አዲስ አበባ (ኢዜአ)፡- መንግሥት ተልዕኳቸውን በአግባቡ የማይወጡ ዲፕሎማቶችን ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት «ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች ትናንት ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ነው።
ኤምባሲዎች አገራዊ ተልዕኮዎች የሚፈጸ ሙባቸው ተቋማት እንጂ የመዝናኛና እረፍት ቦታዎች ባለመሆናቸው ዲፕሎማቶች ተልዕኳቸውን በውጤት ለመደገፍ መስራት አለባቸው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ኤምባሲዎች የሚሰሩ ዲፕሎማቶች በውጤት ስለማይለኩ ፋይዳ በሌለው ሥራ ተጠምደው ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ኤምባሲ የጡረታ ማስከበሪያና የማረፊያ ቦታ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዲፕሎማቶች ከዚህ በኋላ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በውጤት ለመደገፍ ሊታትሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ዲፕሎማቶች ትልቁን አገራዊ ተልዕኮ ከማስፈጸም ይልቅ ለሚደግፉት ቡድንና ሁኔታ የመስራት አዝማሚያ እንደነበራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ይሁንና መንግሥት ከዚህ በኋላ ተልኳቸውን በአግባቡ መፈጸም የማይችሉ ዲፕሎማቶችን አይታገስም ብለዋል።
አምባሳደሮች ወደተለያዩ አገሮች ሲመደቡ ብዙውን ጊዜ ጭቅጭቅ እንደሚፈጠር ጠቁመው፤ ይህም ትልቅ የሚባለውን አገርን ከመሸከም ይልቅ የራስ ምቾትና ተድላን ማሳደድን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። ኃላፊነት የሚፈተነው በምቾት ሳይሆን በችግር ውስጥ በመሆኑ ዲፕሎማቶች ይህን ተገንዝበው የአገር እንደራሴነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል። ዲፕሎማቶች በአሁኑ ጊዜ ብዙሃኑን እያሸነፈ ካለው የእኔነት ስሜት መውጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ «ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጠና የበርካታ ኃያላን መንግሥታትን ቀልብ የሳበ ከመሆኑ አንጻር ከእኔነት ወጥተን ከጎረቤቶቻችን ጋር ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠር አስፈላጊ ነው» ሲሉም ተናግረዋል። ዲፕሎማቶች እራሳቸውን ከዓለም ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የህይወት ዘመን ተማሪዎች መሆን እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
መንግሥት የዲፕሎማሲ ሥራውን አሁን ካለው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውን እንደሚያሻሽልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011