በዓለም ዙሪያ ያሉ ሳይንቲስቶች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት የሚያስችል መላ ለማግኘት ሌት ተቀን ደከመኝ ስለቸኝ ሳይሉ እየተጉ ይገኛሉ። ቫይረሱ ማንንም ሳይመርጥ የሰው ልጆች ህይወት በፍጥነት የሚቀጥፍ በመሆኑ አፋጣኝ ሳይንሳዊ መፍትሔ ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት ውጤት ማፍራቱ እንደማይቀር እሙን ነው።
የሀገራችን ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ጋር በማጣር መፍትሔ ፍለጋ ደፋ ቀና በማለት ከቫይረሱ ጋር ግብግብ ገጥመዋል። የቫይረሱ በፍጥነት መዛመት እረፍት የማይሰጥ በመሆኑ ርብርቡ ቀጥሏል።
የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ቫይረሱ ቻይና ውሃን ግዛት ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችና ግኝቶችን ለሀገራቸው በማበርከት እየተጉ ያሉ በርካቶች ናቸው። የቫይረሱን አደገኛ መሆኑን በመገንዘብ በሚችለው የፈጠራ ሙያ ለወገኖቹ ቅድሚያ በመሰጠት ትልቅ አስተዋፅኦ ካበረከቱት መካከል ወጣት ታምሩ ካሳ አንዱ ነው።
የፈጠራ ባለሙያ የሆነው ወጣት ታምሩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ አፍጣኝ መፍትሔ ፍለጋ በመትጋት የዘመናዊ እጅ መታጠቢያ ቧንቧ በመሥራት በርካቶችን ማዳን ቀዳሚ ተግባሩ አድርጓል።
ዛሬ በሳይንስ አምዳችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ዋንኛ የሆነው የሐኪም ምክረ እጅ በደንብ የመታጠብ ሂደትን ለወገኖቹ ለማቅለል በማሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ ማሽን በመስራት ያደረገው ጥረት በመቃኘት ስለ ወጣቱ የፈጠራ ሥራ ዳሰሳ በማድረግ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ታምሩ የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት የፈጠራ ስራዎችን መሥራት ውስጣዊ ፍላጎቱ መሆኑን ይናገራል። በሀገራችን የበሽታው ፍጥነትና የሰው ግንዛቤ ተመጣጣኝ አለመሆኑና፤ አብዛኛው የከተማችንን ነዋሪ ውጭ የሚውል በመሆኑን በመገንዘብ መፍትሔ በመፈለግ ሥራውን እንደጀመረና ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ወር ጊዜ እንደፈጀበት ይጠቁማል።
የፈጠራ ሥራዎቹ
የፈጠራ ሥራው፤ ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ ማሽን ሲሆን ንክኪ ሳይፈጠር የእጅ እንቅስቃሴን በማድረግ በራሱ የሚከፍትና የሚዘጋ ነው። ሳሙናና እስፖንጅ ላዩ ላይ ያለው፤ አንድ ሺህ ሊትር ታንከር ውሃ የሚይዝ ነው። በእያንዳንዳቸው ቧንቧዎች መካከል የ50 ሳ.ሜ ርቀት የተበጀላቸው ነው። አሁን ላይ ለናሙና የተቀመጠው ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ ማሽን አስር ቧንቧዎች ሲኖሩት በአንደኛው ጎን አምስት፤ በሌላኛው አምስት ጎን ቧንቧዎች አሉት። ማሽኑ ተነቃቃይና ተገጣጣሚ ሆኖ የፈሳሽ ማስወገጃ ጉድጓድ በቦታው የተቆፈረለት ነው።
ከዚህም ሌላ ታምሩ የፈጠራ ስራዎች በርካታ ሲሆን ከእነዚህም የአስፓልት መጠረጊያ፤ ዘመናዊ አስተያየት መስጫ፣ በኤሌክትሮኒክስ የተገጠመለት የአትክልት ማጠጫ ተጠቃሽ ናቸው።
የፈጠራ ሥራው ጠቀሜታ
በአስሩ ቧንቧዎች በእያንዳንዱ 60 ሰው ንኪኪ ሳይፈጠር በበቂ ሳሙናና በውሃ አቅርቦት በአንድ ደቂቃ ውስጥ ያስተናግዳል። ከዚያም በመዝጋት ለቀጣዩ ሰው እድል በመስጠት ቦታ እንዲለቅ ያደርጋል። አንድ ሰው ግማሽ ሊትር ውሃ ሊጨርስ ይችላል።
የማሽኑ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሁለት ሺህ ሰው ማስታጠብ ያስችላል። በአጭር ጊዜ በርካታ ሰዎች ማስተናገድ የሚችል፤ አንድ የሚቆጣጠረው ሰው ብቻ የሚያስፈልገው ነው። ብዛት ያለው የሰው ቁጥርና ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያላቸው ቦታዎች ላይ ጥቅሙ ከፍ ያለ ሲሆን እንደ መርካቶ፤ መገናኛ ያሉ ቦታዎች በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓት በተለይ አስፈላጊ መሆኑንን ይገልፃል።
የፈጠራ ሥራው አሁን ያለበት ደረጃ
ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ ማሽኑ ናሙና በሚኒልክ አደባባይ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ በመሆኑ የታለመለትን ዓላማ ግብ መምታት ችሏል። አሁን ላይ ሰዎች የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው ሰባት የእጅ አስተጣጠብ ቅድመ ተከተል መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ አንድ ሰው በአንድ ደቂቃ ሰባቱንም በመተግበር እየታጠበ ይገኛል።
ቫይረሱ ያልፋ! ለወደፊቱ እጅ መታጠብ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈልግ ወጣት ታምሩ፤ ከሰው የእጅ እጣቢ ወጥቶ የሚፈሰው ውሃ ሲታይ እጅግ እንዳስገረመውና ከእጅ ይሄ ሁሉ ቆሻሻ ይወጣል ብሎ ማሰብ የሚከብድ መሆኑ ይናገራል።
ይህ የፈጠራ ባለሙያም ሃሳቡ ሰፊ ነውና የእጅ መታጠቢያ ጣቢያዎች በመክፈት ስራውን በማሻሻል እጅ ማስታጠብ አገልግሎቱ 24 ሰዓት እንዲሰጥ በማድረግ፤ ሰዎች ሲጠጉት ‹እባኮዎትን እጆትን በመመሪያው መሠረት ይታጠቡ› የሚል ተጨማሪም መልዕክቶችን ማስተላለፍ የሚችል እንዲሆን እንደሚሰራ ይናገራል። ከዚህ በላይ ጎዳና ላይ ውለው ለሚያድሩ ልጆች የእጅ መታጠብና የውሃ መጠጣት የ24 ሰዓት አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውም ይገልፃል።
ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት ዕቅዶች
ታምሩ ለፈጠራ ስራው የተጠቀመባቸው ቁሳቁሶች የሙያው ክፍያ ሳይጨምር ከሰባ ሺህ ብር በላይ ፈጅቶበታል። ለዚህም የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ ያደረጉለት ቤተሰቦቹ መሆኑን ይጠቁማል።
የወጣት ታምሩ ህልም ኮሮና ቫይረስ በመከላከል የሚረዱ የተሻሉ ስራዎች በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች በማስፋፋት ለወገኖቹ አጋዥ በመሆን ለወደፊት ስራውን በማስቀጠል የሚያበረታታና ድጋፍ የሚያደርግለት አካላት ትብብር እንዲደረግለት ጥሪ አቅርቧል ።
ወጣቱ የነበረው ልምድ ተጠቅሞ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን በማስተባበር ያደረገው አስተዋፅኦ ጉልህ ነውና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ ቢደረግ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ጠቀሜታው የጎላ ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/ 2012
ወርቅነሽ ደምሰው