አዲስ አበባ፡- የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመግታት በማሰብ አራት ሺ 11 ታራሚዎችና በይቅርታ እንዲፈቱ፤ 33 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑንና ከዛሬ ጀምሮ ከማረሚያ ቤቶቹ እንዲወጡ መደረጉን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገለጸ።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ከኮሮና ቫይረስ የስርጭት ባህሪ አንጻር በማረሚያ ቤቶች መተፋፈግን ለማስቀረትና ለሚቀሩ ታራሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል ውሳኔው መተላለፉን ተናግረዋል። ውሳኔውን የይቅርታ ቦርድ ማጣራቱንና በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲጸድቅ መደረጉንም አክለዋል።
በሁሉም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ለአራት ሺ 11 ታራሚዎች ይቅርታ፣ ለ33 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ጠቁመዋል። ይቅርታ የተደረገላቸው እስከ ሶስት ዓመታት በሚያስቀጣ ቀላል ወንጀል ዓይነቶች የፍርድ ውሳኔ ያገኙ ሁሉም ታራሚዎች፣ የእስር ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙ እና በህጉ መሰረት ለመፈታት አንድ ዓመት ያህል የሚቀራቸው ሁሉም ታራሚዎች መሆናቸውን ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።
እንዲሁም ከግድያ ወንጀል ውጭ በሌሎች ወንጀሎች የፍርድ ውሳኔ ያገኙ፣ ከህጻናት ጋር ማረሚያ ቤት የሚገኙ እና ነፍሰ ጡር መሆናቸው የተረጋገጡ ሁሉም ታራሚዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል። ከግድያ ወንጀል ውጭ በሌሎች ወንጀሎች እንደ የአደንዛዥ ዕጽ ማዘዋወር፣ የማታለልና በመሳሰሉት ወንጀሎች የፍርድ ውሳኔ ያገኙ ሁሉም የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲለቀቁ መወሰኑንም ገልፀዋል።
የክስ ማቋረጥ ውሳኔን በተመለከተ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ክርክርና ክስ ሂደት ላይ የሚገኙ እና ከግድያ ወንጀል ውጭ በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው ከህጻናት ጋር ማረሚያ ቤት የሚገኙ፣ ነፍሰ ጡር መሆናቸው የተረጋገጡ ታራሚዎች እንደተካተቱበትም ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም በመንግስት ተወስኖ ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረገው 63 ግለሰቦች ጋር በተመሣሣይ ደረጃ የሚገኙ፣ በዋና የወንጀል አድራጊነት ያልተሳተፉ፣ ከዚህ በፊት ክሳቸው ያልተቋረጠና በሂደት ላይ የሚገኙ 33 ተጠርጣሪ ግለሰቦችም ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉንም አመልክተዋል።
እነዚህ በይቅርታ እንዲፈቱ እና ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነላቸው አካላት ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ተመልሰው የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው ቢገኙ የተሰጣቸው ይቅርታም ሆነ የተቋረጠው የክስ ውሳኔ ቀሪ እንደሚሆን በመግለጫው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታትና ለመከላከል በተቋም ደረጃ የሚወሰዱ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት የተቀመጠውን አቅጣጫ መፈጸሙን ተናግረዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ተጠሪ ተቋማት በአጠቃላይ ካሉት ሰራተኞች ውስጥ 20 ከመቶ የሚሆኑት በቤታቸው ሆነው የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲፈጽሙ መደረጉን ተናግረዋል።
በተለይም የተጠርጣሪዎችን መዛግብት የማጣራት ሥራዎችን የሚሰሩ የተወሰኑ ሰራተኞች ቢሮ ገብተው ከንክኪ እና መተፋፈግ በጸዳ መልኩ ሥራዎቸቸውን እንዲሰሩ እንደተወሰነ፣ በሥራ ላይ ለሚቆዩ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት እና ምቹ የሥራ ቦታ እንደሚፈጠርላቸው ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2012