላንም፤ ድውያንም፣ ጤነኛውንም ሁሉ ስለዚህ ጉዳይ እንዲጨነቅ እንዲጠበብ አድርጓል ኮረና፡፡ በተለይ ደግሞ የቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶችና ሁነኛ መፍትሄዎች በእርግጠኝነት ይህ ነው ብሎ መናገር አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት በዓለም አራቱም ማዕዘናት አዝናኝም አሳዛኝም ነገሮች እየተሰሙ ነው፡፡ እኛም ለእናንተ ‹‹እንዲህም ይኖራል፤ እንዲህም ይታሰባል፤ እንዲህም ይደረጋል፣ እንዲህም ይከወናል›› ስንል ከተለያዩ የወሬ ምንጮች ያገኘነውን መረጃ አቀበልናችሁ፡፡
ቅብጠት ወይስ አምሮት
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ አገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብታውጅም ቢራ ያጡት ደቡብ አፍሪካውያን ድንበር ዘለው ከጎረቤታቸው ዙንባቤ ቢራ እየገዙና እየጠጡ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ቡላዋዩ የተሰኘው ሚዲያ እንደዘገበው ከዙንባቤ ድንበር በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሙሲና ከተማ ያሉ አንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያን ለጊዜው በድንበር የተተከለውን አደገኛ አጥር በመዝለል ወደ ዙንባቤ በመሄድ ቢራ እየገዙና እየጠጡ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሲሄዱ ተስተውለዋል። ይሄም ተግባር ሰሞኑ ትንሽ ጋብ ያለ ቢመስልም ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠጥ ቤት ከዘጋች ጀምሮ በስፋት እየተስተዋለ ነበር ሲል ቡላዋዩ አብራርቷል፡፡ አንዳንዶቹም ገንዘብ የሌላቸው ደቡብ አፍሪካውያን ከዙንባቤ የግሮሰሪ ባለቤቶች የምግብ ዘይት በማምጣት በቢራ እየቀየሩ እንደሚገበያዩ የአካባቢ ነዋሪዎች አይተናል፤ ሰምተናል ማለታቸውን ለወሬ ምንጩ መረጃ ሆነዋል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን የቢራ አምሮታቸውን ሙሉ ለሙሉ ባይወጡትም ለጊዜ እየተጎነጩት እንደሆነና ይህ ቫይረስ ከቢራ ጋር ፍቺ እንዲፈፅሙ ጫናውን ቢያበረታባቸውም ደቡብ አፍሪካውያን የቢራ አፍቃሪዎች ግን ህይወታቸውን ለአደገኛ ሁኔታ ጥለው ቢራ ለመፈለግ መፋነናቸውን አልተውትም፡፡
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከቤት ያልወጡት የ93 ዓመቷ አሜሪካዊት አዛውንት ጥያቄ ደግሞ ለቢራ ያላቸው ፍቅር በእጅጉ አነጋጋሪ ሆኗል። አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት አትውጡ ካለቻቸው ነዋሪዎቿ በፔንስልቫንያ የሚኖሩት ኦሊቭ ቪሮኒሲ ከቤታቸው ደጃፍ ላይ ሆነው በአንድ እጃቸው የቆርቆሮ ቢራ ይዘው በሌላ እጃቸው ደግሞ ፅሁፍ አንግበው ‹‹ተጨማሪ ቢራ›› እፈልጋለው በማለት በፎቶ አስደግፈው በፌስ ቡክ የለቀቁት ፎቶ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዓለም ላይ አይተውታል ሌሎችም ተቀባብለውታል።
ፎቶው ከተለቀቀ በኋላ በርካታ ሰዎች በሴትዮዋ ድርጊት ተገርመው ምላሽ ሰጥተዋል። የቢራ ፍቅር እንዲህ እያነሆለላቸው ከደጃፋቸው ላይ እስረኛ ማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ምግብ ሳይሆን ቢራ ናፋቂዋ አዛውንት ኮረና ቫይረስ ጠፍቶ ነፃነቱን ቢያገኙ ስንት ቢራ ይጠጡ ይሆን፣ እሳቸውንም፤ እኛንም የከርሞ ሰው ካለን አዛውንቷን መጨረሻ እናየው ይሆናል፡፡
ሞት እራሱ ይሙት
ባንጋላዲሾች ደግሞ ሞት እራሱ ይሙት ብለው የወሰኑ ይመስላል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት ያንዣበባት ይህች አገር ሰሞኑን በአንድ ቀብር ላይ ከ100ሺ በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። ይህ የባንግላዴሺያውያን ድርጊት ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ከታሰበው በላይ እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
ማኡላና ዙባየር አህመድ የተባለ የሙስሊም እምነት ታዋቂ መምህር ሞተው ቀብሩ የተፈፀመ ሲሆን በቀብሩም ላይ ከ100ሺ ሰው በላይ ሰዎች መገኘታቸው የዓለም ሚዲያን ቀለብ እንዲስብ አድርጎታል። ይሄም በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ከአምስት ሰዎች በላይ ለፀሎት እንኳን በአንድ ላይ መገኘት የተከለከለባት ባንግላዲሽን የመምህሩ ቀብር የተገኙ ሰዎች በቫይረስ ከተያዙ ስርጭቱን በማባባስ ለሀገሪቷ ራስ ምታት እንዳይሆኑ ስጋት ቢጥልም በዓለማችን ከፍተኛ የሙስሊም ማህበረሰብ የሚገኝባት ባንጋላዲሽ ግን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር እንዲሉ›› መምህራቸውን እስከወዲያኛው ለመሸኘት ከኮረና ጋር ተጋፍጠውና ተፋጠው ራሱ ኮረና ይሙት ያሉ ይመስላል፡፡
አልተገናኝቶም
ዓለም መልኳ እንደ ነብር ዥንጉር ጉር ነው፡፡ ኮረና ቫይረስ በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና ቤት አልባ ሠዎችን ለከፋ አደጋ እንዳይጥል መንግስታት ባላቸው እቅም ሁሉ ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ መጠለያ ችግር ገጥሟቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ወዲህ ግን በጀርመን በኮሮና ምክንያት ከቤት አለመውጣት መመሪያን በመቃወም 300 ያክል ሰዎች ሰልፍ ወጥተዋል- ሰሞኑን፡፡
የኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት የጀርመን መንግስት ያወጣውን ከቤት አለመውጣትን መመሪያን በመቃወም ‹‹አሁንስ ሰለቸን መንግስታችን ወደ አምባገነን እየተቀየረ ነው›› በማለት 300 ያክል ሰዎች በሙኒክ በሚገኘው በሮዛ ሉክሰምበርግ ፕላትዝ አደባባይ ህጋዊ ያልሆነ ሰልፍ አካሂደዋል። ህግ ማስከበሩ ግድ የሆነበትና ከበላይ አለቆቹ ቀጭን ትዕዛዝ የተቀበለው የአገሬው ፖሊስ የተወሰኑ ሰልፈኞች ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመኪና ወስዷል። ሰልፈኞቹ ኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት የተከለከለውን እርቀትን ጠብቆ መጓዝን ግድ አልሰጣቸውም፤ ይልቁንስ ተሰብሰበው ነበር ሰልፉን ያካሂዱት ሲል የዘገበው አርቲ ሚዲያ የተሰኘው የወሬ ምንጭ ነው።
ወዲህ ደግሞ በናይጄርያ በኮሮናቫይረስ ከሞቱት ሰዎች ይልቅ ከቤት አለመውጣት የታዘዘውን መመሪያን ጣሳችሁ ተብለው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር መብለጡ ‹‹ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ›› ሳያስብል አልቀረም፡፡
ቫንጋርድ ጋዜጣ የሀገሪቱ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊን ቶኒ ኡጁኩውን ጠቅሶ እንደዘገበው በኮሮናቫይረስ ስጋት የሀገሪቱን ከቤት አለመውጣትን መመሪያ ጥሰው የተገኙ 18 ሰዎች በፀጥታ ሀይሎች መገደላቸውን ጠቅሶ በሀገሪቱ ግን በቫይረሱ እስከ አሁን 11 ሰው መሞቱን ጠቅሷል። ይሄም የፀጥታ ኃሎች ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ እየወሰዱ አለመሆኑን ያሳያል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ዕፅ ተጠቃሚዎችና አዘዋዋሪዎች ደግሞ ሌላ ዓለም ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፈረንሳይ ከስፔንና ከሆላንድ የሚያዋስናትን ድንበር ስለዘጋች እና በድንበሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ የአደንዛዥ እፅ ስለማይተላለፍ የዕፅ አዘዋዋሪዎች አቅርቦቱ የቀነሰውን አንዱን ኪሎ ኮኬን እስከ 32ሺ ዩሮ እየሸጡ ሲሆን ይሄም ኮሮናቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ባለው ዋጋ ላይ የሰባት ሺህ ዩሮ ጭማሪ አሳይቷል ሲል አርቲ ሚዲያ ዘግቧል። ኮሮናቫይረስ በፈረንሳይ ለአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ምቾት ሳይሰጥ እንዳልቀረም እየተነገረ ነው፡፡
ሰሞኑን በኢራን ‹‹የጦር ሰራዊት›› ቀን ላይ ወታደሮች፣ የጦር መሳሪያና ጀቶች በአደባባይ አልታዩም። ይልቁንስ በኮሮናቫይስ የሞቱ ፣ የታመሙ እና ቫይረሱ ከገባ ቀን ጀምሮ ለተዋደቁ ዜጎቿን ለማሰብ ወታደሮች የህክምና ጋዎን በማድረግ በተንቀሳቃሽ ክሊኒክ የሆስፒታል እቃዎችን እንዲሁም መድሃኒቶችን ወደ መንገድ በማውጣት ምንም ታዳሚ በሌለበት መንገድ በመኪና በማዘዋወር ቀኑን አስባለች። ‹‹ለጤናችን ስንል ትዕይንቱን ሰው እንዲታደመው አላደረግንም። አሁን ሀገራችንን የገጠማትን ጠላት እየተዋጉልን ያሉት ዶክተሮችና ነርሶች ናቸው። ትልቅ ክብር ይገባቸዋል›› ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ ተናግረዋል።
ከሦስት ቀናት በፊት ደግሞ ኢራን የመጀመሪያውን ወታደራዊ ሳተላይት ወደ ኦርቢት አስወንጭፌ አስቀምጫለው ብላለች። ታዲያ እንደ አይጥና ድመት ባላንጣዋ አሜሪካ ይህን ትዕቢትሽን አበርድልሻለሁ፤ ሥራሽም ይኮነናል ማለቷን የዘገበው ሬውተርስ ነው፡፡
የገንዘብ ነገር
አይ ኤም ኤፍ አፍሪካ የ114 ቢሊዮን ዶላር ለጤና እና ለማህበረሰባዊ ሥራዎች ትፈልጋለች ብሏል። ብሉንበርግ እንደዘገበው አፍሪካ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ የኮሮናቫይረስን ጨምሮ ለጤና እና ለማህበረሰብ ስራዎች 114 ቢልዮን ዶላር ትፈልጋለች። ለዚህም የግልም ሆነ ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ብድር በመሰረዝ፣ የእዳ መክፈያ ጊዜን በማራዘምና አዲስ የገንዘብ ድጋፍና ብድር በመስጠት ሊያግዟት ይገባል ሲል ዘግቧል።
ወዲህ ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ አናደርግም፤ ድርጅቱ የበላይ ሰው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም መረጃ ደብቆናል ብለው ወቀሳ ማቅረባቸውን ተከትሎ በተቃራኒው ጎራ የቆሙ ደግሞ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡
ለአብነትም ታዋቂዋ አርቲስት ሌዲ ጋጋ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን በኮቪዲ 19 በሰሩት ሥራ ‹‹ልዕለ ሀያል›› በማለት አወድሳቸዋለች፡፡ የፖፕና የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኟ እንዲሁም የፊልም ተዋናዩዋ ሌዲ ጋጋ የዓለም ጤና ድርጅትን ኃላፊ ኢትዮጵያዊውን ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን በኮቪዲ 19 እየከወኑ ያሉትን ስራ “ ልዕለ ሀያል” ወይም ‹‹super hero›› በማለት ዶክተሩ ቫይረሱ እጅግ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር ላደረጉት ስራ ሊመሰገኑ እንደሚገባ ተናግራለች።
አሳሳቢው ነገር
በኒዮርክ ሁለት ድመቶች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የአሜሪካ በሽታን የመቆጣጠርና መከላከል ማእከል አስታውቋል። ከቤት እንስሳትም ቫይረሱ የተገኘባቸው የመጀመሪያዎቹ እንስሳት ሆነዋል። አንደኛዋ ድመት ባለቤቷ የሆኑት የቤተሰብ አባላት በቫይረሱ እንዳልተያዙ የተገለፀ ሲሆን ምን አልባት ድመቷ ከሌላ ቦታ በቫይረሱ ተለክፋ ሊሆን ይችላል የሚል መላምት ተሰጥቷል። የአንደኛው ድመት ካሳደጉት ቤተሰቦች ውስጥ አንድ ሰው ቀድሞ በቫይረሱ ተገኝቶበት ነበር ተብሏል ሲል ሲኤን ኤን ዘግቧል። ድመቶቾ በኒዮርክ ከዚህ በፊት ቫይረሱ ከተገኘባቸው ነብር እና አንበሳ ከሚገኙበት ለይቶ ማቆያ ተወስደዋል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ የነገሮች አቅጣጫ አይታወቅምና እኛም ከቤት እንስሳትን ጨምሮ ቀረቤታችን የተገደበ እንዲሆን ይጠቁመናል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 / 2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር