አዲስ አበባ፡- የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ወቅታዊ ችግሮችን ከማርገብ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና የአገር ግንባታ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የሰላም ሚኒስቴር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ። አገር ግንባታ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚካሄድ ሂደት እንደመሆኑ ትውልድ በመጣና በሄደ ጊዜ እንደየትውልዱ ፍላጎትና አገራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ አዳዲስ መንገዶችን መቀየስ እንደተጠበቀ ሆኖ መሰረታዊ ማህበራዊ እሴቶችን ማሻገር በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይበጠስ አገናኝ ድልድዩም እንዳይሰበር የማድረግ ኃላፊነት የአገር ሽማግሌዎች መሆኑን ጠቁመዋል።
ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደበት ወቅት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፣ አገር በድንቁርና ውስጥ ስትሆን፣ የዘላቂነቷ አምዶች መሸርሸር ሲጀምሩ፣ በትውልድ መካከል የተዛነፈ አረዳድና ግንኙነት ሲኖር፣ የጋራ አመለካከትና ቅብብሎሽ ሲደናቀፍ ማህበራዊ እሴቶች አገርን የመታደግና የማዳን አቅማቸው ትልቅ ነው ብለዋል።
ስለሆነ አገርን መልሶ ለመገንባት የአገር ሽማግሌዎች እጅግ ቅርብ በመሆናቸው ሚናቸውን ጊዜያዊና ወቅታዊ ችግሮችን ከማቃለልና ከመፍታት አሻግረው ዘላቂ ሰላምንና የአገር ግንባታን እውን በማድረግና በየአካባቢያቸው ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ ሰፊ ንቅናቄ በማካሄድ ከወትሮው የላቀ እንቅስቃሴ ማድረግ በሚጠይቃቸው ጊዜ ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በማህበረሰብ ደረጃ ጊዜያዊ የሰላም መደፍረስን በማርገብም ሆነ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማምጣት ሚናችሁ ተኪ የለሽ ነው፤ ያሉት ሚኒስትሯ ሰላምን በመንከባከብና በማሳደግ ረገድ ማህበረሰባዊ መሰረት የመገንባት ዕድልና ችሎታ በእናንተ እጅ ነው፤ ትውልዱ ማንነቱንና ስብዕናውን በሚፈታተኑት ተጽዕኖዎች ውስጥ በመሆኑ እነዚህን ተቋቁሞ ማለፍ እንዲችል ጠቃሚ እሴቶችን በማውረስ ዘመናዊነትን በጥበብና በብልሀት እንዲያስተናግድና እንዲሻገር ብሎም አገርን እንዲያሻግር በማድረግ የነገ ታሪካችሁን የዛሬ ደግሞ ኃላፊነታችሁን መወጣት አለባችሁ ሲሉም ተናግረዋል።
ለወጣቱ ትውልድ አገራዊ እሴቶችን በማውረስ ዘመናዊነትን በጥበብ እና በብልሃት እንዲላበስ፣ የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል አሳስበዋል።
«የአገር ሽማግሌዎች ለአገር ሰላም» በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መድረክ ላይም ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እንዲሁም ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና አደሲንቄዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
በእፀገነት አክሊሉ