አዲስ አበባ፡- የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ወቅታዊ ሁኔታን መሰረት አድርገው በመሰረታዊ ፍጆታዎችና የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉት ላይ የማጣራት ሥራ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን በአጭር ጊዜ ለመከላከል የሚያግዝ ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገለጸ።
በባለስልጣኑ የአቤቱታ፣ ምርመራና ክስ አቀራረብ ዳይሬክተር ጌትነት አሸናፊ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ሰሞኑን በተለያዩ የንግድ ቦታዎች በመዘዋወር ባደረገው የማጣራት ሥራ አንዳንድ ነጋዴዎች የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ደርሶበታል።
በዚሁ መሰረትም በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 14 ነጋዴዎች፣ ለበሽታው ቅድመ መከላከያ የሚውል የእጅ ንጽህና መጠበቂያና መከላከያ ላይ በተመሳሳይ ችግር የፈጠሩ ሁለት አስመጭዎችና ዘጠኝ አከፋፋዮችን ጠርቶ በማነጋገር የማጣራት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።
ጤፍ፣ በርበሬና ዘይት ላይም ቀደም ሲል ከነበረው ዋጋ መጨመሩንና ከ3 ሺ 800ብር እስከ 4ሺ 600 ብር ዋጋ እየተሸጠ መሆኑን ከሸማቾች ከሰበሰበው መረጃና ባለስልጣኑ በራሱም ባካሄደው አሰሳ አረጋግጧል።
ባለስልጣኑ የወቅቱን የወረርሽኝ በሽታ ምክንያት አድርገው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በመገናኛ ብዙሃን በማስጠንቀቅ መልዕክት ማስተላለፉንና ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የክትትል ሥራውን ማጠናከሩን ገልጸዋል።
የንግድ ሱቆችን እስከማሸግ የደረሰ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም አስታውቀዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ዋጋ የሚያስጨምር በቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አለመኖሩንም ተናግረዋል። ሸማቹም ከሚያስፈልገው በላይ መሸመቱ ለችግሩ መባባስ መንስኤ መሆኑን አመልክተዋል።
ባለስልጣኑ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የዋጋ ንረትን የሚያስከትሉ ነጋዴዎችን በመቅጣት ብቻ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል የጠቆሙት አቶ ጌትነት እየሰሩ ህጋዊ መስመር የሚይዙበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
እርሳቸው እንዳሉት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል በተለይም መረጃ ሰብስቦ እርምጃ ለማስወሰድ የሚወስደው ጊዜ ረጅም ሂደትን የሚጠይቅ መሆኑ ቀድሞ የተያዘው ጉዳይ ሳይፈታ ተመሳሳይ ሁኔታ እየፈጠረ በባለስልጣኑ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ሥራው በሸማቹ አመኔታ እንዲያጣም አድርጎታል። በመሆኑም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት በሚፈጠርበት ወቅት ጥብቅ ምርመራ ማድረግ ሳያስፈልግ ነባራዊ ሁኔታውን ባገናዘበ ትዕዛዝ ማስተላለፍና በትዕዛዙ ያልተመራውን ደግሞ በህግ መጠየቅ የሚቻልበትን አሰራር ለመዘርጋት ታስቧል። አሰራሩ በህግ እንዲደገፍና ሌሎችም ማሻሻያዎች የተካተተበት ረቂቅ የህግ ተዘጋጅቷል።
ባለስልጣኑ ባለፉት አመታት ባከናወናቸው ሥራዎች ሸማቹን ሙሉ ለሙሉ ያረካ ነው ብሎ ባያምንም ባለስልጣኑ በመኖሩ ከመስመር ሊወጡ የነበሩትን መመለስ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ጌትነት፣ ከትምህርትቤት ክፍያ ጋር በተያያዘ ይስተዋል የነበረን ችግር ለመቅረፍ ባደረገው እንቅስቃሴ በ 150 ት/ቤቶች ላይ ጥናት በማካሄድ መመሪያ እንዲሻሻል ማድረጉን፣ በ14 ትምህርት ቤቶች ላይ ክስ መመስረቱን፣ ለሁለት መቶ ት/ቤቶች ደግሞ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በ12 ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
እነዚህ ሥራዎች ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ባይቀርፉትም ቅሬታው የበለጠ ይሆን እንደነበር ገልጸዋል። ሸማቹ ካጋጠመው የንግድ ጉድለት ጋር በተያያዘ በሰራው ሥራም ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ብር የሚገመት ሸማቾች ይዘው ቀርበው ትክክለኛው የንግድ ዕቃ እንዲመለስላቸው ማድረጉንም አመልክተዋል። አሳሳችና ሳይንሳዊ ሂደትን ያልተከተለ የንግድ ማስታወቂያን ማስቀረቱንም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012
ለምለም መንግሥቱ