አዳማ፡- በአዳማ ከተማ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ሊመልሱ የሚችሉና 500 ሚሊየን ብር የወጣባቸው ከ20 በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ዛሬ እንደሚመረቁ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአዳማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማው ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በመርሃ ግብሩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን፤ ፕሮጀክቶቹ ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደሚፈቱም ይታመናል፡፡
ዛሬ ለምረቃ ከሚበቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ለ10 ዓመት የተጓተተውና ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ ሲነሳበት የቆየው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሆነ ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡
በአዳማ የመኖርያ ቤት ችግር ለአመታት መሰረታዊ ጥያቄ እንደነበር የጠቆሙት አቶ መስፍን ችግሩን ለመቅረፍ ከዚህ ወደም ግንባታ ቢካሄድም ጥያቄውና አቅርቦቱ የማይመጣጠን በመሆኑ ችግሩ አለመፈታቱን አብራርተዋል፡፡ በእለቱ የሚመረቁት368 መኖርያ ቤቶች ሲሆኑ ችግሩን ለመፍታም አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በከተማዋ በክረምት ወቅት ጎርፍ በትክክለኛ መንገድ ባለመሄዱ የህዝቡን ንብረት ያወድም እንደነበር የገለፁት አቶ መስፍን ችግሩን ለመፍታትም በ11 ሚሊየን ብር የጎርፍ መከላከያ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ቀድሞ በችግሩ ይጠቁ የነበሩ የደንበላ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችን ችግር መፍታት እንደሚያስችል ተናረዋል፡፡
ከድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በመተባበር ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት የሚቀይር ተቋም ግንባታ በአገሪቱ በአንደኛ ደረጃ መጠናቀቅ፣ የአስፋልትና ሌሎች መንገድ ዝርጋታዎች፣ ለጤናና ለወጣቶች መዋያ የሚሆኑ ፓርኮችም በምረቃው የሚካተቱ ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር በሰባት ሔክታር ላይ ያረፈውና የኦሮሞ ባህልን የሚያሳየው የኦቦ ፓርክን በማስፋፋት አሁን ካለበት ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራም ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፓርኩ የበይነ መረብ አገልግሎት የሚሰጥበት፣ የስፖርት ማዕከላትን እንዲሁም የተለያዩ መዝናኛዎችን ያቀፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድልንም የሚከፍት እንደሆነ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከተማዋን ውብና ማራኪ ከማድረግ ባሻገር ተያያዥ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ያቃልላል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
በፍዮሪ ተወልደ