የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናን ቫይረስ በቻይና ከተከሰተና ወርሽኝ መሆኑ ከአረጋገጠ፤ ይህ ወረርሽኝ የአለም ህዝቦች የጤና ስጋት መሆኑን ከተናገረ ወራቶች ተቆጥረዋል። ታዲያ የተለያዩ አገራትን ኮቪድ 19 (የኮሮና ቫይረስ) ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ህዝባቸውን ለማስጠንቀቅ እና ለማስተማር የተለያዩ ስልት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ይህ ብቻ አይደለም አገራቱ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሲኖር የመንከባከብ ስራ ለመስራት አቅማቸው በፈቀደ መልኩ ደፋ ቀና እያሉ እንደሆነ የሚታወቅ ነው።
ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያም ከመግባቱ በፊት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ የጤና ምክረ ሃሳቦች በአስተምሮ መልዕክት ሲቀርቡ ቆይተዋል። ወረርሽኙም በአገሪቱ ከተከሰተም በኋላ መንግስት አቅሙ እስከፈቀደለት ድረስ ተጠቅሞ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል።
በሽታው በጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ያለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ችግሩ የጋራ እንደመሆኑ የሚወሰደውም የመፍትሄ እርምጃ የጋራ ሊሆን እንደሚገባ እሙን ነው። ታዲያ የዚህን ወረርሽኝ ስርጭት ለመቆጣጠር ብሎም ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ለጥቂት ተቋማት፣ ለመንግስት እንዲሁም ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚተው ባለመሆኑ ማንኛውም ህብረተሰብ የየትኛውም ሙያ ባለቤት ይህንን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እና ለማስቆም የራሱ የሆነ ሚና ያለው መሆኑ ልብ ሊል ይገባል።
ይህንን ታዲያ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ የኪነ ጥበብ ሙያ ማህበራት ተወካዮች የተወጣጣ ብሔራዊ የሚዲያ እና የኪነ ጥበብ ግብረ ሀይል እንደተቋቋመ ይታወቃል። የዚህ ግብረ ሀይል አስፈላጊነት ከዚህ በፊት ያሉ ጥሩ ልምዶችን በተደራጀ እና ተከታታይ በሆነ መልኩ የመከላከል ትምህርቶችን ለማስቀጠል እና ፈጠራ የታከለበት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ሙያዊ ስነ ምግባርን የተከተለ፣ ቅርጹን እና አቀራረቡን ይዘቱን፣ ግዝፈቱንና ደረጃውን እንዲጠብቅ በማድረግ የጤና ምክረ ሀሳቦችን እና ቁልፍ መልዕክቶችን አዘጋጅቶ ለማህበረሰባችን ግንዛቤ መፍጠር ነው።
በዚህ ግብረሃይል የተለያዩ እቅዶች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል። ከእነዚህ መካከል በተለያዩ የኪነ ጥበብ እና የፈጠራ ስራዎች ልዩ ልዩ የግንዛቤ ስራዎችን ማዘጋጀት እና ጥቅም ላይ ማዋል አንዱ ሲሆን፤ የጎዳና ላይ የግንዛቤ የማስጨበጫ፣ የቅስቀሳ ስራዎችን በታዋቂ ሰዎች ማከናወን እንዲሁም በአንድነት ፓርክ ሰው አልባ ኮንሰርት በቀጥታ ስርጭት በማካሄድ በሁሉም የመገናኛ ብዙሃን መልዕክት ማስተላላፍ የሚሉት ይገኙበታል።
ግብረሀይሉ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ከዕቅዶቹ መካከል አንዱ የሆነውን በአንድነት ፓርክ ሰው አልባ ኮንሰርት ማዘጋጀት የሚለውን ተግብሮት ነበር። ይህ ሰው አልባ ኮንሰርት ብሔራዊ የሚዲያ እና የኪነ ጥበብ ግብረ ሀይል ጋር አብረው በመሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር ተሳትፈውበት ነበር።
ይህ ሰው አልባ ኮንሰርት በተካሄደበት ወቅት ተባባሪ አካላት ከሆኑት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አንዱ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በኮንሰርቱ ላይ በመገኘትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በንግግራቸው እንዳስቀመጡትም አገሪቱ አሁን ያለችበት ጊዜ እንደሌሎቹ አገራት አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባቷ በፊት፤ ወረርሽኙ እጅጉን ሳይዛመት፤ ሌሎች አገራት ላይ ካደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ትምህርት ተወስዶ በኢትዮጵያም ይህ እንዳይከሰት ሰፊ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል የሚል ነው። ይህ የኪነ ጥበብ ዝግጅትም ከነዚህ ጥረቶች አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ልክ እንደ ኪነ ጥበብ እና የሚዲያ ባለሙያዎች ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ ማህበረሰቡ ወረርሽኙን እንዲከላከልና እንዲጠነቀቅ ለማድረግ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬስ ሴክሬቴሪያቱ አቶ ንጉሱ አክለው ኪነ ጥበብ ህዝብ ሲደነግጥ የማትደነግጥ እንደሆነች ጠቁመው ይልቁኑ የኪነ ጥበብ ሚና የፈራን የምታረጋጋ እንደመሆኗ የአገሪቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ተሰጧቸውን ለዚሁ አላማ ማዋላቸው የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል። ይህም አልፎ ደግሞ ለመመሰጋገን ያብቃን በማለት መልዕታቸውን አስተላልፈዋል።
ሌላው ተባባሪ አዘጋጅ ሚኒስትር መስሪያ ባህል እና ቱሪዝም ነበር። የሚኒስትር መስሪያ ቤቱን በመወከል ንግግር ያደረጉት ዶክተር ሂሩት ካሳው አገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ ችግሮች መፈተኗን አንስተዋል። የወቅቱ ትውልድም ችግሮችን ተጋፍጦ በማሸነፍ ብሎም የተበላሸውን አስተካክለውም እንዳለፉ ተናግረዋል። በመሆኑም በዚሁ ወቅት የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመግታት እና ለማቆም በአንድነት በርትተን እና በተባበረ ክንድ የሚጠበቅብን የጤና ምክሮች እና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ አክለው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እና ለመግታት በሚደረገው ጥረት አገራቸውን በትጋት እያገለገሉ ከሚገኙ አካላት መካከል የሰላም ሚኒስትር የሆኑትን ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልንና የጤና ሚኒስትሯን ዶክተር ሊያ ታደሰን እንዲሁም የኪነጥበብ ማህበረሰቡን በጥቅሉ አመስግነዋል።
በእለቱ እንግዳ የነበሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ነበሩ። እርሳቸውም በመልክታቸው ፖለቲካም ሆነ ሌላ ስራ የሚሰራው አገር እና ህዝብ ሲኖር ነው የሚል ሃሳብ በማንሳት ትኩረታችንን የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ላይ መሆን አለበት የሚል ጠንካራ ንግግር አድርገዋል።
ከታዋቂ አርቲስቶች መካከልም አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ እመቤት ወልደ ገብርኤል፣ ሃናን ታሪክ፣ እፀ ህይወት አበበ እና ቴድሮስ ሞሲሳ ቫይረሱን በመከላከል ዙሪያ የየራሳቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል። ከዚህ የመግቢያ ንግግሮች ምስጋናዎች እና ምክሮች በኋላ ነበር በጥበብ የማስተማር ድግሱ የተጀመረው። በዚህም ታዋቂ እና በኪነ ጥበብ አንቱ የተባሉ ግለሰቦች የጥበብ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል። እነዚህ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንደየ ዘመን ልዩነታቸው በቡድን በመጣመር ነበር ስራዎቻቸውን ያቀረቡት።
ቀድሞ የተወደዱ ስራዎቻቸውን ለወረርሽኙ ማስተማሪያ እንዲሆን እንደ አዲስ ግጥሙን እና ሙዚቃውን በመስራት በዕለቱ በየቤቱ ሆኖ በቀጥታ ለሚከታተለው ታዳሚ አድርሰዋል። የተለያዩ አጫጭር ተውኔቶችም የኮንሰርቱ አካል ነበሩ። እንደሚታወቀው ኪነ ጥበብ ሀዘንን፣ ቂምን እና ቁርሾን ለመሻር፤ ቅራኔን በፍቅር ለመቀየር ሙሉ ሃይል አላት። ለመዝናኛነት ብቻ ከመዋል አልፋ ለአፍቃሪዎቿ የክፉ ቀን መጠጊያ፣ ጨለማውን መሻገሪያ በመሆን ዋጋዋ ከፍተኛ ነው። ይህን ውለታ አሁንም እየከፈለች ትገኛለች። በአንድነት ፓርክም የሆነው ይህ ነበር።
ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ተውኔት፣ ሙዚቃ ብቻም አይደለም እየተሰራ ያለው፤ በስነ ፅሁፉም ዘርፍ የተለያዩ ስራዎችን እየተመለከትን ነው። ከእነዚህም መካከል “ለእጅ፣ ለአፍና ለእግር የተጻፈ ደብዳቤ” በሚል ርዕስ የተከተበው የስንኝ ቋጠሮ ደግሞ አንዱ ነው። ይህ የስንኝ ቋጠሮ በደራሲ እና ገጣሚ እንዳለጌታ ከበደ የተጻፈ ነበር። እስቲ ለርእሰ ጉዳያችን መውጫ እንዲያግዘን ቀንጨብ አድርገን እናቅምሳችሁ፦
ለእጅ ለአፍ እና ለእግር የተጻፈ ደብዳቤ
ተውኝ ተውኝ ተለመኑኝ
ከህይወት ከሰፌድ ላይ ሞት አታዘግኑኝ
ተው አታነካኩኝ ከዘመን ደዌ ጋር ጥላ አታለካኩኝ
እጄ አይኖቼን ተኳረፍ ለጊዜው ተጣላ
አፍንጫዬን ራቀው ነግሬሃለው ኋላ
ተው አትጨባበጥ ሰላምታህን ለውጥ
በንክኪ ሆኗል ዓለም የሚናወጥ
እንደ እንቧይ የሚፈርጥ…እያለ ይቀጥላል!
መሰናበቻ
የሰው መሞት ቁጥር ሆኗል፤ ሬሳ መዝገን የአለማችን የእለት ተዕለት ተግባሯ ከሆነ ሰነባብቷል። ለወትሮ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጉዳዮቻቸው ፈርጣማ ጡንቻ ያላቸው ሀያላን አገራት አሁን ግን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ክንዳቸው ታጥፏል። አንገታቸውን ተደፍቶ የመፍትሄ ያለ እያሉ ነው። ሃያላኑ ዝለዋል፤ ደክመዋል። ዙሪያ ገባው ጨልሞባቸዋል። የሚይዙት የሚጨብጡትን አጥተዋል፤ ሆስፒታሎች ሞልተዋል…ብቻ ነገሩ ግራ ሆኗል። ግራ አጋብቷል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአፍሪካ በተዳከመ ኢኮኖሚ እና በተቀራረበ የማህበራዊ ኑሮ ይህ በሽታ ተጨምሮ የችግሩን አሳሳቢነት ከፍ ያደርገዋል። ለዚህም ከሞት ጋር ለሚደረገው ግብግብ ያሉንን ሁሉ እድሎች አቅሞች ምክሮች… መጠቀም የግድ ይላል። ወረርሽኙን በተሻሉ ሆስፒታሎች፣ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም በዘመናዊ መሳሪያዎች መቆም እንደማይቻል ሀያላኑን ሲፈትን አይተናል። ጠቢብ ሰው ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል እንዲል መጽሐፉ ይህንን ቸነፈር ማምለጥ የሚቻለው ምክርን በአግባቡ በመስማት እና በተግባርም በማዋል ነው።
የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች እንዳደረጉት ሁሉ ሁሉም ግለሰብ በየተሰማራበት መስክ የጥንቃቄውን ትምህርት እንዲሰጥ ላላወቀው እንዲያሳውቅ ግድ ይላል፤ ወረርሽኙን ለብቻችን የምንከላከለው፣ ለብቻችን የምንድንበት አይደለም። በጋራ በመከላከል በጋራ የሚዳን ቸነፈር ነው፤ ቸልተኝነት ዋጋ ያስከፍላል። መንቃት መትጋት እንዲሁም መጠንቀቅ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ጊዜ ላይ ነን።
ኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች አንድ ነገር አላት። ይህም የደረጀ ባህላዊ የሆነ መረጃ መቀባበያ፣ ድንቅ የመቻቻል፣ የሰላም፣ የመረዳጃ እሴት ነው። እነዚህ ድንቅ እሴቶች የመጣብንንና የሚመጣብንን ሰይጣናዊ የጥፋት ውሃ ለመከላከል ለመግታት የሚረዱ ናቸው፤ በዘመን መካከልም እነዚሁ እሴቶች ሲጠቅሙ ነበር። ስለዚህም የሚመገበው ለሌለው ከአለን ላይ በማካፈል፤ መረጃ ላጠረው ከአወቅነው እያሳወቅን፣ የህክምና ባለሙያዎችን ምክር በመስማት እና በማስተዋል ይህንን ጊዜ ማለፍ ያስፈልጋል። ደግሞም ያልፋል። በዓለም ብሎም በአገሪቱ የመጣው ይህ ቸነፈር ተወግዶ የሰላም አየር የምንተነፍስበት ኢትዮጵያም ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ ቀና የሚሆንበት እና ትንሳኤዋ የሚፋጠንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ሁሉም ጥሩ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ የፍቅር የመቻቻል አገርና ምድርነቷም ይቀጥላል። ሰላም!!
አብርሃም ተወልደ