እንዴት ናችሁ ወገኖቼ? ሰላማችሁ ይብዛ። ፈጣሪ ምህረቱን ይስጠን ዘንድ ሳትታክቱ መመሪያዎችን ተግብሩ። የኮቪድ-19 ቫይረስ በሀገራችን መከሰትን ጉዳይ ያው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እየጣርን ነው። የኛ የዋሁ ህዝብ አቅፎ ካልሳመህ ፍቅሩ የማይወጣለት፤ ካልተጨባበጠ ሰላም ያላለ የሚመስለው ነው። ኧረ እንዲያውም ቶሎ ግንዛቤን መያዝ ይችላሉ በሚባሉት ወጣቶችም የሚታዩ ክፍተቶችን መታዘብ ችያለሁ። አሁንም ተቃቅፎ የመሄድ እጅን በአንዱ/ዷ ትከሻ ላይ የማስቀመጥ ዘመናትን የኖርንበትና ያደግንበት የህይወት ዘዬአችን ስለሆነ በቀላሉ ለመፋታት ቸግሮናል።
ግን ምርጫ የለንም ወገን ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው ‹‹ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤›› ተብሏልና እናስተውል። የመጣው ኮሮና ነው። ኮሮና ደግሞ አደገኛ ቫይረስ ነው፤ ጉንፋን ሆኖ ዝንጅብል አያሽለንም። ገንዘብ ያላቸው በምድራዊ ጥበብ የበለፀጉ ሀገራት እነ ቻይና፣ አሜሪካን፣ ፈረንሳይ፤ ጣሊያን፣ ስፔን… ግራ ገብቷቸው ሀብታቸው ከንቱ ሆኖባቸው እውቀታቸው ከኮሮና አቅም በታች ሆኖባቸው ዜጎቻቸው እንደ ቅጠል እየረገፉባቸው ይገኛሉ። እኛ ኢትዮጵያውያንን ግን ፈጣሪ በነርሱ ትምህርት አግኝተን እኛ እንድንነቃቃ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዕድል ሰጥቶናል። እንጠቀምበት! ኮሮናን ለመከላከል ማድረግ ስላለባችሁ ጥንቃቄ ከቀድሞ በበለጠ መልኩ እንድትቀጥሉ አደራ እያልኩ ተከታዩን የትዝብት ዳሰሳ ላቅርብ።
ኮሮና ምን መልካም አጋጣሚ ይዞ መጣ?
በዓለም ዙሪያ ያለው አየር ይበልጥ እየተሻሻለ ነው፤ አነስተኛ ብክለት ወደ ባሕር እየገባ ነው፤ የጎዳናዎች ጫጫታ አነስተኛ ሆነዋል። ቤተሰቦች አብረው ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ የቅንጦት መርከቦችም ወደ ባሕሩ አያቀኑም፤ ሰዎች ለተጨነቁበት ጉዳይ አካባቢያዊ መፍትሄዎችን በጥልቀት መመልከት ችለዋል። ንጽህናን ቸል ብለው የነበሩት ጊዜ ወስደው እጆቻቸውን በመታጠብ ንፅህናን መለማመድ ጀምረዋል። የአመጋገብ ልምዶች እንኳ እየተቀየሩ ናቸው።
አስጨናቂው የጦር እሰጣ ገባ ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ አዝጋሚ ሆኗል። እኛ ምስኪኖችም ጥሩ አየር እየተነፈስን ነው። ሁሉም ሰው ፈጣሪውን አመስጋኝ ሆኗል። አዎ! ይዋል ይደር እንጂ የዚህን ቫይረስ ስጋት እናሸንፋለን። ነገር ግን፣ ወደቀድሞ የአኗኗር ዘይቤያችን ከመዝለላችን በፊት እኛ ጊዜ ላይ በማተኮር እንደ ጥሩ አጋጣሚ መጠቀም አለብን። ወገኖቼ በዙረታችን ወራት ነፃነታችንን እንዳባከንነው ይሄን ምርጥ የእረፍት ጊዜ ማባከን የለብንም። በርግጥ ነገን ለመኖር ዛሬ አለመኖር ይመስላል። ግን ቤታችን መሆን ለምንችል ይሄንን የመሰለውን ጊዜ ብንፈልግ አናገኘውም ነበር። አሁን ካልተጠቀምንበት ወደፊት አናገኘውም። (ከይቅርታ ጋር ብዙዎቻችሁ ያልተመቻችሁ አታስመስሉ ማለቴም ነው) ዝግ ማለት መጥፎ ነገር አለመሆኑንም ማወቅ ይኖርብናል። አሁን ላይ መረጋጋት፣ መተንፈስ፣ መጸለይ ትክክለኛው ጊዜ ነው። የሕይወታችንን ዝርዝር ትንተና ለማካሄድና ከዚህ ፕላኔት ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚስማሙ ሚዛን ለመፍጠር ጊዜው አሁን መሆኑን አይተናል።
በነገራችን ላይ ኮቪድ 19ን እንደ መርገምት ብንመለከተው እንኳን ከላይ ከጠቀስኳቸው ሀሳቦች በተጨማሪ የመርገምቱ በረከቶችም ብዙ ናቸው። ከኮቪድ 19 ለመዳን እየተደረጉ ያሉ ጥንቃቄዎች እግረመንገዳቸውን በእርግጠኝነት ሌሎችንም ህመሞች እያራቁልን ነው። በእስር ቤት ከነበሩ ወገኖች አንፃር ለታሰሩ መፈታት መማለድ የአማኞች ፀሎት ነበርና ሺህዎች ተፈትተዋል። (ምንም እንኳን ስርቆቱ እየበዛ ቢመጣም) ወሳኙን ነገር ማስተዋል፣ የማይረባውን ርዕስ ችላ ማለት እናም አንፃራዊ አንድነት ማግኘት ችለናል። የሰው ልጆች ሁሉ እኩልነት ተገልጧል፣ በሀብታምና በድሃ፣ በነጭና በጥቁር መካከል እንዳለ የሚታሰበው ርቀት ጠባብ ሆኖ ታይቷል። ከሁሉም ይልቅ የሰው ልጆች አቅማችንን አውቀነዋል። ከፈጣሪ ዘንድ ብቻ አለኝታ እንዳለን አውቀናል። እነዚህ እና ሌሎች ብዙ የመርገምት በረከቶች አስተውያለሁ።
ክፍተቶች
ኮቪድ 19 በዚህ ሰአት እርግጠኛ ውይይት መደረግ ያለበትና አስተያየት መሰጠት ያለበት ጉዳይ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ ያየሁትን ጉድለትና መልካም አጋጣሚዎችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ትዝብቶችን መጠቆምም ሆነ ማስተላለፍ የዜግነት ግዴታ ብቻም ሳይሆን የራስ የመኖር ህልውናም ጭምር ነው።
ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በተደጋጋሚ ከታዘብኩት የቫይረሱ መተላላፊያ መንገዶች ናቸው ተብለው ከሚነገሩት እጅን መታጠብ ብቻ መፍትሄ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ በእጅጉ እየጎለበተ ነው። በዋናነት ያላስተዋልናቸው መጠጋጋት (የተነገረውን እርቀት አለመጠበቅ) እና ተጠጋግቶ መቀመጥ እንዲሁም የጎላ ንክኪ ማድረግ ለማን የተተው ተግባራት ይሆኑ? ይህንን በተመለከተ አንዱ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ሲፈልግ ሌላው ቸልተኛ ይሆናል።
ግንዛቤው በእኩል ደረጃ እስኪፈጠር ድረስም በታክሲና አውቶቡስ ተራ አካላዊ መራራቅን የሚቆጣጠሩ ሰዎች መኖር አለባቸው። በተለይ የታክሲ ተራ ደንብ አስከባሪዎች የተራ ገንዘብ ከማሯሯጥ ይልቅ የሰው ነፍስ ለማዳንም መፍጠን ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ቦታ ላይ የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ ሰዎች አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ሲሰሩ ይታያል። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ፖሊሶቻችን ሰዎች እንዳይቀራረቡ እየሰሩ ቢሆንም፤ ለአደጋው ተጋላጭ እንደመሆናቸው እነርሱም ርቀታቸውን ጠብቀው ቢሰሩ ጥሩ ነው። የእግረኛ መንገዳችንም በቂ ባለመሆኑ አካላዊ መራራቅ ከሰው ብዛት አንጻር ለመጠጋጋት ስለሚዳርግ ከቤት አለመውጣቱ ደግሞ ጥሩ አማራጭ ነው። ቫይረሱ የበለጠ ዋጋ ሳያስከፍለን እርምጃም ሊያስወስድ በሚችል መልኩ፤ ቢቻል ከደንብ አስከባሪዎች እና ከጸጥታ አባሎች ጋር በማቀናጀት ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ በየወረዳውም ሆነ በየመስሪያ ቤቱ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመዘዋወር በግዴታ እንዲተገበር ማስደረግ ይገባል።
በሌላ በኩል በመዲናችን አዲስ አበባ ታክሲዎች የመጫን አቅማቸው በ50 በመቶ ቢቀንስም የሚደረገው ጥንቃቄ ግን አሁንም አናሳ ነው። የታክሲ ረዳቶች ፊት መሸፈኛ ሳያደርጉ ነው የተለመደውን ሥራቸውን የሚያከናውኑት። በየመንገዱ ቡና ጠጡ የሚሰሩት ሰዎች ደግሞ ከሚያስተናግዱት በርካታ ሰው አንጻር ጥንቃቄያቸውም ከፍ ማለት አለበት። ስኒዎቻቸውን በንጽህና መጠበቂያ በማጽዳት እንዲሰሩ ማስገደድ የግድ መስሎ ይታየኛል።
እኔ ተዘዋውሬ እንዳስተዋልኩት ጥንቃቄ ለማድረግ የሚሞክር ሰው ላይ የሚያፌዝ እንጂ ከልቡ የሚተገብር ሰው ውስን ነው። በማህበረሰባዊ ንቅናቄ ታጠቡ፣ተራራቁ እና እርዳታ ስጡ ብቻ ሳይሆን አግባብነት ያላቸው ርምጃዎች ያስፈልጋሉ። ኢትዮጵያውያን ደጋግመን እንደምንለው እንቅስቃሴያችንን ካላስተካከልን ከጣሊያን በላይ የመከራ ጊዚያትን የማንቀበልበት ምክንያት አይኖርም።
ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎችና፣ የቆንስላ ሰራተኞች በተለይ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጊዜ ቤት ውስጥ መቀመጥ ለምን እንደሚያዳግታቸው አይገባኝም። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም አውሮፕላን ላይ ከብዙ ሰዎች ጋር እንደሚነካኩና ተጋላጭ እንደሆኑ እያወቁ ስለምን መስማት እንደተሳናቸው አይገባኝም። በከተማዋ ያለው የአኗኗር ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ በግብይት አካባቢ ያለው መጨናነቅ እንዳለ ነው። በተለይም በቅርቡ ወደ ጃንሜዳ የተዘዋወረው አትክልት ተራ ከበር ጀምሮ እስከ መገበያያው ቦታ ድረስ ፍጹም የሆነ አካላዊ ርቀታቸውን ያልጠበቀ እንቅስቃሴ ይታይበታል። ይህንን ለመቀነስ በጎ ፍቃደኛ አንቂዎችን በመልመል በ‹‹ማይክራፎን›› እንዲያስተምሩ ቢደረግና ከዚህም ባሻገር ችግሩ እንዳይባባስ አፋጣኝ ርምጃ መውሰድ ተገቢ ይሆናል።
ሌላው ትምህርት ባለመኖሩ ምክንያት ተማሪዎች በየመንገድ ዳር አንድ ላይ ተሰባሰበው ይታያሉ፤ ይህ ነገርም መከልከል አለበት። ተማሪዎች ቤት ውስጥ እያነበቡና ሌሎች ተጓዳኝ ክንዋኔዎችን እንዲፈጽሙ እንጂ እንደ እረፍት ጊዜያቸው ወጣ ብለው እየተዝናኑ እንዲቆዩ አይደለም ውሳኔ የተላለፈው።
በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ማለት ይቻላል አሁንም ምንም እንዳልተፈጠረ የተለመደው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሰዎች በርካቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን መከልከል አቅቷቸው ሳይሆን ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠት ነው። ጉዳዩ ላይ ግንዛቤ የሚሰጧቸውን ደብድበው እስከመግደል የደረሱም አሉ። አሁን ወገን በወገን ላይ ሳይሆን ወገን በአንድነት በበሽታው ላይ የሚጨክንበት ጊዜ መሆን ነበረበት።
ወገን ዘላቂ ጤና ከዘላቂ ሰላም ጋር እጅጉን አስፈላጊ ነው። አሁን ላይ የፖለቲካ ትንታኔ ለፖለቲከኞች፣ የኢኮኖሚም ለኢኮኖሚስቶች ተትቷል ተመስገን ነው። እነዛ እናውቃለን ባዮች አክቲቪስቶችም አረፉልን። ይህ የጭንቅ ወቅት አልፎ ዳግም የፖለቲካና የብሄር ዛር ካደረባቸው ግን ያስተዛዝበናል። ካደረጉም ደግሞ መንግስት በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሀገር አፍራሽ አክቲቪስቶችንም ጭምር ከክፋታቸው እስኪያገግሙ ድረስ ማቆያ ውስጥ ቢያስገባልን ዘላቂ ጤና ከዘላቂ ሰላም ጋር እንደምናገኝ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህንን ለማንሳት የተገደድኩት የመኖር ያለመኖር ምርጫውን ወደ ኋላ ብሎ ለፖለቲካ ምርጫ የሚሯሯጥ መኖሩን በማስተዋሌ ነው።
አንዳንዶች የቆየ ልማዳቸው አሁንም አልፎ አልፎ ፖለቲካ ፖለቲካ ያስጓራቸዋል። መቼም አምስት ሳንቲም ሳይረዱ ወይም ለዓለም የመጣን ወረርሽኝ ለተቃወሙት ሰው ብቻ እያላከኩና እየኮነኑ ሁል ጊዜ የመልካም ነገር ተቃራኒ እየሆኑ ከመኖር አንደኛቸውን ወደ ማገገሚያው ገብተው ቢለይላቸው የተሻለ ሳይሆን አይቀርም።
ዛሬም ስለ ብሄርና ሀይማኖት ስለድርጅትና ፖለቲካ የሚያወሩ ሰዎች ይገርሙኛል። ዓለም እንዲህ በጭንቅ በተዋጠችበት ግዜ ይሄ ይወራል? ለማንኛውም የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አቅም ለሌላቸው ወገኖች አለኝታነታችሁን እያሳያችሁ ስለሆነ ምስጋና ይገባችኋል። ቪዲዮ መጥቶ ዜና ካልተሰራላቸው ማካፈል የማይወዱ የከተማችን ባለሀብቶችም እንዳሉ ግን ታዝቤያለሁ። የዛኑ ያህል ደግሞ ደጋግና ታይታን የማይወዱ ብዙ ሰዎች አሉ። በተለያየ ቦታ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በአንድ ሰብስበው የሚረዱ እንቁ ዜጎች አሉ። በዚህ ሰዓት ስለ ሱቅ ኪራያቸው የሚያስቡም አሉ። ጉድ እኮ ነው ግን ሁሉም “ኢትዮጵያዊ” ነው።
አንዳንዶች ደግሞ መድሃኒቱን የቻይና እና የአሜሪካ ተመራማሪዎች ያገኙታል ብለው በአዕምሯቸው እያብሰለሰሉ ኖረው ድንገት የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች አገኙት ሲባሉ የደስታ እና የቅናት ስሜት ድብልቅልቅ ብሎባቸው ሲዘባርቁ መዋላቸውንም በቅርቡ ታዝበናል። በአንዳች ክፉ መንፈስ የተያዘ ሰው የመድሃኒትን ነገር ስትጠራበት ጤነኛ መስሎ ሊያጭበረብርህ ነው የሚሞክረው። በእርግጥ ጫፍ ያልደረሰን ነገር እንዳለቀለት አድርጎ መግለጫ መስጠትም ጥሩ አይደለም። ግን ደግሞ በራሳችን ጥረት የሚደረገውን የህይወት መድህን ርብርብ ማድነቅ ተገቢ ነበር።
የኮሮና ቫይረስ መድሃኒት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው ተብሎ ሲገለጽ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብርድ ብርድ የሚልና ትንታኔ የመሰለ ነገር በመሞነጫጨር ፖለቲካ የሚዘራ ሰው ካያችሁ ያ ሰው ማቆያ ውስጥ መቆየት ይገባዋል ባይ ነኝ። እስከ መቼ ስማችን በክብሪት ቀፎ ላይ ብቻ ‹‹የኢትዮጵያን ምርት ይጠቀሙ!›› ተብሎ ይጻፋል?
ሰላማችሁ ይብዛ! በመጠንቀቅ እናሸንፍ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
አዲሱ ገረመው