አዳማ፦ በባህላዊ መንገድ ሲሰጥ የኖረውን የኢስላማዊ ትምሕርት በዘመናዊ መልኩ ለመስጠት የሚያስችል፤ በኢትዮጵያም የመጀመሪያ የሆነ ‹ኢማሙ አል ሻፊ› የተባለ ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአዳማ ተመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው መሥራች፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጥሪ ማኅበር ፕሬዚዳንትና የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ ሼህ ሃጂ ኢብራሂም፤ ከዚህ ቀደም ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ዕውን መሆን «ብዙ ውጣውረድ ያሳለፍንበት ቢሆንም ውጤቱ ያመረ፤ ለወደፊት ህልማችንም ተስፋ ሆኗል» ብለዋል።
እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲው ከ10 ዓመታት በፊት ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተረከበው 30ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው። ለምርቃት በደረሰበት ደረጃ 16 መማሪያ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፤ ለሴቶችና ለወንዶች የተለያየ የማደሪያ ስፍራ፤ የመፃሕፍት ቤትና መመገቢያ ያሟላ ነው። የተጠናቀቀው ሥራም 7 ሚልየን ብር ሲፈጅ የቀሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ 3 ነጥብ 5 ሚልየን ብር ያስፈልጋል።
«ጅምሩ ይህ ይሁን እንጂ የተለያዩ ግንባታዎች ይገነባሉ።» ያሉት ሃጂ ኢብራሂም፤ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ለመቀበልና ለማሳደግ እቅድ መኖሩን ገልጸዋል። እነዚህን ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግም 5 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት መሆኑን በመግለጽም፤ 2,000 ተማሪዎችን ሲቀበል በርቀት መማር ለሚፈልጉ ሦስት ሺህ ወንበሮች እንዳሉት አስታውሰዋል።
በዩኒቨርሲቲው ምርቃት ላይ የታደሙት ሐጂ ሙፍቲ ኢድሪስ ባደረጉት ንግግር፤ የመጀመሪያውን ሃይማኖታዊ መማሪያ በመከፈቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ስያሜውም በኢማም ሻፊ ስም መሆኑ ለአገራችን ክብርና ፀጋ ነው ብለዋል። አያይዘውም ከሃይማኖት አባቶችና መምህራን መልካም ነገር መውጣት አለበት። ከፈጣሪ ያገኘነውን ምክርና ሰላማዊ አገራዊ ተግባራት መከወን ይገባል ብለዋል፡፡ መረዳዳት ብሎም መከባበር እንዲኖርና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአንድነት እንዲቆምም ጥሪአቸውን በአደራ አቅርበዋል።
«ይህ ኮሌጅ ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል» ያሉት ደግሞ ኡስታዝ አቡበከር መሐመድ ናቸው። እንደእርሳቸው ገለጻ፤ ሃይማኖታዊ የትምህርት ተቋማት ትውልድ የሚቀርፁ እንዲሁም ማኅበረሰብን የሚያንፁ ናቸው። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ረጅም ህልም ያለው እንዲሆንና ያለ ረጅም ህልም ትውልድን ማፍራት እንደማይቻል ጠቁመዋል። እናም ኮሌጁ የተወሰኑ ሰዎች የሚጠቀሙበት ሳይሆን ሁሉንም አቃፊ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ባለስልጣናትና የሃይማኖቱ አባቶች እንዲሁም ከተለያየ ከተማ የተውጣጡ በርካታ ምዕመናን ታድመዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጥሪ ማኅበር ከተመሠረተ 17 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፤ በተለያዩ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። ከዚህ ቀደምም ማህበሩ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው በማስተማር ተማሪዎችን ለ8 ዓመታት አስመርቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
በሊድያ ተስፋዬ
ፎቶ፡- ሀዱሽ አብርሃ