የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ፣ የነበረኝን እድሜና የነበርኩበትን ቦታ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ያውቁታል። ትምህርት አምልኮ እና ንባብ ገንዘቤ ነበሩ። መልካም ነው፤ ምክንያቱም ዛሬን እንድቆም ያኔም እንድፈራ አድርገውኝ ነበረና ። ፍርሃት ለምን ይጠቅማል፣መድፈር እንጂ የሚሉኝ ደርዘን ያል ወዳጆች ነበሩኝ ። አዎ መድፈር መልካም ነው፤ መልካምነትን ደፍሮ መናገር ፣ “አነሰ ኮሰሰ” ሳይሉ፣ ያለንን ለሰው ለመስጠት መድፈር መልካም ነው፤ ይህ ነገር ጥሩ አይደለም፤ አላደርገውም ብሎ ለታላቅ ወንድምም ሆነ ለትልቅ ባለስልጣን የመናገር ድፍረት መልካም ነው።
ለዚህ አንድ ስብሰባ ላይ አንድ ጡረታ የወጣ የሥራ መሪ፣ ለአዲስ የሥራ መሪ ልምዱን ሲያካፍል ፣የተናገረውን ነገር ላካፍላችሁ። ሰውየው “የይርጋለምን ሐምሊን ሆስፒታል”፣ ለመስራት እድሉን አገኘሁና ለማሰራት ከዶክተር ሐምሊን ጋርና ከሌሎች ወዳጅ ሐገሮች ሚሽን ጋር ተነጋገርኩ ። አሁን የተሰራበት ቦታ ለሆስፒታሉ አያመችም ፤ ስለዚህ ሌላ ቦታ ይሰጠኝ ስል ለማዘጋጃ ቤት የመሬት አስተዳደር አመለከትኩ። ሥራውን የምሰራው ከቤትና ቤተሰባቸው በፊስቱላ ህመም ሳቢያ (ከ10 እስከ 30 ለሚደርሱ ዓመታት አላግባብ ለተገለሉና በልዩ ልዩ ምክንያት የማህጸን ደጃፋቸውና የዓይነ ምድር ማውጫው የሚተረተርባቸው እናቶች ናቸው) እና በዚያ ሳቢያ ለተጎዱት ሴቶች የመስራት እቅዴን አስተዛዝኜ ስናገር ሆስፒታሉ የሚያስፈልገው እዚህ ሳይሆን በክልሉ ሌላ ዞን ላይ ነው፤ ብሎ ፕሮጀክቱን እንዳነሳው ወይም እንድለውጥ፣ ከለከለኝ ይላል።
ከዚያም አለ፤ የፕሮጀክቱ ጥናት የሚያመለክተው እኔ ባለሁበት አካባቢ፣ ችግሩ በስፋት ያለው እዚህ አካባቢ፣ ገንዘቡ የተለቀቀውና ግብረ መልስ የሚሰጠው ለዚሁ አካባቢ ሥራ ሆኖ ምክንያቱን ባላውቅም ችግር በሌለበት ሥፍራ መፍትሔ ፈላጊ አለቃ፣ ሆነብኝና እርሱም አሳዘነኝ፤ ፕሮጀክቱ የእርሱ ጓደኞች ወዳሉበት ዞን እንዲሄድ ሳያስብ አልቀረም ። ይሁንናም የመጀመሪያውንም የጉቦ ጠያቂ “አይሆንም” አላልኩትም፤ እስቲ ላስብበት አልኩትና ወጣሁ። ምክንያቱም ፕሮጀክት ሲሰራ እንደምታውቁት ለጉቦ የሚከፈል በጀት አይያዝም፤ መጣሁ ብዬ በአየር ላይ አንጠልጥዬው ሄድኩ፤ ሥራዬን እንዳይስተጓጉል። ለበላይ አለቃዬም ዝም አልኩና አይመችም ባልኳችሁ ተዳፋት ስፍራ ላይ አፈር አስሞልቼና አስጠቅጥቄ የግንባታ ፕሮጀክቴን በሚገባ ካከናወንኩ በኋላ ፤ በኣመቱ “መጥተው ይመርቁልኝ “ ብዬ ፤ በደብዳቤ ጋበዝኩ፤ በአካልም አሳሰብኩ። ከመጣ በኋላ ማሻሻያ ያልከኝ ሥራ የቱ ነው ሲለኝ፤ የሐምሊንን የፊስቱላ ሴንተር አሳየሁት፤ ምንም ማድረግ ስላልቻለ ዶክተር ሐምሊንም አሉና ፣ መርቆ ጥሩ ንግግር አድርጎ ወጥቶ ሄደ። አላሰራ ቢሉህም፣ መልካም ለማድረግ ማንንም ሳትለማመጥና ሳትፈራ ሥራህን አከናውን ። ካልጠብከው ስፍራ እንኳን አላሰራም የሚል ሥራ አጋች እና ጎታች እንቅፋት ሲገጥምህ ለበጎነት ትጋ ፤ ሲል መከረው።
በተረፈ መልካም ለማድረግ እንደመድፈር ያለ በጎነት መቼም ወርቅ ነው። በዚያው ልክ ጓደኞች፣ አብሯደጎች፣ የክፍል ልጆች፣ እንድንደፍር የሚገፋፉን ልክ ያልሆኑ ነገሮችን አለመድፈር ትልቅነት ነው። ዛሬም እንኳን ሳስባቸው እንኳን ያልደፈርኩኝ የምልባቸው፣ ነገሮች ደስ ያሰኙኛል።
ከእለታት በአንዱ ቀን ዘጠነኛ ክፍል እያለን ፣ ከክፍላችን ቆንጆ የነበረችውን ኤልሳቤጥ አየለን፣ (ስሟ ለደህንነቷ ሲባል ተለውጧል) አንድ ሃብታም የሆነ ለእኛ በእረፍት ሰዓት ሻይም ፤ብስኩትም የሚገዛው ወንድማችን ይወዳታል ። ልጅቱ በዚህ እድሜዋ የምትወደድ ናት ። ምክንያቱን ባላውቅም እኔን አግባባኝ ይለኛል፤ ለወትሮው ብዙም የማይገደኝ ሰው ብሆንም ፣ ለምንድነው የማግባባህ አልኩት። እወዳታለሁና እንድትተዋወቀኝ ፈልጌ ነው፤ አለ። ሰይጣን ሹክ ያላት ይመስል ፤ ጠራችን። ና፣ እንሂድ ስለው አልሄድም አለኝ። በዚህ ጊዜ እኔው አፍ እንድሆነው መፈለጉ ገባኝና አልነግራትም ብዬው ስሄድ ተከተለኝና መጣ። እንደደረስንም ልተዋወቃት ፈልጋለሁ ይላል፤ ስላት “ ባለጌ ነው” ብላኝ ና እንሂድ ብላ አቀፈችኝ ። እኔን አቅፋ ልጁን ስትሰድብ ፣ ደነገጥኩና ቢደበድብሽ የለሁበትም አልኳት። “ ልብ የለውም አይነካኝም፤” አለችኝ። “ጉድ ፈላ፤ ለም?” ስላት ከልቡ ስለሚወደኝ ቦቅቧቃ ነው፤ አየህ፣ አንተ ምንም ስለሌለብህ በነጻነት ትቦርቃለህ፤ እሱ ግን እስረኛዬ ነው።” አለችኝ ።
ሳቅ እፍን አደረገኝ ። ራቅ ብሎ ቆሞ ያየናል እኮ አይተሽዋል ስላት ? ክፍል ውስጥ እኮ ዓይኑ ተጎልጉሎ የሚወጣ ነው የሚመስለው፤ አለችኝና ፤ ዝም በለው አከለችበት። ሁሉም ነገር ለእኔ እንግዳ ነበረ።
የሚወድድ ሰው በአንድ በኩል፤።
የተወደደ አለ፤ ሌላ አካል።
ወዳጅ ላይ ፍርሃት ሰፍሯል።
ተወዳጅ በኩራት ታፍኗል።
ኧረ ለመሆኑ ፣ የተወደደችውም ምን አቀበጣት ፤ ወዳጅስ ምን አንጰረጰረው። ድፍረት የት ጋ፣ መግባት ነበረበት? ፍርሃትስ በእውኑ አድራሻው የት መሆን ነበረበት? ልጁ የፈራው ፍርሃት እኔ እንድደፍርለት ፈልጓል። እርሷ የደፈረችውን ድፍረት እኔን አስታክካ ገልጻለች። እናም ይህ ሆኖ አይቻለሁ፤ ይሁንናም፣ እንዲህ ዓይነቱን ድፍረትም ፍርሃትም ለማንም አልመኝም፤ አልጋብዝምም ።
ቀጥሎ ያሉት የፍርሃት ምሳሌዎቼ ግን እናንተንም ይጠቅማሉ ብዬ ስላሰብኩ፣ ስላሰብኩ ብቻ አይደለም ስላመንኩ ላካፍላችሁ ወድጃለሁ።
ልጆች ሆናችሁ መቼም ልብን ከፍ የሚያደርጉ፣ እና የሚያንጠለጥሉ ትናንሽ ፍላጎቶችና ሃሳቦች አእምሮን ይወጥራሉ፤ ያኔም የምትጠሉትን ነገር ለማድረግ ትወስናላችሁ።
ቤት ውስጥ ከገበያ መልስ የሚቀመጡ መልሶች በእናቶቻችን እንደዘበት ኮሞዲኖ ላይ ወይም በበርጩማ ወይም ሶፋ ላይ ይጣላሉ፤ ይተዋሉ፤ እናንተ ደግሞ የሰፈር የእግር ኳስ ቡድን መዋጮ አለባችሁ። ስለዚህ ድንገት ቤት ዘው ስትሉ እናንተ እና ፍራንኮቹ ፊት ለፊት ትፋጠጣላችሁ፤ ያኔም እናታችሁ ጀርባውን ሰጥታ በክፍሉ አንድ ጥግ ላይ ምስር ትለቅማች ወይም ልብሶች እያስተካከለች ነው። ፈራ ተባ እያላችሁ ወደ ሳንቲሙ ጉዞ ስትጀምሩ፣ ፊቷን ሳታዞር እሱን ሳንቲም እንዳትነካ ስትባሉ እናቶቻችሁ ባለአራት ዓይን ይሆኑባችኋል። ሳይዞሩ የሚያዩ ፤ ገምተው የሚናገሩ ከጀርባ ዓይን የተገጠመላቸው ጉዶች ይሆኑባችኋል። ወሬ የለም ፤ ግን ውስጣችሁ እየጮኸ ክፍሉን ለቃችሁ የምትወጡት የኋላችሁን አስባችሁና ፈርታችሁ ነው። እናቶች ደግሞ የማያጠያይቅ ስልጣን በእናንተ ላይ እንዳላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። በኋላ የመጣውን የህጻናት መብት ጥበቃና ቅብጥርሴ እርሱትና የማይገሰስ ወላጃዊ መብት እንዳላቸው ያላሰባችሁ እውነተኛ ልጆች አትገኙም።
ሌላ ምሳሌ ላምጣላችሁ ሥራ ከጀመራችሁ በኋላ፤ ኦዲተሮች እንደሆናችሁ አስቡና ፣ በኦዲቲንግ ቀመር ሳቢያ ያገኛችሁት የገቢና ወጭ መዛባት ተከሰተ እንበል። ጉዳዩ ተገቢው ደረሰኝ ባለማሟላት የመጣ መሆኑን ገምታችሁ ገንዘብ ቤቱን እስከ 24 ሰኣት አሟላ ብላችሁ እድል ስትሰጡት ፣ በዚያ ፋንታ “የድርሻህን ውሰድና ውጣ” ብሎ ሲፈትናችሁ፤ ስጦታ የሚያስከትለውን መዘዝ ገምታችሁ ሪፖርታችሁን ከነጉድለቱ በማቅረብ ስትወጡ የሚሰማችሁ ነጻነትና ፣ “የድርሻችሁን ወስዳችሁ” የተዛባ ሪፖርት በማቅረብ ራሳችሁን በጥቅም ባርነት ውስጥ ከትታችሁ ብትሸማቀቁ ያለውን ልዩነት ታውቁታላችሁ። አንደኛው ነገን በመፍራት የሚመጣ ፣ የዛሬ ነጻነት ሲሆን ሌላኛው ለነገ ደንታ ቢስ በመሆን የመታወር እርምጃ ነው። የትኛውን መረጣችሁ? የክብር ነጻነቱን ወይስ የክብር ባርነቱን? ተጠልታችሁ መከበር ወይስ ተወድዳችሁ መደፈር? የቱን ትመርጣላችሁ?
የሚገርመው ሂሳቡን ያሰራችሁ ሰው እኮ፤ ዝም የሚላችሁ እንዳይመስላችሁ። ወዲያውኑ ዞር ብሎ “እሱ እኮ ሆዳም ነው”፣ “ጅብ ነው “፣ የሚላችሁ እንጂ ሰብዓዊነት የሚሰማው ባለሙያ ነው ፤ አይላችሁም።
ስለዚህ በዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ላይ የምትወስዱት ፍርሃት የተሞላበት የጥንቃቄ እርምጃ ራሳችሁንና ቤተሰ ባችሁን የሚውቃችሁንም ሰው የሚያስከብር ይሆናል። ደፍራችሁ የምታደርጉት ወል ጋዳ ውሳኔ ደግሞ እናንተን ባያሳፍር የሚያውቃችሁን ሰው ያሳፍራል።”ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር” እንዲሉ ነው፤ ነገሩ።
ሞኞች ፣ ደፋሮች ናቸው። ደፋሮች ደግሞ የማይነካ ነገር ይነካሉ፤ የነኩት ነገር የሚያስከትለው ነገር ደግሞ አያሳስባቸውም። ስለማያሳ ስባቸው ደግሞ ይዳፈሩና ጦስ ያመጣሉ። ሌላው ቀርቶ ተው ይህ ነገር አይሆንም ቢባሉ እንኳን ፣ ያለማመንታት፣ “ደፋርና ጪስ መውጫ አያጣም” ብለው ፤ በፍጻሜያቸው መርዝ ይጠጣሉ።
ክፉ ነገርን መተው የመሰለ ወተት መንገድ ሳለ ፣ አስቸጋሪውን የድፍረት መንገድ መርጦና የሙጥኝ ብለው ለከፋ የመርዝ ፍጻሜ መብቃት አለመታደል ብቻ ሳይሆን አለማስተዋልም ነው። እስቲ አስቡት፤ የሆነ ዓላማን ማሳካት የፈለጉ ሰዎች አንተ ባለህበት ስፍራ፣ እድሉ እና አጋጣሚው ስላለህ ብቻ ሳይሆን፣ ደፋርና ብርቱ ሰው በመሆንህ ይችን ነገር ተናገርልን ፣ ወይም አቅርብልን ወይም ጻፍልን ፣ ብለው ሲሉህ ስላሞካሹህ ብቻ ተነስተህ በድፍረት ባደረግከው ነገር ስትጠየቅ እነርሱ ናቸው ያሉኝ ብለህ ብትል ማን ይሰማሃል? ለነገሩ ምድራችን በብልጥና ራሳቸው ፈሪ በሆኑ ሰዎች አማካይነት ሞኞችን በእሳት ላይ የሚጥዱ ጨካኞች የበዙበት ዘመን ነው።
አንተ የትኛውን ትመርጣለህ ? በማስተዋል ተጠንቅቀህ ትራመዳለህ? ፍርሃትህን ለጥንቃቄህ ሹክ ብለኸው ተገቢውን ትሰራለህ? ወይስ “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም”፣ ብለህ ጭሱ አፍኖ በሚገድልህ ሁኔታ ውስጥ ትገባለህ? አይገባም። በቅንነትና በፍርሃት በመመላለስ፣ ሞገስ ታገኝ ይሆናል እንጂ አታፍርም፤ መልካም ይሆንልሃል እንጂ አትዋረድም። ስለዚህ ነው፤ በድፍረት ላልፈፀምኳቸው ክፋቶች ፍርሃቴን የማመሰግነው።
አሁን ደግሞ በሚያስገርም መንገድ ጸረ-ሰብእ የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ -19 ምድራችንን እንደ ደራሽ ጭጋግ ወርሯታል። በዚህ ዘመንና ጊዜ አስፈላጊው ነገር የተሰጠውን ትእዛዝ ፣ የተደረጉትን መመሪያዎች በመፈጸም ራስንና ቤተሰብን ፣ ራስንና ሐገርን፤ ማህበረሰብን መጠበቅ የተገባ ነው። እያንዳንዱ ሰው ሲጠነቀቅ ለሐገርም ጥንቃቄ ይሆናል፤ እያንዳንዱ ሰው ቫይረሱ የሚደርሰውን ጥቃት ተገንዝቦና ፈርቶ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ካልወሰደ በውጤቱ ማጣፊያ የሌለውን ነገር ሁሉ ነው የምናጣው ።
ሰኞ ማታ በሲኤንኤን ይተላለፍ በነበረ አንድ ፕሮግራም ላይ አንዲት አሜሪካዊ ዋና ነርስ ( ማርጌስ ይባላል ስሟ ) ቀርባ ስትናገር፣ “የገጠመን የመንከባከብ ሥራና እየመጣ ያለው የህመምተኛ ብዛት ሊመጣጠን አልቻለም፤ ለእኛ ደግሞ የመከላከያ ጭንብል ሳኒታይዘር በሉት፣ የፊት መከላከያ ማስክ ወይም ሆነ ጓንት እየቸገረን ነው፤ አስጊ ነው። በግሌ ፍጻሜያችን አስፈርቶኛል፤” ብላለች።
አንዲት የአሜሪካ ሴናተር ደግሞ “ የሰው ልጆችን ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የገጠማቸው እጅግ ግዙፍ የህክምና ዓለም ጦርነት ነው፤ “ ሲሉ ተደምጠዋል። የ2ኛው የዓለም ጦርነት ዓውደ ውጊያ በስፋት የነበረው አውሮፓና በከፊል ኤዥያን ያካተተ ሲሆን አሁን ግን እውነተኛው ምድራችን ገጥሟት የማያውቀው የዓለም ጦርነት ነው። በምድር ዙሪያ ያልተመዘገበበት ቦታ ቢኖር ሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች ማለትም አንታርክቲክና አርክቲክ ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም በእዚያ ሰው ስለማይኖር እንጂ የሰው ልጆች ባሉበት ስፍራ ሁሉ ቫይረሱ ደርሷል። ኣለም በሮቿን ጠርቅማ በራሷ መንገድ ብቻ የምትገባውና የምትወጣው ሰሜን ኮሪያ እንኳን 5 ሰዎች የተያዙባት መሆኑን ዘግባለች። ከተገኘ፣ የተገኘበትን ሰው እገድላለሁ እስከማለት የዘለቀ መግለጫ ያወጣችው ሐገር ዛሬ የመያዟ እውነት ተነግሯል።
ኮሮና ፣ በሳውዲ ዓረቢያ “ትመጣና ወየውልህ”፤ ተብሏል ። ማስፈራራት የማያስቀረው ግን እኛ ከፈራንና ራሳችንን በቤት ውስጥ ከቆጠብን የምንገላገለው አጥፊ ወረርሽኝ ነው። ኮሮና መምጫው መንገድ የታወቀ ግን ያልታሰበ፣ መከላከያውም የተነገረ፣ ከተያዝን በኋላ ግን የሚተላለፍበት መንገድ ደግሞ የረቀቀ በመሆኑ እጃችንን፣ መገልገያ ቁሶቻችንን፣ የምንነዳቸውን መኪኖች፣ የምንሾፍራቸውን ሞተሮችና ብስክሌቶች እጀታ ፣ የኮምፒዩተር ማውዞች፣ ኪቦርዶች ለጊዜው ከሌሎች ጋር ባለመጋራት ፣ የምንከፍትና የምንዘጋቸውን በሮች፣ እጀታ ሁሉ በጥንቃቄ ለመጠቀም ከሞከርን አደጋውን እንቀንሳለን። ስልኮቻችንን በምንም ምክንያት ለሌሎች አለማዋስ መልካም ነው። ንፍገት አይደለም ፤ ጥንቃቄ እንጂ፣ ጥላቻ አይደለም፤ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መፍራት እንጂ።
ፍርሃት የሚጠቅመው ክፋትን ላለማድረግም ስለሆነ አሁን አሁን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንደምናያቸው አንዳንድ ክፋቶች ጸረ-ማኅበረሰብ የሆኑ ክፋቶችን ባለመፈጸም ፍርሃቶች ውስጥ ማለፍ ምንኛ ጠቃሚና ቀና ሰዎች ያደርገናል መሰላችሁ።
ስለዚህ ኮሮና ሆይ እንፈራህ ዘንድ ግድ በሆነበት ጊዜ ላይ ነንና አንተ በማክሮና ማይክሮስኮፕ ብቻ ወይም ከዚህ በረቀቁና በደቀቁ መመርመሪያዎች የምትታይ ደቃቅ ተሃዋሲ ብትሆንም ክብደታችን ከ40 እስከ 100 እና 150 የምናህለውን ግዙፋን የሰው ልጆችን የመተንፈሻ አካላት አፍነህና አድቅቀህ መጣል፣ ጥለህም እስከወዲያኛው እንድናሸልብ ማድረግ መቻልህን በጣሊያን ከ12ሺህ በላ ነፍሶችን ነጥቀህ ፣ በቻይና የዚህን 1/3ኛ ቁጥር ያህል፣ በስፔን ወደ 3000 ሰው ገደማ፣ እየቀጠፍክ በአፍሪካ አንዳንድ ሰሜናዊ፣ ምስራቃዊ፣ ደቡባዊ ሐገሮችና እስያ በደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሲንጋፖር፣ ፊሊፒንስና ኢንዶኔዥያ፣ አውስትራሊያና ላቲን አሜሪካ ፣ ካናዳ ሠው እንደ ቅጠል እያረገፍክ እያየን ነው።
ሩዋንዳ በኮሮና ሳቢያ በአዋጅ የከለከለችውን የስብሰባ አዋጅ ጥሰው፣ ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን፤ ያሉ “ደፋሮች” አደባባይ በመውጣታቸው ፖሊስ በወሰደው የአጸፋ እርምጃ የሁለት ሰው ህይወት አልፏል። ፈርተውና አርፈው ቢቀመጡ ለፖሊስም ጦስ ለመንግስትም ሃዘን ባልሆኑ። ክፉ ደፋሮች ለራሳቸውም አይሆኑ፤ ለሌላውም ጠንቅ በመሆን ይታወቃሉ። ናይጄሪያ እንኳንስ የተቃውሞ የድጋፍ ሰልፍ አይፈቀድም ብላለች። አልጄሪያ ፣ ባለፉት አራት ወራት ፣ በተቃውሞ በየሳምንቱ አርብ አርብ ስትናጥ ቆይታ ኮሮና አደብ አስገዝቷቸዋል።
ስለዚህ ኮሮና ሆይ! በብዙ ጥንቃቄ ይህንን ገዳይ እጆችህንና ሃይልህን በመፍራት ልናሳልፍህ የግድ ነው። በኮሮና የድፍረት መብት የለም ፤ ኮሮናን በህክምና እንጂ ኮሮናን በአካል ገጥሞ ያሸነፈ ሰብኣዊ አካል የለምና ፤ ሳንወድ በግድ ልንፈራው ይገባል፤ እኔም መፍራቴን አውቃለሁ። ስለዚህ እነዚህ ቀኖች ያልፋሉ፤ አልፈውም ቀናቱ የፈጠሩብን ስሜቶችና ሰቆቃዎች፣ ፍርሃትና ትጋታችንን ፣ ልንተርካቸው የምንችልበት ቀን እንዳይረዝም ከፈለግን በፍርሃት ጥንቃቄና በጸሎት ጉልበት ፤ በእምነት ድፍረትና በስጋት ቁጥብነት እንለፈው ።
ሙጋቤ አሉት ተብሎ የተነገረውን ግን ባይሉትም ጠቃሚ ነገር ነውና ጽሑፌን በዚሁ ልደምድም ። አፍሪካ ውስጥ፣ አስቸጋሪው ነገር ህዝቡ የተባለው ትቶ ያልተባለውን ወይም በተቃራኒው ማድረጉ ነው። “እግረኞች ሆይ፣ በተሸከርካሪ በስተግራ ያለውን መንገድ ይዛችሁ ተጓዙ ሲባሉ፣ አዋጁን መነገሩን ለማረጋገጥ በስተቀኝ መሄድን ይመርጣሉ። ሁላችሁም ወደ ደጅ ባለመውጣትና በቤታችሁ በመቀመጥ ወረርሽኙን እንከላከል ፤ ሲባሉም ምን ያህል ሰው በቤቱ እንዳልተቀመጠ ለማረጋገጥ ብዙ ሰዎች ወደደጅ ይወጣሉ” እንደተባለው እንዳንሆን በፍርሃት ብልሃት በቤታችን በመሆን ኮሮናን እንከላከል። ኮሮና፣ አንተ ግን፣ መጥኔውን ይስጥህ፤ እኔስ ከፍርሀቴ ጋር ቤቴ ተቀመጥኩ!! መልካም ፣ የመቀመጥና የመከላከል ሳምንት ይሁንልን ፤
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ