@ አቶ ኢሳያስ ዳኘው በዋስትና እንዲለቀቁ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፡- ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ 12 የቀድሞ ሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ሁለት ግለሰቦች ከመርከቦች ግዢ፣ጥገናና አስተዳደር ጋር ተያይዞ ትናንት በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት 544 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር በመንግሥትና ህዝብ ላይ ያላግባብ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ፡፡
ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች እንደቅደም ተከተላቸው፤ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮሎኔል በርሄ ወልደሚካኤል፣ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፣ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁሩንዲ፣ ኮሎኔል ተከስተ ኃይለማርያም፣አቶ ሰለሞን ኃይለሚካኤል፣ኮሎኔል መሀመድብርሃን ኢብራሂም፣ ሻለቃ ሰለሞን አብርሃ፣ኮሎኔል አለሙ ሽመልስ፣ ኮሎኔል አዜብ ታደሰ፣ሻምበል ይኩኖ አምላክ ተስፋዬ፣ ሻምበል ሰመረ ሃይሌ፣ሚስተር ሞህድ ራፍኤችና አቶ ኡስማን አብዱ ናቸው፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ህግ በግለሰቦቹ ላይ የመሰረተው ሦስት የተለያዩ ክሶችን ነው፡፡ ክስ የተመሰረተው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ተከሳሾች ላይ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በመንግሥትና በህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን በማለፍ በተፈጸመ ድርጊት ተከሰዋል፡፡ተጠርጣሪዎቹ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ለመርከቦች ጥገናና አስተዳደር 544 ሚሊዮን 702ሺ 623 ብር የሚገመት ለፕሮጀክት የተመደበ ውስን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት ለራሳቸውና ለሌሎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም በማግኘትና በማስገኘት መጠርጠራቸውም ተጠቁሟል፡፡
ሁለተኛው ክስ በ1ኛ፣ በ2ኛና ከ6 እስከ 14 ባሉ ተከሳሾች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ተከሳሾቹ ለፕሮጀክት የተመደበ የአገሪቱን ውስን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት በሥራው ግንኙነት ምክንያት ለራሳቸውና ለተዋዋይ ወገኖች ያላግባብ ጥቅም የሚያገኙበትና ሊከላከሉት የሚገባቸውን የመንግሥትና የህዝብ ጥቅም ያላግባብ ጉዳት እንዳደረሱም ተመልክቷል፡፡
ዓቃቤ ህግ በሦስተኛነት የመሰረተው ክስ በሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ ነው፡፡ ክሱ እንደሚያመለክተው፤ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው መርከቦቹ ወጪ ብቻ እያስወጡ ከቆዩ በኋላ ያለጨረታ አጭር ዝርዝር ወጥቶ እንዲሸጡ በማዘዝ ሲሆን፤ ከተገዙበት ዋጋ 607 ሺ ብር 432 ዶላር ከስረው እንዲሸጡ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡መንግሥት ከውድድር ሊያገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳሳጡም ተጠቅሷል፡፡ ዓቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሶ 24 የሰውና 70 የሰነድ ምስክሮችን አቅርቧል፡፡
በሌላ ዜናም፤በሶማሌ ክልልና በባሌ ዞን የሞባይል ኔት ወርክ ማማ ተከላ ያለጨረታ ከወንድማቸው ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጋር ተመሳጥረው ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሰጥተዋል፣ ውልም አሻሽለዋል በሚል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፖሊስ እየተጣራ የሚገኘው አቶ ኢሳያስ ዳኘው 100 ሺ ብር እንዲያስይዙና የጉዞ እግድ ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት ጉዳይ ቢሮ እንዲጻፍ በማዘዝ ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ልደታ ምድብ አዟል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
ዘላለም ግዛው