በጎርጎረሳውያኑ 2019 መጠናቀቅያ ቻይና ውስጥ የተቀሰቀሰው ኮቪድ 19 አሊያም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት ዓለምን አዳርሷል። በቻይና የቫይረሱን ስርጭትን ለመግታት ጠንካራ የዝውውር እገዳ ከተጣለ እና ኢኮኖሚያዊ ገቢን የሚያስገኙ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ሁሉ በሙሉ ከተዘጉ በኋላ ዛሬ በኮሮና ቫይረስ የሚሞተውም ሆነ የሚያዘው ሰው ቁጥር መቀነሱ እየተነገረ ነው።
ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቻይና የውሃን ከተማ አስተዳደር በስድስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ሆስፒታል ሰርቶ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ሆስፒታሉ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁና የተጠረጠሩ ሰዎች ማቆያነት ታስቦ የተሰራ ነበር:: በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ ዜጎቿን ያጣችው ቻይና ባደረገችው ጥረት በአሁኑ ወቅት በሽታውን መቆጣጠር ችላለች። ለዚህ ደግሞ በቀናት ውስጥ ገንብታ ወደ ስራ ያስገባቻቸው ሆስፒታሎች የራሳቸው አስተዋፅኦ ነበራቸው::
የቻይና መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ከሆነ፤ አዲስ የተገነባው ሆስፒታል አንድ ሺህ አልጋዎች ያሉት ነው:: መገናኛ ብዙሀኑ በድረ ገፅ ላይ የለጠፉት ምስል እንደሚያመለክተውም፤ ሆስፒታሉ 25 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈ ነው:: በስድስት ቀናት ውስጥ የግንባታው ሁኔታ ተፋጥኖ መገባደድ መቻሉ ብዙዎችን ያስደነቀ ሲሆን፣ እኤአ 2003 በሳርስ ቫይረስ ምክንያት በቤጂንግ ከተማ ከተገነባው ሆስፒታል ጋር ተመሳሳይነት አለው::
በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የግሎባል ጤናና ማህበራዊ ጤና መምህር የሆኑት ጆን ካሁፉማን እንደተናሩት፤ በቻይና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለብቻቸው በማድረግ ህክምና መስጠት ውጤታማ የበሽታ መከላከያ መንገድ ነው:: ለዚህም ደግሞ በፈጣን ሁኔታ የተገነባው ሆስፒታል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል::
በውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ምክር ቤት የዓለም አቀፍ ጤና ባልደረባ የሆኑት ያንዞንግ ሁሀንግ፣ ‹‹ቻይና እንደዚህ ላሉት ታላላቅ ፕሮጀክቶች እንኳን በፍጥነት ነገሮችን የማከናወን ሪኮርድ አላት።›› ብለዋል። እኤአ በ2003 ቤጂንግ ውስጥ በሳርስ በሽታ ምክንያት በሰባት ቀናት ውስጥ ሆስፒታል ተገንብቷል። በመሆኑ የግንባታ ቡድኑ ምናልባት ያንን ሪኮርድን ለማሸነፍ እየሞከረ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ልክ እንደ ቤጂንግ ሆስፒታል የውሃን ማእከል ቀደም ሲል ከተገነቡ ሕንፃዎች በፍጥነት ቀዳሚ ነው።
የሆሼን ሆስፒታል ግንባታ የተጀመረው እኤአ 2020 ጥር 23 ቀን ሲሆን፣ እኤአ 2020 የካቲት 3 ቀን ግንባታው ተጠናቋል:: በግንታው ወቅት ብዛት ያላቸው ኤክስካቫተር፣ ቡልዶዘር እና ሌሎች ለቁፋሮ የሚሆኑ ማሽኖች ጥቅም ላይ ውለዋል:: በማሽኖቹም በመታገዝ ሆስፒታሉ የሚያርፍበት ቦታ ወጥ ከማድረግ አንስቶ ኮንክሪት በፍጥነት እንዲሞላ አድርገዋል:: በፍጥነት ለመገንባት ታቅዶ የነበረው ሆስፒታል ስራ ሲጀመር አነስተኛ ሰራተኞች በመገኘታቸው ምክንያት በሁለት ፈረቃ ስራው ይከናወን ነበር። በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ሰራተኞች በመጨመራቸው በሶስት ፈረቃ ሰባት ሺህ ሰራተኞች ግንባታውን አከናውነዋል።
ግንባታውን በጊዜው ለማጠናቀቅ መሐንዲሶች ከመላ አገሪቱ እንደሚመጡ ተደርጓል። በምህንድስና ስራው ቻይና ብዙ ርቀት የተጓዘች ሲሆን፣ በከፍተኛ ፍጥነት ህንፃዎችን የመገንባት ታሪኮችም አሏት። ግሎባል ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ፤ ለሆስፒታሉ አገልግሎት በጦር ሀይል ውስጥ የሚሰሩ 150 የጤና ባለሙያዎች እንዲመጡ ተደርጓል። ሆስፒታሉ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ከጦር ሃይል ኮሚሽን 950 ያህል የቁሳቁስ ድጋፍ እና ከህክምና ዩኒቨርሲቲዎች 450 ተማሪዎች ለስራው ወደ ሆስፒታሉ ተልከዋል። በተጨማሪም የህክምና ርህቦቶች ከታካሚ ናሙናዎችን ለመውሰድ ጥቅም ላይ ውለዋል። እንደ ሪፖርቱ ከሆነ፤ 63 ሰራተኞች ከዢንግን ሀናን ግንባታውን ለማገዝ የመጡ ሲሆን፣ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ መጡበት ሲመለሱ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል። ማቆያ ውስጥ ከነበሩት 63 ሰራተኞች ውስጥ ሁለቱ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሆነው ተገኝተዋል።
የሆስፒታሉ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ በሚረዱ ቀላል መሳሪያዎች የተከናወነ ነው። የግንባታ መሰረቶች ጠንካራ በመሆናቸው ሆስፒታሉ ንቅናቄ እንዳይፈጥር አድርጎታል። እያንዳንዱ መሰረት ሁለት አልጋዎች እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራ ነው። እያንዳንዱ ክፍልም ጥቃቅን ተዋስያን እንዳይወጡ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ተገጥሞላቸዋል። በተጨማሪም ለክፍሎቹ የንፋስ መግቢያ (ቬንትሌተር) እና ሁለት ጎን ያለው ቁም ሳጥን ተገጥሞለታል። ቁም ሳጥኑ ክፍሎችን ለመከፋፈል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ የሆስፒታሉ ሰራተኞች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለማድረስ ሁሉም ክፍል እንዳይገቡ አድርጓቸዋል። በሆስፒታል ውስጥ የቪድዮ ሲስተም የተገጠመ ሲሆን፣ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ቤጂንግ የሚገኘው አጠቃላይ ሆስፒታል ይከታተል ነበር።
የሳርስ በሽታ በተከሰተበት ወቅት ደግሞ የሳርስ ምልክቶች የሚታዩባቸውን ሕመምተኞች ቁጥር ለማስተናገድ በ2003 ውስጥ የዣያቶናንሻን ሆስፒታል ቤጂንግ ውስጥ ተገንብቷል። ይህ ፈጣን የሆስፒታሉ ግንባታ የዓለም ሪኮርድን የሰበረ ሲሆን፣ በሰባት ቀናት ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ነበር። ሆስፒታሉን በሰባት ቀን ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ አራት ሺህ ሰዎች ቀንና ሌሊት ሰርተዋል።
በውስጡ የኤክስሬይ ክፍል፣ ሲቲ ክፍል ፣ ከፍተኛ-እንክብካቤ ክፍል እና ላቦራቶሪ ነበረው። እያንዳንዱ ክፍል የራሱ የሆነ የመታጠቢያ ቤት አለው። በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት የሣርስ ህመምተኞች አንድ-ሰባተኛ አምኖ ተቀብሎ ለመታከም ወደ ሆስፒታሉ የገቡ ሲሆን፣ ይህም በህክምና ታሪክ ተዓምር ተደርጎ ተቆጥሯል:: በሳርስ ወረርሽኝ ወቅት ድርጅቱ እና ወጭዎቹ በአካባቢዎች የሚሸፈኑ ቢሆኑም፤ ከሰራተኞች የደመወዝ ወጭዎች እስከ ህንፃው ድረስ በሲስተሙ ውስጥ የሚወርዱት ብዙ ድጎማዎች ነበሩ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
መርድ ክፍሉ