አዲስ አበባ ፡- መንግስት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ለአካል ጉዳተኛው ተደራሽ አለመሆናቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴረሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ጉጆ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ተጠቂዎችን ለማከምና ስርጭቱን ለመግታት በሚደረገው ርብርብ አካል ጉዳተኞች ሊደረግላቸው የሚገባው ትኩረት እንደተነፈጉ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ በላይነህ ገለጻ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞችን መብት ደህንነት ልዩ ሪፖርተር ካታሊና ዴቫንዳስ የገለፁትን ሀሳብ ዋቢ በማድረግ በሀገራችን ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የሚሰጠው መረጃ በሚፈለገው ሁኔታ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች መረጃዎችን ሲያስተላልፉ ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት አልተሰጡም፡፡ ይህ ሊታረም ይገባዋል ብለዋል፡፡
እንደስራ አስኪያጁ ገለፃ፣ በሀገራችን የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምክንያት ለኮሮና ቫይረስ የበለጠ ተጋላጮች ስለሆኑ ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽኑ ስለሚያደርጉት ጥንቃቄ መረጃዎችን እየሰጠ ቢገኝም የአቅም ውስንነት በመኖሩ ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም፤
በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በሚፈለገው መንገድ የግንዛቤ ማስጨበጫውን በማስተላለፍ ሰለባ እንዳይሆኑ እንክብካቤና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ጥበቃ ጋር መረጃዎችን ለህበረተሰቡ በሚሰጥበት ወቅት አካል ጉዳተኞች የሌሎችን እገዛ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው ተገቢውን መረጃ ማስተላለፍ ይገባል ያሉት አቶ አባይነህ መረጃዎችን በሚሰጡበት ወቅት ለአይነ ስውራንና መስማት ለተሳናቸው በቂ መረጃ በመስጠት የኮረና ቫይረስ ሰለባ እንዳይሆኑ ማደረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ በበኩላቸው አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ከድህነት ወለል በታች ስለሚኖሩ ለመከላከሉ የሚያግዙ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን መግዛት አይችሉም ፤ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በተለይም አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙባቸው እንደ ክራንች፣ ዌልቸርና የመሳሰሉት ሁሉ ንፅህናን መጠበቅ ስለሚስፈልግ ልዩ ትኩረትን ይሻሉ ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው አካል ጉዳተኞች ስለቫይረሱ መረጃውን በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ ቤተሰቦቻቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊንከባከቧቸው ይገባል፡፡ አካል ጉዳተኞች ለድጋፍ የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያዎች በጥንቃቄ ከአላስፈላጊ ንክኪ ተቆጥበው መጠቀምና በጤና ሚኒስቴር መመሪያ መሰረት በየወቅቱ በንፅህና መጠበቂያ ኬሚካሎች ማፅዳት እንዲችሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
ሞገስ ተስፋ